የሩሲያው ወታደራዊ ቡድን ''በሊቢያ እየተዋጋ ነው''

ወታደራዊ ታንክ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በመቶዎች የሚቆጠሩ የሩሲያ ስውር የወታደራዊ ኃይሎች በሊቢያ አማፂያንን በደገፍ እየተዋጉ መሆኑን ሾልኮ የወጣ የተባበሩት መንግሥታት ሪፖርት ገለፀ።

ወታደራዊ ኃይሉ አማፂው ጄነራል ካሊፋ ሃፍታርን በመደገፍ መቀመጫውን ትሪፖሊ ያደረገውን መንግሥት ይወጋል።

እ.ኤ.አ. ከ2014 ጀምሮ ሊቢያ በሁለቱ ቡድኖች መካከል ተከፋፍላ ትገኛለች።

ይሄው የሩሲያ ወታደራዊ ኃይል 'ዋግነር' ተብሎ የሚታወቅ ሲሆን በዩክሬን፣ ሶሪያ እና ሌሎች አካባቢዎች ባሉ ግጭቶች ውስጥ ተሳትፎ እንዳለው ይታመናል።

የሩሲያ መንግሥት በሁለቱ ተዋጊዎች መካከል ምንም ዓይነት ወታደራዊ ተሳትፎ እንደሌለው በመግለፅ አስተባብሏል። ዋግነር የሚባሉት ወታደራዊ ኃይሎች በቀድሞው የሩሲያ ልዩ ኃይል ባልደረባ ዲሚትሪ ኡትኪን መመስረቱ ይነገርለታል።

የተባበሩት መንግሥታት ሪፖርት ምን ይላል?

ሪፖርቱ የተጠናቀረው የተባበሩት መንግሥታት በሊቢያ ላይ የጣለውን ማዕቀብ በሚመለከተው ገለልተኛ ቡድን ነው። ሪፖርቱ ይፋ ባይሆንም በዜና ተቋማት እጅ ውስጥ ግን ገብቷል።

የተባበሩት መንግሥታት በሊቢያ ዋግነር ስለላው ተሳትፎ በይፋ ሲናገር የመጀመሪያ ጊዜው ነው። የመንግሥታቱ ድርጅት እንደሚለው ወታደሮቹ ከ 800 እስከ 1000 ያህል ይሆናሉ።

ይህ ባለ 57 ገፅ ሪፖርት እንደሚለው ዋግነር የተሰኘው የሩሲያ ወታደራዊ ኃይል እ.አ.አ. ከጥቅምት 2018 ጀምሮ በሊቢያ ነበር።

"ለወታደራዊ መኪኖች እና በጦርነቱ ላይ ለሚሳተፉ የቴክኒክ ድጋፍ ይሰጣል"

አባላቱ የጦር መሳሪያ እንዲሁም የአየር ቅኝት በማድረግ የሚሳተፉ ሲሆን በተጨማሪም " ከተቃራኒ ወገን የሚመጡ የኤሌክትሮኒክ ሞገዶችን ምላሽ ለመስጠት ሙያዊ ድጋፍ ማድረግና አልሞ ተኳሽ በመሆን ይሰማራሉ" ተብሏል።

ወታደሮቹ አብዛኞቹ ሩሲያውያን ሲሆኑ ነገር ግን የቤላሩስ፣ ሞልዶቫ፣ ሰርቢያ እና ዩክሬን ዜጎችም እንዳሉበት በሪፖርቱ ላይ ተገልጿል።

ከዚህ ቀደም ፕሬዝዳንት ፑቲን በሊቢያ የሚገኝ ማንኛውም ሩሲያዊ አገራቸውን እንደማይወክል እንዲሁም በመንግሥታቸው ተከፋይ አለመሆኑን ገልፀው ነበር።

የመንግሥታቱ ድርጅት ሪፖርት እንደሚለው ከሆነ የሶሪያ ቅጥረኞች ከጄነራል ሃፍታር ጎን ሆነው እየተዋጉ ነው።

ሊቢያ ሙዓመር ጋዳፊ እ.አ.አ. በ 2011 በሕዝባዊ ተቃውሞ ከስልጣን ከወረዱና ከተገደሉ በኋላ ጀምሮ በእርስ በርስ ጦርነት እየታመሰች ነው።

በሊቢያ ዓለም አቀፋዊ እውቅና ያለው መንግሥት ያለ ሲሆን በኳታር፣ እና በቱርክ ይደገፋል።

በዚህ መቀመጫውን በትሪፖሊ ባደረገው መንግሥት ላይ ከሚያዚያ ወር ጀምሮ የጄነራል ሃፍታር አማፂ ኃይል ጥቃት መሰንዘሩን አጠናክሮ ቀጥሏል።