ለወንጌላዊያን አብያተክርስቲያናት ካውንስል እውቅና እንዲሰጥ መንግሥት ወሰነ

የሚኒስትሮች ምክር ቤት

የፎቶው ባለመብት, Office of the Prime Minister of Ethiopia

የኢትዮጵያ መንግሥት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለኢትዮጵያ ወንጌላዊያን አብያ ተክርስቲያናት ካውንስል እውቅና ለማስሰጠት በተወካዮች ምክር ቤት እንዲጸድቅ ወሰነ።

ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት የወጣው መግለጫ እንዳመለከተው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባው ላይ የወንጌላዊያን ካውንስልን ጉዳይ ከሌሎች ሦስት ጉዳዮች ጋር ተመልክቶ ነው ውሳኔ የሰጠው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በተለያዩ ጊዜያት በአገሪቱ ያሉ የወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያናት ተጠሪዎችን በመሰብሰብ ኅብረት እንዲፈጥሩና እንዲሰባሰቡ ሲያበረታቷቸው መቆየታቸው ይታወሳል።

ዛሬ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ተመልክቶ ወደ ተወካዮች ከመራቸው ጉዳዮች መካከል ቀዳሚው የሆነው የኢትዮጵያ ወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ሕጋዊ ዕውቅና ለመስጠት የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ በስፋት ማወያየቱን ተገልጿል።

በዚህም የአብያተ ክርስቲያናቱ ኅብረቶች ያቋቋሙትን አገር አቀፍ ተቋም የሕግ ሰውነት እንዲያገኝ መደረጉ ተገቢ መሆኑ በመታመኑ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ ምክር ቤቱ ተቀብሎት እንዲጸድቅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ መወሰኑ ተጠቁሟል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መሪዎች መካከል ለዘመናት የነበረውን አለመግባባት በዕርቅ እንዲፈታ በማድረግ በሰሜን አሜሪካ እና ኢትዮጵያ ውስጥ ለሁለት ተከፍሎ የነበረውን የቤተክርስቲያኗን ሲኖዶስ ወደ አንድ እንዲመጡ አስችለዋል።

በተጨማሪም በተመሳሳይ በእስልምና እምነት ተቋም ውስጥ የነበረውን ልዩነትና አለመግባባት ሁሉም የዕምነቱ ተከታዮች ተቀራርበው በመነጋገር ፈትተው ወደ አንድነት እንዲመጡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያደረጉት ጥረት ውጤታማ እንደነበር ይታወሳል።

በተጨማሪም በአገሪቱ ያሉት እነዚህ የዕምነት ተቋማት በመንግሥት በኩል የሚያስፈልጋቸውን ሕጋዊ ዕውቅና እንዲያገኙ ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ የአገሪቱ መንግሥት የተለያዩ እርምጃዎችን ወስዷል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ ከኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ዕውቅና በተጨማሪም የብሔራዊ ትራንስፖርት ፖሊሲን እና የሎጂስቲክስ ዘርፍ ፖሊሲን፣ የኢትየጵያ ልማት ባንክ ማቋቋሚያ ደንብ ማሻሻያን ተመልክቶ ውሳኔ ማሳለፉ ተገልጿል።