ትራምፕ 'ቀላል ጉንፋን ነው' ያሉት ቫይረስ የ100ሺህ ዜጎቻቸውን ህይወት ነጠቀ

ሃኪም

የፎቶው ባለመብት, Reuters

አሜሪካ በኮሮናቫይረስ የሞቱባት ዜጎች ቁጥር በቬትናም፣ በኢራቅ፣ በአፍጋኒስታንና በኮሪያ ጦርነቶች በድምሩ ከሞቱትም በላይ ሆኗል፡፡

በጥር 21 የመጀመርያው በኮሮናቫይረስ የተያዘ ሰው በአሜሪካ ተገኘ፡፡

ዶናልድ ትራምፕ ለነገሩ ፊትም አልሰጡትም ነበር፡፡ ‹‹ቀላል ጉንፋን ነው›› ሲሉት ነበር፡፡ ቀጥለው ደግሞ ‹‹ሥራ ፈት ዲሞክራቶች እኔን ለማሳጣት የፈጠሩት አሉባልታ ነው›› እያሉ አጣጣሉት፡፡ ትንሽ ቆይተው ‹‹ተራ ነገር ነው፤ ሰሞኑን ብን ብሎ ይጠፋል›› አሉ፡፡ በኋላ ላይ ነገር ዓለሙ ሲምታታባቸው ከልብስ ማጽጃ ኬሚካል እስከ ወባ መድኃኒት ውሰዱበት ማለት ጀመሩ፡፡

እውነት ለመናገር ትራምፕም ሆነ ሌሎች ፖለቲከኞች ወረርሽኙ በዚህ አጭር ጊዜ እንዲህ አሜሪካንን የሚያህል አገር በእምብርክክ ያስኬዳል ያለ አልነበረም፡፡

የሆነው ማንም ከገመተው በላይ ነው፡፡

በተለይ በሕክምናም ሆነ በኅብረተሰብ ጤና እጅግ መጥቃለች የምትባለው ኃያል አሜሪካን በዚህ ደረጃ የሚዳፈር ወረርሽኝ ይኖራል ያለ ነበር ለማለት ይከብዳል፡፡

እነሆ ኮቪድ በአራት ወራት ውስጥ አንድ ሚሊዮን ሰባት መቶ ሺህ ዜጎቿን ሰቅዞ ይዞ፣ አንድ መቶ ሺዎቹን ደግሞ ከዚህ ዓለም በሞት አሰናብቷል፡፡

በሌላ ቋንቋ በዓለም ላይ በዚህ ክፉ ደዌ ከተያዘው ሰው 30 እጁ አሜሪካዊ ነው እንደማለት ነው፡፡

በሟቾችም ሆነ በተያዦች ቁጥር አሜሪካ የዓለም ቁንጮ ትሁን እንጂ ከሕዝቧ ስፋት አንጻር የሟቾች አሀዝ ሲሰራ አሜሪካ በዓለም 9ኛዋ ተጠቂ አገር ነው የምትሆነው፡፡

አሁን በመላው ዓለም የተያዦች ቁጥር አምስት ሚሊዮን ስድስት መቶ ሺ አልፏል፡፡

በአሜሪካ የሟቾች ቁጥር መቶ ሺ ሲዘል ጠቅላላው የዓለም የሟቾች ቁጥር ደግሞ ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ 354 ሺህ 984 ደርሷል፡፡

አሐዞችን እየተከታተለ ይፋ የሚያደርገው የጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ የመረጃ ቋት እንደሚያስረዳው አሁን በትክክል በአሜሪካ ምድር የተመዘገው የሟቾች ቁጥር 100ሺህ 276 ነው፡፡

የቢቢሲው የሰሜን አሜሪካ የፖለቲካ አርታኢ ባልደረባችን ጆን ሶፔል ይህንን ቁጥር በተሸለ ሲገልጸው አሜሪካ አሁን በኮቪድ-19 ያጣቻቸው ዜጎቿ ቁጥር በታላቁ የቬትናም ጦርነት፣ በኢራቅ፣ በኮሪያ፣ በአፍጋኒስታን ባለፉት 44 ዓመታት የሞቱባት ዜጎች ተደምረው እንኳ የሚበልጥ ነው፡፡