በብራዚል በአንድ ቀን ብቻ 33 ሺህ ሰዎች በኮሮና ተያዙ

ብራዚል ውስት ፀሎት የሚያደርጉ አዛውንት

የፎቶው ባለመብት, AFP

የብራዚሉ ቀኝ አክራሪ ፕሬዝዳንት ጄር ቦልሶናሮ ዛሬም ድረስ ‹‹ለጉንፋን እጅ አትስጡ›› እያሉ ነው፡፡ የአገራቸው ሕዝብ ግን በኮቪድ- 19 እየረገፈ ነው፡፡

ቅዳሜ ዕለት ብቻ የአገሪቱ ጤና ጥበቃ ይፋ እንዳደረገው 33 ሺህ ዜጎች በቫይረሱ ተይዘዋል፡፡ ትናንትና ደግሞ 1000 ሰዎች ሞተዋል፡፡

አሁን ብራዚል በዓለም ላይ በሟቾች ቁጥር ፈረንሳይን በልጣ ከአሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ጣሊያንን ተከትላ 4ኛ ሆናለች፡፡

በጠቅላላ የሞቱባት ዜጎችም 28 ሺህ 834 ደርሰዋል፡፡

ብራዚል አሁን በሟቾች ቁጥር ከዓለም 4ኛ ትሁን እንጂ በቀጣይ ቀናት አሜሪካንን ተከትላ 2ኛ እንደምትሆን ባለሞያዎች ቅንጣት ጥርጣሬ የላቸውም፡፡ ይህን እንዲተነብዩ ያስቻላቸው ደግሞ ቫይረሱ በዚያች አገር የሚዛመትበት ፍጥነት አስደንጋጭ በመሆኑ ነው፡፡

አወዛጋቢው የቀኝ አክራሪ መሪ ጄር ቦልሴኔሮ አሁንም ሕዝባቸውን ለኮቪድ እጅ መስጠቱን ትቶ ወጥቶ ሥራ እንዲሰራ እየመከሩት ነው፡፡ ለዚህ አመለካከታቸው በርካታ ደጋፊም አላቸው፡፡

ብራዚል በቫይረሱ የተያዙትባት ሰዎች ጠቅላላ ቁጥር ግማሽ ሚሊዮን ደርሷል፡፡ ይህም ከአሜሪካ ቀጥላ ዓለምን በ2ኛነት ተጎጂ አገር ያደርጋታል፡፡

በአሜሪካ አሁን የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከአንድ ሚሊዮን ሰባት መቶ ሺህ ከፍ ብሏል፡፡

ፕሬዝዳንት ቦልሴኔሮ ከሪዮ ዴጄኔሮ ገዢና ከሌሎችም አስተዳዳሪዎች ጋር ሽኩቻ ውስጥ ናቸው፡፡

እርሳቸው ሰው እየሞተ ነው ብሎ ቤት መቀመጥ አገሪቱን በምጣኔ ሀብት መቀመቅ ውስጥ መክተት ነው ብለው ያምናሉ፡፡ ሌሎች የግዛት ገዢዎች ግን ‹‹እርስዎ ሰውዬ ጤና የለዎትም ወይ›› እያሏቸው ነው፡፡

‹‹ቦልሴኔሮ በቫይረሱ የሚመጣውም ሞት ነው፤ ቤት ብንቀመጥም ኢኮኖሚው ተንኮታኩቶ በረሀብ እንሞታለን›› ሲሉ በር ዘግቶ መቀመጥን ክፉኛ ሲቃወሙ ቆይተዋል፡፡

በአንድ ወቅት ይህንኑ ጉዳይ በምሳሌ ሲያሰረዱ የመኪና አደጋ አለ ብለን ቤት እንደማንቀመጠው ቫይረስ አለ ብለን በር ዘግተን አንቀመጥብ ብለው ነበር፡፡

በዚህ ወጣ ያለ አመለካከታቸው ተቃዋሚዎች እንዳሏቸው ሁሉ ከፍተኛ ድጋፍ የሚሰጧቸውም አሉ፡፡

ፕሬዝዳንት የአፍ-አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ሳያደርጉ ከደጋፊዎቻቸው ጋር ፎቶ ሲነሱና ሲተቃቀፉም ለበርካታ ጊዜ በአደባባይ ታይተዋል፡፡