ሩሲያና ቱርክ የሚፎካከሩባት ሊቢያ

ሊቢያ በተፈጥሮ ጋዝና ነዳጅ ሃብት የበለፀገች ብትሆንም በተለያዩ አማፂያን መካከል ያለው ጦርነት ዜጎቿን እረፍት ነስቷቸዋል

የፎቶው ባለመብት, AFP

ሊቢያ አንድ ምዕራፍ አጠናቅቃ ወደ ሌላ እየተሸገገረች ይመስላል። ነገር ግን ቀጣዩ ምዕራፍም ለአገሪቱ መጻዒ እድል መልካም ነገር ይዞ ይመጣል ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር አይቻልም።

ሊቢያ የቀድሞ መሪዋ ሞአመድ ጋዳፊ ከስልጣን ከተወገዱና ከተገደሉ ወዲህ በእርስ በእርስ ጦርነትና በውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት ምስቅልቅሏ ወጥቷል።

ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ጄነራል ካሊፍ ኻፍታር፣ በምሥራቅ ሊቢያ ጠንካራውን ጦር የሚመሩት ግለሰብ፣ በአገሪቱ ምዕራባዊ ክፍል የምትገኘውንና ዋናዋ መዲናን ትሪፖሊን ለመቆጣጠር እልህ አስጨራሽ ጦርነት አካሂደዋል።

በተባበሩት መንግሥታት እውቅና ያለውን የትሪፖሊውን መንግሥት በመደገፍ ቱርክ ጦሯን ያዘመተች ሲሆን ጄነራል ኻፍታርም ቢሆኑ ደጋፊ አላጡም። ከሩሲያ የመጡ እና በሺህዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች ከጎናቸው ናቸው።

ነገር ግን ይህ የሁለት ወገኖች ድጋፍ ለሊቢያውያን ሁሌም የሚሹትን ሰላም አምጥቶላቸዋል ማለት አይደለም። እንደውም ሊቢያን በቅርበት የሚመለከቱ አሁንም ኪሳራውን የሚሸከሙት ሊቢያውያን ናቸው ሲሉ ይናገራሉ።

ሊቢያውያን አገራቸው በተፈጥሮ ጋዝና በነዳጅ ሃብት የበለፀገች ብትሆንም የሚያስቡትን ሰላም፣ ደህንንት፣ ትምህርት፣ የጤና አገልግሎት፣ እንዲሁም የተረጋጋ ህይወት ሊያመጣላቸው አልቻለም።

ቤታቸው በጦርነቱ ምክንያት ያልወደመባቸው ሊቢያውያን ራሳችን ከኮሮናቫይረስ ለመከላከል ብቻ ሳይሆን ከተባራሪ ጥይትም ለመከላከል በሚል ቤታቸውን ቆልፈው ተቀምጠዋል።

የእርስ በእርስ ጦርነቱ በርካታ ጤና ጣቢያዎችንና ሆስፒታሎችን አውድሟል።

በምዕራብ ሊቢያ ወደ 200 ሺህ ሊቢያውያን ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን የሂውመን ራይትስ ዎች ሪፖርት ያሳያል።

የፎቶው ባለመብት, AFP

የውጪ ኃይሎችና ሊቢያ

ጄነራል ኻፍታር ወደፊት የመጡት እአአ በ2014 ነበር። በወቅቱ ሊቢያ በርስ በርስ ጦርነት ትታመስ ነበር። የሊቢያ ሁለተኛዋ ትልቋ ከተማ ከሆነችው ቤንጋዚ አክራሪ እስላማዊ ቡድኖችን ካስወገዱ በኋላ ጄነራሉ ስማቸው ጎልቶ መጠራት ጀመረ።

ጄነራል ኻፍታር በሊቢያ ስማቸው በሚገባ የሚታወቅ የጦር መኮንን ናቸው። ጄነራሉ ጋዳፊ ስልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት አሜሪካ ተቀምጠው፣ የሲአይኤ መቀመጫ በሆነችው ከተማ፣ የጋዳፊን ውድቀት ሲያሴሩ ነበር።

የአሁኗ ሊቢያ ራሷን በሁለት መንግሥታት መካከል አግኝታዋለች።

ጄነራል ኻፍታር መቀመጫቸውን በአገሪቱ ምሥራቃዊ ክፍል ከምትገኘው ቤንጋዚ አድርገው አገሪቱን አንድ ለማድረግ ወደ ምዕራብ በመገስገስ ትሪፖሊ ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት ሰንዝረዋል። አላማቸው የዓለም አቀፍ መንግሥታት እውቅና ያለውን እና በፋዬዝ አል ሳራጅ የሚመራውን መንግሥት መጣል ነው።

የፎቶው ባለመብት, AFP

ጠቅላይ ሚኒስትር ፋዬዝ አል ሳራጅን የሚደግፉት መንግሥታት ቱርክ፣ ኳታርና ጣልያን ሲሆኑ ጄነራል ካሊፍ ኻፍታርን የሚደግፉት ደግሞ የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ፣ ዮርዳኖስ፣ ግብጽ፣ ሩሲያ፣ ፈረንሳይ ናቸው።

በርስ በርስ ጦርነት ወቅት የውጭ አገራት እጃቸውን እንደሚያስገቡ እሙን ነው። ሊቢያ ደግሞ የየትኛውም አገር አይን ሊያርፍባት የምትችል አገር ናት።

በአፍሪካ ትልቁ የሆነው የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት የሚገኝበት በመሆኗ የአገራት ልብ መቋመጡ አይቀርም። ከሰባት ሚሊዮን በታች የሕዝብ ብዛት ያላት ሊቢያ ከአወሮፓ በቅርብ ርቀት ላይ መገኘቷ ሌላው የበርካቶችን ልብ የሚያማልል ነው።

ሊቢያ በቀጥታ ነዳጇን በሜዲትራያኒያን ላይ አቋርጣ ለአውሮፓ ገበያ ስታቀርብ በተቃራኒው የባሕረ ሰላጤው አገራት ደግሞ እጅግ አደገኛ በሆነ የባህር መስመር ላይ ምርታቸውን በማጓጓዝ ይሸጣሉ።

ጄነራል ኻፍታር ሁነኛ ወዳጆች ሩሲያ፣ የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ እና ግብጽ ናቸው።

ለትሪፖሊው መንግሥት ደግሞ ቱርክ ጠንካራ አጋር ናት።

አሜሪካ በዶናልድ ትራምፕ የሥልጣን ዘመን ጠቅላይ ሚኒስትር ሳራጅንም ሆነ ጄነራል ኻፍታርን የሚደግፉ ምልክቶች ልካለች። ነገር ግን ይህ ምልክት የእስላማዊ አክራሪ አማፂያንን በቦንብ ከመደብደብ ያለፈ ድጋፍ አላሳየም።

አሁን ትልቁ ስጋት የሩሲያው ፕሬዝዳንት ፑቲን በሊቢያ እግራቸው ስር ሰዶ ልክ እንደ ሶሪያ ያለ ሁኔታ ይፈጠራል የሚል ነው።

በሊቢያ አሁን እየተካሄደ ያለው ጦርነት ከሶሪያ ጋር የሚያመሳስለው ነገር እየተፈጠረ ነው። የእርስ በእርሱ ጦርነት መደምደሚያ ያለው በውጪ ኃይሎች እጅ ይመስላል።

በሊቢያ በእጅ አዙር የሚደረገው ጦርነት የሶሪያ ቅጣይ ነው የሚሉ ወገኖች እንደማስረጃነት የሚያቀርቡት ሁለቱም ወገኖች ወታደሮቻቸውን ሶሪያ በመላክ ልምድ ለማግኘት መሞከራቸውን በማንሳት ነው።

የቱርክ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶጋንና የሩሲያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን በሶሪያ የተገበሩትን በሊቢያ አስልተው መምጣታቸው ግልጽ ነው።

በሊቢያ የሚዋጉት ሩሲያውያን ዋግነር ግሩፕ ከተሰኘ ተቋም የተገኙ ናቸው፤ ይህ ተቋም ደግሞ ለፕሬዝዳንት ፑቲን ቅርብ በሆነ ሰው የሚመራ መሆኑ ይታወቃል። የዋግነር ተዋጊዎች በሶሪያ ጦርነት ላይ ተሳትፈዋል።

ሩሲያውያን የጦር አውሮፕላኖቻቸውን ወደ ሊቢያ ስታሰማራ ቱርክ በበኩሏ ሰው አልባ የጦር አውሮፕላን አዝምታለች።