ደቡብ አፍሪካዊያን ቢራ ጠምቷቸዋል

ቢራ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ደቡብ አፍሪካዊያን ከዛሬ ጀምሮ መጠጥ መግዛት ይፈቀድላቸዋል፡፡ በዚያች አገር ላለፉት ሁለት ወራት ክልከላ ተጥሎባቸው ከነበሩ ነገሮች አንዱ መጠጥ መግዛት ነበር፡፡

ደቡብ አፍሪካ ወረርሽኙን ለመግታት በዓለም ላይ ጥብቅ የክልከላ ደንቦችን ካወጡ አገሮች ተርታ ተመድባ ቆይታለች፡፡

ከዛሬ ጀምሮ በሚላላው በዚህ ጥብቅ መመሪያ ዜጎች መጠጥ መግዛት ቢችሉም መጠጡን መጠጣት የሚችሉት ግን ቤታቸው ወስደው ነው፡፡

ከኮቪድ ወረርሽኝ ጋር የመጠጥ ክልከላ ማድረግ ያስፈለገበተ ምክንያት በዚያች አገር ሰዎች ሲሰክሩ ጸብ አይጠፋምና ተጎጂዎች የሆስፒታል አልጋ ያጣብባሉ ከሚል ስጋት ሲሆን ሌላኛው ምክንያት ደግሞ ዜጎች ከቤት እንዳይወጡ ተደርጎ መጠጥ ግዢ ቢፈቀድ በተለይም በሴቶች ላይ የሚደርሰው የቤት ውስጥ ጥቃት ይበራከታል የሚል ስጋት ስለነበረ ነው፡፡

በደቡብ አፍሪካ ከመጠጥ ስካር ጋር የተያያዙ የቡድን ጸቦች በስፋት የሚመዘገቡባት አገር ናት፡፡

በደቡብ አፍሪካ በሳምንቱ መጨረሻዎች ፖሊስ ጣቢያዎችም ሆኑ በሆስፒታሎች ከመጠጥ ኃይል ጋር ተያይዘው የሚፈጠሩ ወንጀሎችና ጉዳቶች የትየሌሌ ናቸው፡፡

ሰሞኑን ከፖሊስም ሆነ ከሀኪሞች የተገኙ መረጃዎች እንደመሰከሩት የመጠጥ ሽያዥ እቀባ በተጣለባቸው ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥ የወንጀል፣ የጸብና የአካላዊ ጉዳት መጠኖች በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሰው ታይተዋል፡፡

በዚህ ለሁለት ወራት በጸናው የመጠጥ እቀባ መመርያ ወንጀልንና ጥቃትን መቀነስ ቢቻልም ቢራ ጠማቂዎች፣ ውስኪ ቸርቻሪዎችና ዋይን ፋብሪካዎች መንግሥት ንግዳችን ላይ ጉዳት አድርሶብናል ሲሉ ወቅሰዋል፡፡

መንግሥት በበኩሉ እኔም እኮ ከናንተ ሽያጭ አገኝ የነበረው የግብር ገቢ ቀርቶብኛል ሲል ምላሽ ሰጥቷል፡፡

በደቡብ አፍሪካ 31ሺ ዜጎች በቫይረሱ ተይዘዋል፡፡