አዶልፍ ሂትለር የተወለደበት ቤት ፖሊስ ጣቢያ ሊሆን ነው

የቪየና አስተዳደር የሂትለርን የተወለደበት ቤት ወደ ፖሊስ ጣብያ ለመቀየር አዲስ ንድፍ አስተዋውቋል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በዓለም የጭካኔ ቁንጮ ተደርጎ የሚታየው አዶልፍ ሂትለር የተወለደው በኦስትሪያዋ የድንበት ከተማ ብራውና ነበር፡፡ የብራውና ነዋሪዎች ስማቸው ከዓለም ጨካኙ ሰው ጋር መነሳቱ ይከነክናቸዋል፡፡

መንግሥትም ቢሆን የሂትለር ቤት ለአክራሪ አፍቃሪዎቹ የጉብኝት መዳረሻ መሆኑ ሲያሳስበው ቆይቷል፡፡

ይህም ሆኑ ሂትለር የተወለደበት ቤት እስከዛሬም ድረስ ባለበት አለ፡፡ የእርሱ የትወልድ ስፍራ ስለመሆኑ የሚያመላክት ግን ምንም ዓይነት ቅርስ የለም፡፡ የርሱ ስም ያለበት ጽሑፍም አይታይም፡፡ ደጁ ላይ ብቻ ‹‹ ፋሺዝም መቼም እንዳይደገም›› የሚል ጽሑፍ ድንጋይ ላይ ታትሟል፡፡

ይህንን መኖርያ ቤት መንግሥት የአስገዳጅ ግዥ በመፈጸም የራሱ ካደረገው ቆይቷል፡፡

ባለፈው ኅዳር ነበር መንግሥት አወዛጋቢ ውሳኔ ላይ የደረሰው፡፡ ቤቱን ወደ ፖሊስ ጣብያነት መቀየር፡፡

አንድ የኦስትሪያ የኪነ ሕንጻ አሰናጅ ቤቱን ወደ ፖሊስ ጣቢያነት የሚቀይረውን ሀሳብ እየነደፈ ይገኛል፡፡

‹‹ለጨካኙ የናዚ ጌታ የትውልድ ቤት አዲስ ምዕራፍ ይከፈትለታል›› ብለዋል የኦስትሪያ የአገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትር ካርል ናሃመር፡፡

ንድፉን ያሸነፈው ማንቴ ማንቴ የሚባለው ድርጅት ከ12 እጩዎች መሀል የተመረጠ ሲሆን በሦስት ዓመታት የማሻሻያ ግንባታውን አጠናቆ በፈረንጆች 2023 መኖርያ ቤቱን ፖሊስ ጣቢያ አድርጎ ለማስረከብ የ5 ሚሊዮን 6 መቶ ሺህ ዶላር ስምምነት ፈጽሟል፡፡

የሂትለር የትውልድ ቤት ወደ ፖሊስ ጣቢያነት ሲቀየር ስለርሱ ታሪክ የሚያወሳ ምንም ዓይነት ቅሪት እንደማይኖር ተነግሯል፡፡

‹‹ፋሸዝም መቼም አይደገም!›› የሚለው መፈክርም ወደ ኦስትሪያ ዋና ከተማ ቪየና ሙዝየም ይወሰዳል፡፡

አንድ የከተማዋ ነዋሪና የታሪክ ባለሞያ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ይህ ‹‹ፋሺዝም መቼም አይደገም›› የሚለው ድንጋይ ጽሑፍ በከተማዋ መቆየት ይኖርበታል ብለዋል፡፡

በዚህ የሂትለር የትውልድ መኖርያ ውስጥ አምባገነኑ ሰው የተወለደው በ1889 ሲሆን ቤተሰቦቹ ግን ከጥቂት ሳምንታት በኃላ አፓርትመንቱን ለቅቀው ወደ ሌላ ሰፈር ሄደዋል፡፡ ሂትለር 3 ዓመት ሲሞላው ደግሞ ጭራሽ ከተማዋን ጥለው ሄደዋል፡፡

ዛሬም ድረስ የናዚ ደጋፊዎች ወደ ሂትለር የትውልድ ቤት እንደሚጓዙ የጠቀሱት የመንግሥት ባለሥልጣናት ይህንን ለማስቀረት አንዱ መንገድ የቤቱን አገልግሎት መቀየር እንደሆነ ተረድተዋል፡፡

ኦስትሪያ በናዚ ጀርመን እንደ አውሮፓዊያን በ1938 የተጠቃለለች ሲሆን የናዚ ቀዳሚ ተጠቂ አገር አድረጋ ራሰዋን ትመለከታለች፡፡

ነገር ግን በዚያን ጊዜ አብዛኛው ሕዝብም ሆነ አስተዳደሩ ወደ ጀርመን መቀላቀሉን ወዶት እንደነበር ይነገራል፡፡

ቤቱን ከ1970ዎቹ ጀምሮ መንግሥት ለግለሰቦች ያከራየው ነበር፡፡ በኋላም የአካል ጉዳቶች የእንክብካቤ ማዕከል ተደርጎ ቆይቷል፡፡

ቤቱ በቅርስነት መቆየት እንጂ መነካት የለበትም በሚሉና የመንግሥትን እርምጃ በሚደግፉ መካከል አሁንም ድረስ የጦፈ ክርክር እየተደረገ ይገኛል፡፡

የድንበር ከተማዋ ብራውና ግን አሁንም ቢሆን ከሂትለር ጋር ተያይዛ መታሰቧ የሚቀር አልሆነም፡፡