"በጣም እርግጠኛ ሆነን ያወጣነው ሪፖርት ነው" አምነስቲ ኢንተርናሽናል

የአምንስቲ አርማ

የፎቶው ባለመብት, Amnesty

አምንስቲ ኢንተርናሸናል ከቀናት በፊት ባወጣው ሪፖርት በኢትዮጵያ የመንግሥት ኃይሎች ፈጽመውታል ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በዝርዝር አስቀምጧል።

ይህ የድርጅቱ ሪፖርት የመንግሥት፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዲሁም የተለያዩ ግለሰቦች መነጋገሪያ ሆኗል። እነዚህ ወገኖችም በሪፖርቱ ላይ የተለያዩ ትችቶችን ሲሰነዝሩ ቆይተዋል። የተነሱ ቅሬታዎችን በተመለከተ የአምንስቲ ኢንተርናሸናል የአፍሪካ ቀንድ የሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ አጥኚ የሆኑት አቶ ፍሰሃ ተክሌ ለቢቢሲ ምላሻቸውን ሰጥተዋል።

የኦሮሚያ ክልል ቅሬታ

የኦሮሚያ ክልል ኮሚኒኬሽን ቢሮ አምነስቲ ያወጣው ሪፖርት ተቀባይነት የሌለው ነው ብሏል። ክልሉ ሪፖርቱን የማይቀበልበት አንዱ ምክንያት፤ በአራቱ ወለጋ ዞኖች እንዲሁም በሁለቱ የጉጂ ዞኖች ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ግድያዎችን እየፈጸሙ፤ በሪፖርቱ ሳይካተቱ ለምን ቀሩ በሚል ነው።

አቶ ፍሰሃ ለዚህ ክስ መልስ ሲሰጡ ግለሰቦችም ሆኑ የታጠቁ ኃይሎች የሚፈጽሙት በወንጀል የሚታይ ነው በማለት፤ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የሚፈጸሙት ግን በመንግሥት ኃይሎች ነው ይላሉ።

ሰለ ሰብዓዊ መብት ጥስት ስናወራ ስለ መንግሥት እያወራን ነው ያሉት አቶ ፍሰሃ የሰብዓዊ መብትን የማስጠበቅ ኃላፊነት የሚጫነው የመንግሥት አካላት ላይ መሆኑን አጽንኦት ሰትተው ኣስረዳሉ።

"ግለሰቦች ወይም የታጠቀ ኃይል የሚፈጽመውን ወንጀል መንግሥት የመከላከል ኃላፊነት አለበት። አሁን ጥያቄው መንግሥት ይህን አድርጓል ወይስ አላደረገም ነው። ይህ የሚወስደን ደግሞ መንግሥት አላደረገም ወደሚለው ነው። ይህ ደግሞ ራሳቸውን መልሶ ተጠያቂ ነው የሚያደርገው። የታጠቁ ቡድኖች ወንጀል ሲፈጽሙ ሕግ ፊት የማቅረቡ ግዴታ የመንግሥት ነው። . . .'86 ሰዎች ግድያ አልተጠቀሰም ይላሉ' ይህ እኮ የመንግሥት ውድቀት ነው የሚያሳየው" ብለዋል።

እአአ 2014 አምነስቲ ኢንተርናሽናል 'በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ- የአገሪቱ መንግሥት እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰላም አስከባሪ ኃይል ንጹሃን ዜጎችን ከታጣቂዎች ጥቃት መጠበቅ አለባቸው' የሚል መግለጫ አውጥቶ ነበር። በኡጋንዳም በአምነስቲ ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ መግለጫ ወጥቷል። ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ የታጠቁ ኃይሎች በአራቱ የወለጋ ዞኖች እና በጉጂ የሚያደርሱት ጥቃት ለምን ሪፖርት አልተደረገም ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄ አቶ ፍሰሃ

"እነዚህ መግለጫዎች የሚሉት 'ታጥቀው በሚንቀሳቀሱ ኃይሎች የሚፈጸሙ ጉዳቶችን መንግሥት የመከላከል ኃላፊነት አለበት' ነው። ከላይ በተጠቀሱ ሪፖርቶች ላይ ታጣቂዎች የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጽመዋል አላልንም። መንግሥት ጥቃቶችን መከላከል ባለመቻሉ ኃላፊነቱን እየተወጣ አይደለም ነው ያልነው። በኢትዮጵያ ታጣቂዎች ይህን ያክል ሰው ገደሉ ሲባል፤ መንግሥት መከላከል አልቻለም የሚለው ነው የሚመጣው።"

የአማራ ክልል ቅሬታ

የአማራ ክልል ኮሙኑኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ግዛቸው ሙሉነህ "ሪፖርቱ ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት የሌለው ነው፤ እውቅና አንሰጠውም" ብለዋል። የክልሉ ቃል አቀባይ ሪፖርቱ ተቀባይነት የለውም ያሉበትን ምክያት ሲያስረዱ፤ የቅማንት ብሄረሰብ አስተዳደር የራስ አስተዳዳር የመመስረት ፍላጎት ጋር ተያይዞ ግጭት ተከስቷል። በግጭቱም በአማራ እና በቅማንት ላይ ጉዳት ደርሷል። ይሁን እንጂ አምነስቲ በሁለቱም ህዝቦች የደረሰውን ጉዳት በእኩል ዓይን አላየም፣ የመንግሥት ኃይል ሰላም ለማስፈን የወሰደው እርምጃ የብሄር ጥቃት አድርጎ አቅርቧል ብለዋል።

"የእርስ በእርስ ግጭት በራሱ የሰብዓዊ መብት ጥሰት አይደለም" በማለት የሚጀምሩት አቶ ፍሰሃ፤ በግጭቱ ወቅት መንግሥት የወሰደው እርምጃ ምንድነው የሚለውን እንደተመለከቱ ይናገራሉ። "ባገኘነው መረጃ መሠረት የጸጥታ አካላት በዛ የእርስ በእርስ ግጭት ውስጥ ግልጽ በሆነ መልኩ ለአንድ ወገን ወግነው ተሳትፈዋል።"

ከዚህ በተጨማሪ የመንግሥት ጸጥታ አስከባሪዎች ማድረግ ሲገባቸው ያላደረጉት አለ ይላሉ አቶ ፍሰሃ። "ለምሳሌ የአካባቢው ሠራዊት ጥሪ ሲደረግለት አልመጣም። ግጭት ያለማስቆም ሁኔታ ነበረ" ይላሉ።

የአማራ ክልል ድርጅቱ ባወጣው ሪፖርት ላይ ያቀረበው ሌላኛው ቅሬታ፤ ከሰላም እና ደህንነት ቢሮ መረጃ ቢሰጣቸው መረጃው በሪፖርቱ ላይ በአግባቡ አልተካተተም የሚለው ነው። "ጥናት ሲካሄድ ብዙ የሚነገርን ነገር ይኖራል። ለጥናቱ ይጠቅማል፤ አይጠቅምም የሚለው መለየት አለበት። ከኃላፊው ጋር በተቀመጥንበት ጊዜ ከተነገሩን ለጥናቱ የሚሆኑን ነገሮችን ነው ያስገባነው" ብለዋል አቶ ፍሰሃ።

የተለያዩ ግለሰቦች እና ቡድኖች ካነሷቸው ቅሬታዎች መካከል አማራ ክልል ተከትስቶ በነበረው ግጭት የህውሃት ተሳትፎ በሪፖርቱ ሳይጠቀስ አልፏል የሚል ይገኝበታል። የአማራ ክልል ከዚህ ቀደም ጎንደር አከባቢ ግጭት በተከሰተ ወቅት ህውሃት ለሚሊሻዎች ድጋፍ ያደርጋል ሲል መውቀሱንም ይጠቅሳሉ።

አቶ ፍሰሃ ግን የቅማንት ሚሊሻዎች ከሌላ አካል ድጋፍ ስለማግኘታቸው የሚያሳይ መረጃ አላገኘንም ይላሉ። አክለውም በትክከል የህውሃትም ሆነ የሌላ አካል እጅ ስለመኖሩ የሚያሳይ ማረጋገጫ ማግኘት አልቻልንም ብለዋል።

'የጥናቱ ተሳታፊዎች ምላሽ ሙሉ ምልከታን የሚሰጡ አይደሉም'

ሌላ በአምነስቲ ሪፖርት ላይ የቀረበው ቅሬታ በጥናቱ ተሳታፊ የሆኑ ሰዎች ቃለ መጠይቅ ሲደረግላቸው፤ ጥናት አድራጊዎች ተሳታፊዎቹን በሚገባ አልጠየቋቸውም የሚል ነው። እንደ ምሳሌ አንድ የጥናቱ ተሳታፊ 'የሸኔ አባል ነህ ተብዬ ጉዳት ደረሰብኝ ቢል' በሪፖርቱ ላይ ጥናት አድራጊው 'የሸኔ አባል ነህ?' ብሎ ሲጠይቀው አይታይም። ይህም የሪፖርቱ አንባቢያን ሙሉ ምልከታ እንዳያገኙ አድርጓል የሚል ነው።

አቶ ፍሰሃ ግን በሪፖርቱ ላይ የተጠቀሱት ሰዎች ንግግር የተወሰደው ''quotations'' እንጂ ሙሉ ቃለ መጠይቁ አይደለም ካሉ በኋላ፣ "ዝርዝር ነገር ነው የምንጠይቀው፤ ተከታታይ ጥያቄዎችን በመጠየቅ ለጥናቱ ግብዓት ይሆናሉ የምንላቸውን ብቻ መርጠን ነው የምናወጣው" በማለት አምነስቲ መረጃ የሚሰበስብበት፣ የሚያደራጅበት እና የሚተነትንበት የራሱ የሆነ የተራቀቀ ስርዓት እንዳለው ይናገራሉ።

አምነስቲ ይፋ ባደረገው ሪፖርት ላይ በተለያዩ ስፍራዎች ከሚገኙ 80 ሰዎች የጥናቱ ግብዓት መሆናቸውን በሪፖርቱ ገልጿል። የጥናቱ ተሳታፊዎች የሚሰጡት መረጃ ትክክለኛነት በምን ታጣራላችሁ? የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ፍሰሃ፤ በሪፖርቱ ላይ 80 ሰዎች ይጠቀሱ እንጂ ከዛ በላይ ሰዎችን ነው ያናገርነው ብለዋል።

በተጨማሪም ለጥናቱ አግባብ የሆኑ መረጃዎቸን የሰጡን ብቻ ነው ያካተትነው በማለት በሪፖርቱ በብዛት የተካተቱት ጉዳት የደረሰባቸው መሆናቸውን ይገልጻሉ። ይህንን ጥናት ካሄዱ ባለሙያዎች አንድን ከስተት ከሶስት እና ከአራት ሰዎች እንደሚሰሙ፣ አንዱ የተናገረውን ከሌላኛው ጋር መተዓጣም አለመጣጣሙን እንደሚመዝኑና እውነታውን ለይተው እንደሚያወጡ አስረድተዋል።

ሪፖርቱ ስህተት ሆኖ ቢገኝ ማስተካከያ ታወጣላችሁ?

ጠቅላይ አቃቤ ሕጓ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ትናንት ጠዋት በፌስቡክ ገጻቸው ላይ፤ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያወጣውን መግለጫ መመልከታቸውን ገልፀዋል። ጠቅላይ አቃቤ ሕጓ ጨምረውም፤ "የማጣራት ስራም ጀምረናል። ሪፖርቱ እውነት በሆነበት ልክ፣ መወሰድ ያለበቸውን እርምጃዎች እንወስዳለን። ሀሰት በሆነበት ወይም በተጋነነበት አኳያ ከአምነስቲ ኢንተርናሽናል ጋራ በመወያየት ሪፖርቱ እንዲስተካከል እንጥራለን" ብለዋል።

አምነስቲ ያወጣው ሪፖርት መንግሥት በሚያቀርበው ማስረጃዎች ስህተት ሆኖ ቢገኝ ማስተካከያ ታደርጋላችሁ ወይ? የሚለው ለአቶ ፍሰሃ ያቀረበነው ጥያቄ ነው።

"በጣም አርግጠኛ ሆነን ያወጣነው ሪፖርት ነው። ግን መንግሥት የሚያደርገው ማጣራት በገለልተኛ እና አመቺ በሆነ መልኩ የሚካሄድ ከሆነ ለመቀበል ዝግጁ ነን። ዋነኛ ዓላማችንም መንግሥት የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስድ ማድረግ ነው"

አቶ ፍሰሃ አክለውም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ወደስልጣን ከመጡ ወዲህ በሚወጡ ሪፖርቶች ላይ መንግሥት የተሻለ አስተያየት ይኖረዋል የሚል እምነት እንደነበራቸው ይናገራሉ። ከመንግሥት የተሰጡ ምላሾች ግን የቀድሞውን አስተዳደር የሚመስሉ መሆናቸውን በመጥቀስ "ለሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ያላቸው አመለካከት መቀየር አለበት። መሬት ላይ ያለውን ነገር ለመቀየር የሚረዳው ከድርጅቱ ጋር በቀና መንፈስ መነጋገር" መሆኑን ይገልፃሉ።

የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ሪፖርትን በተመለከተ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሰጠው ምላሽ ሪፖርት ሚዛኑን ያልጠበቀና በአገሪቱ ያለውን ሁኔታ ከግንዛቤ ያላስገባ ነው በማለት "ሪፖርቱ ወደ አንድ ወገን ያጋደለ ቁንጽል የጸጥታ ሁኔታ ትንተና ነው" ሲል ተችቶታል።

ጨምሮም የኢትዮጵያ መንግሥት የኮሮናቫይረስ መስፋፋትን በመግታት የዜጎችን ህይወት ለማመታደግ ጥረት እያደረገ ባለበት ወቅት ሪፖርቱ "ጊዜያዊ የፕሮፓጋንዳ ጥቅም ለማግኘት ሲባል ወረርሽኙ የደቀነውን ከባድ አደጋና ተጽዕኖ ችላ ያለ ከመርህ የራቀና ግዴለሽነት የታየበት ነው" ሲል ወቅሷል።

ነገር ግን የኢትዮጵያ መንግሥት ተከሰቱ ስለተባሉት የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ማጣራት እንደሚያደርግ ጠቅላይ አቃቤ ሕጓ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ መግለጻቸው ተዘግቧል።