የስዊድኑን ጠቅላይ ሚኒስትር የገደላቸው ማን እንደነበር ይፋ ሆነ

ኦሉፍ ፓልማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ይህ በዓለም ላይ ምስጢር ሆነው ከቆዩ እጅግ አስገራሚ ግድያዎች አንዱ የሆነው የሲዊዲኑ ጠቅላይ ሚንስትር የግድያ ወንጀል አንዱ ነው፡፡

በአመዛኙ በስዊድናዊያን ዘንድ ተወዳጅና እጅግ አወዛጋቢ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ኦሉፍ ፓልማ የተገደሉት እንደ አውሮጳዊያኑ በ1986 ነበር፡፡

ከ34 ዓመት በኋላ ፖሊስ ገዳያቸው ማን እንደሆነ አውቂያለሁ ብሏል፤ ዛሬ።

ነፍሰ ገዳዩ ሰው ስቲግ ኢንግስትሮም የሚባል ሰው ሲሆን አሁን በሕይወት የለም፡፡ ራሱን በገዛ እጁ ያጠፋውም በ2000 ዓ. ም ነበር፡፡

ይህ ሰው በቅጽል ስሙ "ስካንዲያ ማን" ይባል የነበረው ሲሆን በሕይወት ሳለ ፖሊስ ጠርጥሮ አስሮት ነበር፡፡

ዋና አቃቢ ሕግ ክሪስተር ፒተርሰን ዛሬ ከደቂቃዎች በፊት ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ስዊድንን ለ34 ዓመታት ሰቅዞ የያዛት ጉዳይ እነሆ ፍጻሜውን አግኝቷል፡፡

የሚገርመው ገዳዩ በዚያ ዘመን ሰውየው ሲገደሉ አይቻለሁ ብሎ ምስክርነት ሰጥቶ ነበር።

የያኔው ጠቅላይ ሚኒስትር ፓልማ የተገደሉት ከባለቤታቸው ጋር በሕዝብ ሲኒማ ቤት ገብተው ፊልም አይተው ሲወጡ በጎዳና ላይ ነበር፡፡

ፓልማ አጀብና የፖሊስ ጥበቃ የማይፈልጉና እንደ ተራ ዜጋ በጎዳና ይንቀሳቀሱ የነበሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ነበሩ፡፡

ሰውየውን የገደላቸው ጥቁር ኮት ያደረገ የስካንዲኒቪያን መልክና ገጽታ የነበረው ረዥም ሰውዬ እንደነበር ግድያውን አጠናቆ ሲሄድ የተመለከቱት ቢያንስ 20 ሰዎች መስክረው ነበር፡፡

በ34 ዓመታት ውስጥ ከ10ሺህ ሰዎች በላይ ከግድያው ጋር በተያያዘ በፖሊስ ሲመረመሩ ነበር፡፡

ገዳዩ ማን ነበር?

ስቲግ ኢንግስትሮም ወይም በቅጽል ስሙ ስካንዲያ ተብሎ የሚጠራው ግለሰብ አዲስ ተጠርጣሪ አይደለም። ይህ ቅጽል ስም የተሰጠው ደግሞ ይሰራበት የነበረው መሥሪያ ቤት ስሙ ስካንዲያ ስለሚባል ነበር፡፡

ስካንዲያ ኢንሹራን ኩባንያ የሚገኘው ደግሞ ጠ/ሚኒስትሩ ከተገደሉበት ጎዳና አቅራቢያ ነው፡፡

ያቺ ጠ/ሚኒስትሩ የተገደሉባት አርብ ምሽት ላይ እሱ በዚህ መሥሪያ ቤት ውስጥ አምሽቶ ይሰራ እንደነበር ፖሊስ ደርሶበታል፡፡

ይህ ሰው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲገደሉ ባይኔ በብረቱ አይቻለሁ ብለው በገዛ ፈቃዳቸው ለፖሊስ ምስክርነት ከሰጡ 20 ሰዎች መካከል አንዱ ነው፡፡

በመጨረሻም ራሱን በገዛ እጁ ያጠፋው በ2000 ዓ. ም በፈረንጆች ነበር፡፡

ይህ ሰው ጠቅላይ ሚኒስትሩን ሳይገድላቸው አልቀረም ብሎ መጀመርያ የጠረጠረው ቶማስ ፒተርሰን የተባለ ጋዜጠኛ ነበር፡፡

በኋላም ፖሊስ ምርመራ ጀምሮበት ነበር፡፡ ምርመራው ተጠናክሮ የቀጠለው ግን ሰውየው ራሱን ካጠፋ ከ18 ዓመታት በኋላ ነው፡፡

ይህ ሰው ጠቅላይ ሚኒስትሩን የገደላቸው ግራ ዘመም አመለካከታቸውን አይወድላቸው ስለነበረ ነው ተብሏል፡፡

ጋዜጠኛው ይህን ሰው ሊጠረጥር ያስቻለው ምስክር በሰጠበት ወቅት ወደ ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር የቀረብኩት ነፍሳቸው ካልወጣች ልረዳቸው ፈልጌ ነው ሲል መዋሸቱን ተከትሎ ነበር፡፡

ፖሊስ ይህን ተከትሎ ባደረገው ምርመራ ደግሞ ሰውየው የጦር መሣሪያ አተኳኮስ ልምምድ ማድረጉን ደርሶበት ነበር፡፡

ከገዳዩ ጋር በትዳር የኖረችውና በኋላም ፍቺ የጠየቀችው ሴት በ2018 ፖሊስ ጠርቶ እንደመረመራት ለስዊድን ጋዜጣ ተናግራ ነበር፡፡

ገዳዩ እሱ ይሆናል ብለሽ ትገምቻለሽ ወይ ተብላ ተጠይቃ የነበረችው የቀድሞው ባለቤቱ፣ እረ እሱ በጣም 'ቦቅቧቃ ነው'፤ ዝምብ እንኳ የመግደል ድፍረት ያለው ሰው አይደለም" ስትል ተናግራ ነበር፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ፓልማ ግድያ ዙርያ በመቶዎች የሚቆጠሩ ፊልሞች፣ መጻሕፍትና የመድረክ ሥራዎች የቀረቡ ሲሆን በስዊድን አገር ለሦሰት ዐሥርታት እጅግ አነጋጋሪ ጉዳይ ሆኖ ዘልቋል፡፡

የቀድመው ጠቅላይ ሚኒስትር ኦሉፍ ፓልማን ያስገደሏቸው የደቡብ አፍሪካ አፓርታይድ ሥርዓት ባለሥልጣናት ናቸው የሚል ጠንካራ እምነት ነበር፡፡ ምክንያቱም ፓልማ የማንዴላና የኤኤንሲ ደጋፊ ነበሩና ነው።

በኚህ ጠቅላይ ሚኒስትር ዙርያ ዘለግ ያለ ንባብ ይህንን ማስፈንጠሪያ ነክተው ያገኛሉ፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለቤት ወ/ሮ ሊዝቤት ፓልማ የሞቱት ከ2 ዓመት በፊት የባለቤታቸውን ገዳይ ሳያውቁ ነው፡፡ ባለቤታቸው በተገደሉበት ምሽት ግን አብረዋቸው ነበሩ፡፡

ይህ ለ34 ዓመታት ሚስጥር ሆኖ ስለቆየው ታሪክ ተጨማሪ ለማንበብ፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ማን እንደገደላቸው ከ34 ዓመታት በኋላ ይፋ ሊሆን ነው