"ከሴቶችና ህፃናት ጥቃት ጋር በተያያዘ 94 መዝገቦች በፖሊስ ምርመራ ላይ ናቸው" ጠቅላይ አቃቤ ህግ

ደብተር የያዘች ህፃን

የፎቶው ባለመብት, NurPhoto

በባለፉት ወራት ከመቶ በላይ ህፃናት መደፈራቸው ጋር በተያያዘ 94 መዝገቦች በፖሊስ ምርመራ ላይ መሆናቸውን እና 23 ክሶች መመስረታቸውን ጠቅላይ አቃቤ ህግ አዳነች አቤቤ በፌስቡክ ገፃቸው አስታውቀዋል።

ከዚሁም ጋር ተያይዞ በአራት መዝገቦች ላይ የፍርድ ውሳኔ መሰጠቱንም ጠቁመዋል።

የኮሮናቫይረስ ስርጭት መዛመትን ለመግታት ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸውን ተከትሎ የተደፈሩ ህፃናት ቁጥር ማሻቀቡንና ከመቶ በላይ ህፃናት ሴቶችና ወንዶች መደፈራቸውን የአዲስ አበባ ሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ከሰሞኑ መግለፁ የሚታወስ ነው።

በተቃራኒው የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ከጠቅላይ አቃቤ ህግ የሚፃረር መረጃን ሰጥተዋል።

ህፃናቱ ከተፈፀመባቸው ወንጀል ጋር ተያይዞ ክስ አለመጀመሩን የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ ባለፈው ሳምንት አርብ በትዊተር ገፃቸው አስፍረዋል።

"ከአዲስ አበባ ህፃናትና ሴቶች ቢሮ ሮ በህፃናት ላይ የሚደርስ ጥቃትን በተመለከተ ለህዝብ የተገለፀውን መረጃ መሠረት በማድረግ ባለፉት 2 ወራት የተከፈቱ የክስ መዝገቦችን ለመከታተል ባደረግነው የመረጃ ዳሰሳ ባለፉት 2 ወራት የተከፈቱ መዝገቦች እንደሌሉ አውቀናል" በማለት ፕሬዚዳንቷ መዓዛ አሸናፊ በትዊተር ገልፀዋል።

በሃገሪቷም እየተከሰተ ያለውን የሴቶች እና የህፃናት ጥቃትን በተመለከተ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ግምገማ ማድረጋቸውን ያስታወቁት ጠቅላይ አቃቤ ህጓ ከኮቪድ 19 መከላከል ጋር ተያይዞጥቃቶች መጨመራቸውን አስረድተዋል።

ወ/ሮ አዳነች በፌስቡክ ገፃቸው እንዳሳወቁት በዚህ ግምገማ ላይ የተሳተፉት የሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር፣ ጠቅላይ እና የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት፣ አዲስ አበባ ፖሊስ አዲስ አበባ ሴቶች ህፃናትና ወጣቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ግምገማቸውም እንደሚያሳየው ወረርሽኙን ተከትሎ ጥቃቶች መጨመራቸውን፣ ወደ ፍትህ አካላት መምጣት መቀነሱን እና በተጨማሪም መረጃ አያያዞች ላይ ባለው ክፍተት ላይ ከባለድርሻ አካላቱ ጋር መነጋገራቸውን አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ ባለፉት ወራት ከመቶ በላይ ከ15 አመት በታች የሆኑ ህፃናት በወላጅ አባቶታቻቸውና የቤተሰብ አባላት ጭምር መደፈራቸውም ከፍተኛ ቁጣና ውግዘት ያስከተለ ሲሆን ቤቶችም ቢሆኑ ምን ያህል ለህፃናት ደህንነታቸው ያልተጠበቁ የመሆናቸውንም እውነታ አጋልጧል።

የትምህርት ቤቶች መዘጋትና ልጆች ቤት መዋላቸውንም ተከትሎ የሚደፈሩ ህፃናት ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩንም የአዲስ አበባ ሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ የተለያዩ ሆስፒታሎችን ዋቢ በማድረግ የጠቀሰ ሲሆን፤ ጥቃት የደረሰባቸው ህፃናት በተለያዩ የጤና ማእከላት ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑንም ተገልጿል።

ከዚህም በተጨማሪ አምሳ ሴቶች የቤት ውስጥ ጥቃት እንደደረሰባቸውም ሪፖርት አድርገዋል።

በፌደራል ፍ/ቤቶች የህፃናትና ሴቶች ጉዳይን የሚያዩ ችሎቶች በኮቪድ19 ምክንያት ያልተዘጉ መሆናቸውንም ወይዘሮ መዓዛ እንዲሁም ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ገልፀዋል።