ሻንጣ ሙሉ ወርቅ ባቡር ላይ ረስቶ የወረደን ሰው ፖሊስ እያፈላለገ ነው

ወርቅ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ብዙ ወንዶች የኪስ ቦርሳ ታክሲ ላይ ይጥላሉ፡፡ የድምጽ ማዳመጫ (ሄድፎን) መርሳትም የተለመደ ነው፡፡ 'ስዝረከረክ ቻርጀሬን ባቡር ውስጥ ረስቼው ወረድኩ' ብሎ ጸጉሩን የሚነጭም ብዙ ነው፡፡

አንድ ፌስታል ሙሉ ሙዝ ታክሲ ላይ ጥለን በመወርዳችን ሕይወት አዳለጠችኝ ብለን ራሳችንን ረግመንም ይሆናል፡፡ አንድ ሻንጣ ሙሉ ወርቅ ባቡር ላይ ረስቶ የሚወርድም አለ። እንግዲህ ሁሉም ሰው እንደ አኗኗሩ ነው፡፡

ይህ የስዊዘርላንድ ሰው አንድ ሻንጣ ሙሉ ወርቅ ባቡር ውስጥ ረስቶ ነው የወረደው፡፡ ግን ለምን ወንድ ነው ብለን አሰብን? እርግጥ ነው ወንዶች ከሴቶች ይልቅ ዝንጉ ናቸው፡፡

ሙሉ ሻንጣ ወርቁን ዘንግታ የወረደችው ሴት ልትሆንም ትችላለች፡፡

ሰው እንዴት ሻንጣ ሙሉ ወርቅ በባሩር ውስጥ ረስቶ ይወርዳል? ወርቁን ከመርሳት ራስን መርሳትስ አይቀልም ያሉ ብዙ ናቸው፡፡

ይህ ወርቅ ረስቶ/ረስታ የወረደው ሰው (የወረደችው ሴት) ቢፈለግ ቢፈለግ (ብትፈለግ ብትፈለግ) አልገኝ ስላለ/ስላለች ፖሊስ ፍለጋውን ለማቆም ተገዷል፡፡

ባለፈው ጥቅምት ወር ላይ ነበር 3 ኪሎ ግራም የሚመዘዝን ወርቅ ተረስቶ ባቡር ውስጥ የተገኘው፡፡

ባቡሩ ይጓዝ የነበረው ከቅዱስ ጋለን ወደ ሉሰርን ነበር ተብሏል፡፡

የወርቁ ዋጋ እንዲያ በገደምዳሜ ወደ 200ሺህ ዶላር አካባቢ ያወጣል ተብሏል፡፡

የዚህ ሙሉ ወርቅ የሞላበት ሻንጣ ባለቤት ነኝ የሚል ወይም የምትል በአምስት ዓመት ውስጥ የሉሰርን አቃቢ ሕግ ቢሮ ቀርባችሁ ንብረታችሁ ተረከቡ ብሏል ፖሊስ፡፡

ነገሩ በይፋ 'ወርቅ ባቡር ውስጥ የጣለችሁ ኑ እና ውሰዱ' መባል የተጀመረው ፖሊስ ባለቤቶችን በራሱ መንገድ ሊደርስባቸው ሙከራ አድርጎ ስላልተሳካለት ነው፡፡

ፖሊስ በሚቀጥሉት ቀናት እኔ ነበርኩ ባቡር ውስጥ ወርቅ ረስቼ የወረድኩት በሚሉ ሰዎች ሊጨናነቅ ይችል ይሆናል፡፡ ሀቀኛውን ሰው እንዴት ለይቶ ይህንን አዱኛ ሊያስረክብ እንደሚችል የታወቀ ነገር የለም፡፡