ፈረንሳይ ኮሮናቫይረስን ድል ነሳሁት አለች

ኢማኑኤል ማክሮን

የፎቶው ባለመብት, AFP

ኢማኑኤል ማክሮን ለሕዝባቸው ባደረጉት ንግግር ከኮሮናቫይረስ ጋር የነበረውን ጦርነት ፈረንሳይ በድል አጠናቃለች ብለዋል፡፡ ሆኖም ጦርነቱ የመጀመርያ ዙር እንጂ አልተጠናቀቀም፡፡

በዚህም የተነሳ በእንቅስቃሴ ላይ ተጥሎ የነበረው ገደብ እንዲነሳ ፈረንሳይ ወስናለች፡፡

ይህን ተከትሎ ከዛሬ ሰኞ ጀምሮ በየካፌው፣ በየሬስቶራንቱ ዘና ማለት ተፈቅዷል፡፡

በመላው ፈረንሳይ የሚገኙ አገልግሎት መስጫዎችም ለደንበኞች ክፍት ተደርገዋል፡፡ በአገር ውስጥም ሆነ ወደ ሌላ የአውሮፓ አገራት መጓዝም ተፈቅዷል፡፡

መጦሪያና የእንክብካቤ ማዕከላት ውስጥ የሚገኙ አዛውንቶችን መጎብኘትም ይቻላል ብላለች ፈረንሳይ፡፡ እነዚህ የመጦሪያ ማዕከላት ውስጥ በርካታ የዕድሜ ባለጸጋ ፈረንሳዊያን በቫይረሱ ተይዘው መሞታቸው ይታወሳል፡፡

ዛሬ ሰኞ ፈረንሳይ ብቻ ሳትሆን በርካታ የአውሮፓ አገራትም ድንበሮቻቸውን መከፋፈት ጀምረዋል፡፡

ለሕዝባቸው በቴሌቪዥን ንግግር ያደረጉት ማክሮን ቫይረሱን ድል ብናደርገውም ተመልሶ አይመጣም ማለት ግን አይደለም ሲሉ መዘናጋት እንደማያስፈልግ አስጠንቅቀዋል፡፡

ፈረንሳይ ትምህርት ቤቶች ከሰኔ 22 ጀምሮ ወደ መማር ማስተማሩ እንዲገቡ ብላለች፡፡ ይህ መመሪያ ግን የ2ኛ ደረጃ ተማሪዎችን አይመለከትም፡፡

አሁን ገደቦችን ብናነሳም ቫይረሱ በድጋሚ ከመጣ ግን በፍጥነት በራችንን ዘግተን ለመፋለም ተዘጋጅተናል ብለዋል ማክሮን በንግግራቸው፡፡

የትኞቹ የአውሮአገራት ድንበራቸውን ከፈቱ?

የአውሮፓ ኅብረት ከዛሬ ሰኞ ጀምሮ አባል አገራት ድንበራቸውን እንዲከፋፍቱ እያበረታታ ቢሆንም ሁሉም አባላት ግን ተቀብለውታል ማለት አይደለም፡፡

ለጊዜው ዛሬ ሰኞ ድንበር ሙሉ በሙሉ እንከፍታለን ካሉት መካከል ቤልጂየም፣ ክሮሺያ፣ ስዊዘርላንድና ጀርመን ይገኙበታል፡፡

ቼክ ሪፐብሊክ ድንበሬ ለ26 አገራት ክፍት ነው፣ ሆኖም ግን ለስዊድን፣ ለዩናይትድ ኪንግደም፣ ለፖርቹጋልና ለቤልጅየም አልፈቀድኩም ብላለች፡፡

ግሪክ በበኩሏ እንኳንስ ከዚህ ከአውሮፓ ይቅርና እንደ አውስራሊያ፣ ኒውዚላንድ፣ ጃፓንና ደቡብ ኮሪያ ካሉ ሩቅ አገራት ጭምር ለሚመጡ ድንበሬ ክፍት ነው ብላለች፡፡

ጣሊያንና ሆላንድ ቀደም ብለው ድንበራቸውን የከፈቱ አገራት ናቸው፡፡

ስፔንና ሉክዘምበርግ ወረርሽኙ ከተከሰተ ጀምሮ ድንበራቸውን ያልዘጉ ብቸኛ አገራት ናቸው፡፡

ፈረንሳይ የአካባቢ ምርጫን አራዝማለች

ፈረንሳይ 2ኛ ዙር የአካባቢ ምርጫ መርኅ ግብር ለጊዜው እንዲራዘም ወስናለች፡፡ መጋቢት ላይ ይደረጋል የተባለው ይህ ምርጫ ወደ ሰኔ 28 ተገፍቷል፡፡

ሆኖም ምርጫው የሚካሄደው ተገቢው ርቀት ተጠብቆ በከፍተኛ ጥንቃቄ ይሆናል ተብሏል፡፡

ፈረንሳይ 29 ሺህ 400 ዜጎቿን ቫይረሱ ገድሎባታል፡፡

አሁንም ድረስ በቫይረሱ የተያዙት ደግሞ 194 ሺህ ደርሰዋል፡፡ ሆኖም አዲስ የሚያዙት ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል፡፡