በዩትዩብ የትኞቹ አፍሪካውያን ሙዚቀኞች ይመራሉ?

ዲጄ ኢዱ፣ ዳይመንድ ፕላትነምዝ፣የሚ አላዴ፣ አያ ናኩማራ

ዳይመንድ ፕላትነምዝ ታንዛኒያዊ ሙዚቀኛ ነው፡፡ ፕላትነምዝ የመድረክ ስሙ ሲሆን ነሲቡ አቡዱል ጁማ የሚለውን የፓስፖርት ስሙን የሚያውቀው ያለም አይመስልም፡፡

የተወለደው በዳሬ ሰላም ነው፡፡ አሁን ገና 30 ደፍኗል፡፡

ባለፈው ሳምንት ብዙዎች የሚወዱለትን ደረቱን አጋልጦ በግማሽ እርቃን ቤተ መንግሥት በመሰለ ቤቱ እየተንጎማለለ ሳለ የርሱ የሙዚቃ ኩባንያ ሰራተኞቹ ‹‹በድንገቴ የምስራች!›› አስደነገጡት፡፡

ያስጋገሩት ኬክ የ‹ዩትዩብ› ልዩ የንግድ መለያ ቀይ ምልክት የተደረገበት ነበር፡፡

ለካንስ እሱ ዘንግቶት እንጂ ዳይመንድ ፕላትነምዝ በዩቲዩብ የተመልካቾቹ ቁጥር ያን ዕለት 1 ቢሊዮን ሞልቶ ነበር፡፡ ለዚህም ነበር የምሥራቹ!

ባለፉት 10 ዓመታት ዳይመንድ ፕላትነምዝ በርካታ ሽልማቶች አግኝቷል፡፡ የስዋሂሊ ቋንቋን ከእንግሊዝኛ ጋር በማቀናጀት ባህላዊና ዘመናዊ የሙዚቃ ቃናዎች በማዳቀል ተወዳጅ ሥራዎችን ለአድናቂዎቹ አቅርቧል፡፡

‹‹ፕላትነምዝ በጣም ታታሪ ሙዚቀኛ ነው›› ይላል ዲጂ ኤዱ፡፡

ዲጄ ኤዱ ሳምንታዊውን የፓን አፍሪካን የሙዚቃ ዝግጅትን በቢቢሲ ለረዥም ዘመን ሲያጫውት የኖረ የራዲዮ ሙዚቃ አሳላፊ (ዲጄ) ነው፡፡

55 ሚሊዮን ሕዝብ ባላት ታንዛኒያ ዘመናዊ ስልክ ኖሮት ኢንተርኔት የሚያገኘው ሕዝብ በየጊዜው እየጨመረ መምጣቱ ዳይመንድን ለመሰሉ ሙዚቀኞች ትልቅ ገበያ ነው፡፡

ለጊዜው ከታንዛኒያ ሕዝብ 43 ከመቶ ብቻ ነው ኢንተርኔትን በስልኩ ማግኘት የሚችለው፡፡

ከዳይመንድ ሌላ አዳዲስ ሙዚቀኞች በስዋሂሊ ተናጋሪ ምሥራቅ አፍሪካዊያን ዘንድ ተወዳጅ እየሆኑ ነው፤ ዕድሜ ለበይነመረብ፤ ዕድሜ ለ‹ዩትዩብ›፡፡

ቢሊዮን ተመልካች በዩቲዩብ ማግኘት ብርቅ ነው?

ዳይመንድ ፕላትነምዝ ከዩትዩብ ይልቅ በኢንስታግራም በርካታ ተከታይ አለው፡፡ የዩትዩብ ታማኝ ተከታዮቹ (ሰብስክራይበርስ) 3.7 ሚሊዮን ሲሆኑ የኢንስታግራም ግን 9.7 ሚሊዮን ደርሰዋል፡፡

ዲጄ ኤዱ እንደሚለው ኢንስታግራም በዋናነት የሕይወት ዘይቤና ፋሽንን መስበኪያ መድረክ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዝነኛ የሆነው ቲክቶክ በአንጻሩ በጣም ወጣት የሆኑ አድናቂዎችን ለመመልመል ይበልጥ ተመራጭ ነው፡፡

ገና ከወዲሁ አንዳንድ ሙዚቃዎች እጅግ ዝነኛ ሆነዋል በቲክቶክ፡፡ ለምሳሌ ዳይመንድ ፕላትነምዝ በቅርቡ የለቀቀው ኳረንቲን የተሰኘ ሥራው ተወዳጅ የሆነው በቲክቶክ አማካኝነት ነው፡፡

ተወዳጅ የሆኑ ሥራዎችን ወደ ዩትዩብ መውሰድ የተለመደ የሆነው በ‹ዩትዩብ› በማስታወቂያ የሚገኘው ገንዘብ ጠርቀም ያለ ስለሆነ ነው፡፡

ባለፉት ዓመታት ለአፍሪካ ሙዚቀኞች ዩትዩብ እጅግ ጠቃሚው የመታያ መድረክ ሆኗል፡፡ ምክንያቱም አሁን ቴሌቪዥን ጣቢያዎችን ደጅ መጥናት እየቀረ መምጣቱ ነው፡፡ በጣቢያዎች ይሁንታ ለማግኘት የነበረው ዕድል አሁን በሞዛቂዎቹ በእጃቸው እንዲገባ የሆነው በዩትዩብ ምክንያት ነው፡፡

በዩትዩብ ከአፍሪካ ማን ይመራል?

ዳይመንድ ፕላትነምዝ ከሰሀራ በታች ከፍተኛ የዩትዩብ አድናቂዎች ቁጥር ቢኖረውም እርሱን ከሰሜን አፍሪካ ሞዛቂዎች ጋር ካነጻጸርነው እዚህ ግባ የሚባል አይሆንም፡፡

ምክንያቱም የሰሜን አፍሪካ ሞዛቂዎች ከሰሀራ በታች ካሉት ይልቅ በቀላሉ ዝነኛ ስለሆኑ ነው፡፡

የሰሜን አፍሪካ አገራት በመካከለኛው ምሥራቅ የአረብኛ ተናጋሪዎች ዘንድ የመታየት ዕድል ስለሚኖራቸው ሰፊ መልከአምድር የመሸፈን ዕድል ያገኛሉ፡፡

አንዳንድ የአፍሪካ አገራት ሙዚቀኞች ደግሞ ተቀማጭነታቸው በአፍሪካ ባይሆንም ሰፊ የዩትዩብ ተቀባይነት ሊያገኙ ይችላሉ፡፡

ለምሳሌ የማሊ ተወላጇ አያ ናካሙራን ብንወስድ የምትኖረው በፈረንሳይ ቢሆንም በ2018 የለቀቀችው ጃጃ (Djadja) የተሰኘው ሥራዋ 1.7 ቢሊዮን ተመልካቾች ወደውላታል፡፡ አያ ገና 25 ዓመቷ ነው፡፡

በዚህ ረገድ ሌላው ተጠቃሽ ኤኮን ነው፡፡ የሴኔጋሉ ተወላጅ ኤኮን 3.5 ቢሊዮን የዩትዩብ ተመልካች አግኝቷል፡፡

ከሰሀራ በታች በዩትዩብ ተመልካች ብዛት ከዳይመንድ ፕላትነምዝ የሚፎካከሩ ሞዛቂዎች የሚከተሉት ናቸው፡፡

  • ፒ ስኬዌር - 810 ሚሊዮን
  • ዴቪዶ - 618 ሚሊዮን
  • ፍሌቨር - 617 ሚሊዮን
  • ቴክኖ - 574 ሚሊዮን
  • በርናቦይ - 507 ሚሊዮን
  • ዊዝኪድ - 480 ሚሊዮን

በዚህ ዝርዝር ውስጥ የዴቪዶና የበርና ቦይ ቁጥር ልዩ የሚያደርገው ሁለቱም ዩትዩብ የከፈቱት ከ2 ዓመት በፊት ገና በ2018 ነበር፡፡ ዳይመንድ ፕላትነምዝ ግን ከ2011 ጀምሮ ዩትዩብ ላይ ነበረ፡፡

ዊዝኪድ በበኩሉ ስታርቦይ ቲቪ የሚባል የሙዚቃ ዩትዩብ መለያና ስቱዲዮ አለው፡፡ በዚያ በኩል ያለው ተመልካቹን ስንደምረው የዩትዩብ ተመልካቾቹ ብዛት 802 ሚሊዮን ያልፋል፡፡

አንዳንድ ሙዚቀኞች ሥራዎቻቸውን በሙዚቃ ስቱዲዮ በኩል እንዲለቀቅ ያደርጋሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ በቀጥታ በራሳቸው ቻናል ይለቁታል፡፡ ሙዚቃ አሰናጆች ቢሮክራሲያቸው ይበዛል ብለው የሚያስቡ ናቸው በራሳቸው መንገድ በቀጥታ መልቀቅ የሚመርጡት፡፡

ማጂክ ሲስተም የተሰኘው የአይቮሪኮስት የደቦ ሙዚቃ ቡድንም ቀላል ተመልካች አይደለም ያገኘው፡፡ 477 ሚሊዮን ሰዎች ተመልክተውታል፡፡ ይህ የሙዚቃ ቡድን በተለይ በምዕራብ አፍሪካ የፈረንሳይኛ ተመልካቾች ዘንድ ተወዳጅ ናቸው፡፡

ዊዝኪድ ከካናዳዊው እውቅ አቀንቃኝ ድሬክ ጋር በ2016 በጥምረት የሰራው ‹‹ዋን ዳንስ›› የተሰኘው ሥራው 1.8 ቢሊዮን ጊዜ በዩትዩብ ተሰራጭቷል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ ማን በርካታ ዩትዩብ ተመልካች አለው?

ካናዳዊው ድሬክ 7 ቢሊዮን የዩትዩብ ተመልካች አለው፡፡

ቢዮንሴ 12 ቢሊዮን የዩትዩብ ተመልካች አግኝታለች፡፡

ቢዮንሴ ባለፈው ዓመት ከአፍሪካዊ አርቲስቶች ጋር የ‹‹ላየን ኪንግ›› አልበምን መሥራቷ ይታወሳል፡፡

ገና በአዳጊ ዕድሜው ዝናን የተቀዳጀውና አሁን የ26 ዓመት ወጣት የሆነው ካናዳዊው ጀስቲን ቢበር 21.6 ቢሊዮን ተመልካቾች አሉት፡፡

በ2016 የተመሰረተው የሴት ሞዛቂዎች ቡድን ብላክፒንክ 9 ቢሊዮን የዩትዩብ ተመልካቾች አሉት፡፡

የአፍሪካ ሴት ሞዛቂዎች ደረጃ የት ነው?

በሚገርም ሁኔታ ሴት የአፍሪካ ሙዚቀኞች በርካታ የዩትዩብ ሙዚቀኛ ማግኘት አልሆነላቸውም፡፡

ለምሳሌ የሚ አላድ እና ቲዋ ሳቬጅ ከወንድ አቻዎቻቸው ጋር ሲነጻጸር እጅግ ያነሰ የዩትዩብ ተመልካች ነው ያላቸው፡፡ የሚ 434 ሚሊዮን፣ ቲዋ ደግሞ 239 ሚሊዮን ተመልካቾች አግኝተዋል፡፡

ይህ ምናልባት የአፍሪካ የሙዚቃ መድረክ በወንዶች የተያዘ መሆኑ እና ለሴቶች እምብዛምም ቦታ አለመኖሩ ያመጣው ችግር ይመስለኛል ይላል ዲጄ ኤዱ፡፡

"እንዲያውም እኮ በቅርብ ጊዜ ነው ለትልልቅ የሙዚቃ ድግሶች ሴት ሙዚቀኞችን በዋናነት ማስፈረም እየተለመደ የመጣው፡፡ ትልልቅ መድረኮች ላይ እየተጋበዙ ቢሆን ኖሮ ብዙ ተከታይ እያፈሩ መምጣታቸው ደግሞ አይቀርም" ይላል ዲጄ ኤዱ፡፡

ከሙዚቀኞች እኩል የወንጌል ዘማሪዎችም በአፍሪካ የሙዚቃ ገቤ ትልቅ የዩትዩብ ተመልካች አላቸው፡፡

ለምሳሌ ዘማሪ ሲናች 472 ሚሊዮን ተመልካቾች አሏት፡፡ ይህን ማሳካት የቻለችው ደግሞ ዓለም አቀፍ መንፈሳዊ ጉባኤዎችን ስለምትመራና በ‹‹ክራይስት ኤምባሲ›› ቤተ ክርስቲያን ስለምትሰብክ ነው፡

"ዘማሪዎች ተከታይ ለማግኘት መድከም አይጠበቅባቸውም፡፡ ለመዝሙራቸው ግጥም ሲመርጡም አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መስመር ሳብ አድርጎ ማውጣት ብቻ ነው የሚጠበቅባቸው፡፡ እንዲህ ሲያደርጉ ግጥሞቻቸው ቤት የሚመቱት በራሳቸው ጊዜ ነው፡፡ ተከታይ ለማፍራት ብዙ መድከም አይጠበቅባቸውም" ይላል ዲጄ ኤዱ፡፡

የትኛው ይሻላል? በአካል ወይስ በዩትዩብ

እንደ ኡጋንዳዊው ኤዲ ኬንዞ ያሉ ዘፋኞች ከመድረክ ሥራ ይልቅ የበይነ መረብ በኩል ዝናን ማጋበስ የተሻለ ነው ብለው ያምናሉ፡፡ ኬንዞ 388 ሚሊዮን የዩትዩብ ተመልካች አለው፡፡

ለአንጎላዊው ሲፎር ፔድሮ ግን ለመድረክ ሥራ ከአገር አገር መዞርን የመሰለ የለም፡፡

የኪዞምባ ስልት ኮከቡ ፔድሮ ብዙ አገር ሄዶ ስታዲየም ሙሉ ታዳሚ ማግኘት ይችላል፡፡ ዳይመንድ ፕላተነምዝ ግን ምንም እንኳ በዩትዩብ ዝነና ቢሆንም ዓለም አቀፍ ተጽእኖ ፈጣሪነቱ ውስን ነው፡፡

ኾኖም ግን ዝናና ገናና ስም ገና ላልገነቡ የአፍሪካ ሙዚቀኞች ዩትዩብን የመሰለ መድረክ የለም፡፡ ገና ጀማሪ ወጣቶች ዩትዩብን ይመርጣሉ፣ ገፋ ያሉት ደግሞ መድረክ ይወዳሉ፡፡

ለምሳሌ የዚምባብዌ ተወላጅ የ32 ዓመት ሙዚቀኛ ጃ ፕራይዛህ 99 ሚሊዮን የዩትዩብ ተመልካቾች አሉት፡፡

የአፍሪካ አፍሮ ጃዝ አባት እየተባለ የሚሞካሸውና የአህጉሪቱ ጥላሁን ገሠሠ የሚባለው ኦሊቨር ምቱኩዚ ግን ባለፈው ዓመት ሕይወቱ እስክታልፍ ድረስ ከመድረክ አልራቀም፤ የሚደንቀው እስኪሞት ድረስ አንድም የየትዩብ ቻናል በስሙ አልነበረም፡፡

"ኦሊቨር ምቱኩዚን ካየሽው ዕድሜ ዘመኑን ከመድረክ መድረክ ጊታሩን ይዞ ሲዞር ነው የኖረው፡፡ የሙዚቃ ጉዞው ፋታ አልነበውረም፤ ዓለምን ሲዞር ኖሮ ነው የሞተው ፡፡ አንዳንድ ጊዜ መቶ ሚሊዮን የዩትዩብ ተመልካች ከመቃረም 50 ጽድት ያሉ የመድረክ ሥራዎችን አቅርቦ ማለፍ ይሻል ይሆን ያስብላል" ይላል ዲጄ ኤዱ፡፡

በገቢ ረገድም ቢሆን ዩትዩብ ሚሊዮነር አያደርግም፡፡

"አንድ ሚሊዮን ተመልካች በዩትዩብ ያገኙ 3ሺህ ዶላር ያገኛሉ፡፡ አንድ ቆንጆ መድረክ ሥራ የዚህን 10 እጥፍ አያስገኝም?"