አፋር፡ የአዋሽ ወንዝ ባሰከተለው ጎርፍ ከ27 ሺህ በላይ ሰዎችን አፈናቀለ

የአዋሽ ወንዝ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በአፋር ክልል ባለፉት ሁለት ሳምንታት የአዋሽ ወንዝ በከፍተኛ ሁኔታ ሞልቶ ሰፊ አካባቢን በማጥለቅለቁ ከ27 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ከመኖሪያ ቦታቸው ተፈናቀሉ።

የክልሉ የአደጋ መከላከልና የምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሐመድ ሁሴን ለቢቢሲ እንዳስታወቁት አደጋው የተከሰተው በአዋሽ ወንዝ መሙላትና በደራሽ ጎርፍ ምክንያት መሆኑን ጠቁመዋል።

በዚህም በተለይ በ12 ወረዳዎች ውስጥ 67 ሺህ የሚሆን ሕዝብ በጎርፍ አደጋው ሰለባ መሆኑን ጠቁመዋል።

በአደጋው ምክንያት የአንድም ሰው ህይወት አላለፈም ያሉት መሐመድ ከ10 ሺህ በበላይ እንስሳት ላይ ጉዳት መድረሱን አስታውቀዋል።

ችግሩን ለመቅረፍ ክልሉ በራሱ አቅም የምግብ፣ የመጠለያ እና ህክምና ቁሳቁሶችን በማቅረብ ላይ ይገኛል።

ከፌደራል መንግሥት በቀረበ ሔሊኮፕተር በአደጋው ቀጣና ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን የማውጣት ሥራ ከማከናወን ጎን ለጎን ምግብ የማቅረብ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።

ሰዎችን ከአደጋ ቀጣና ከማውጣት ጎን ለጎን ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው የክረምቱ ዝናብ እስከ መስከረም አጋማሽ እንደሚቀጥል ትንበያዎች ያሳያሉ ያሉት አቶ መሐመድ፤ ከዚያ በኋላ ደግሞ በዘላቂነት ለማቋቋም መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ካለው የሃብት እና የሎጂስቲክስ እጥረት በተጨማሪ በመኪና በመንቀሳቀስ እርዳታ ለመስጠት ስለማይመች ተጨማሪ ሔሊኮፕተር እንዲቀርብ ጥያቄ ለፌደራል መንግሥት ቀርቧል ብለዋል።

በፌደራል መንግሥት በኩል እርዳታ መቅረብ መጀመሩን ኃላፊው አስታውቀው ነገር ግን በተለይ ለሰብዓዊ እርዳታዎች ትኩረት በመስጠት በፍጥነት እንዲደርስ ሊሠራ ይገባል ብለዋል።

በአገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንም ከክልሉ የአደጋ መከላከልና የምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ጋር በመተባበር ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

የአዋሽ ወንዝ በተደጋጋሚ ጊዜ የሚያደርሰው ጉዳት ተፈጥሮአዊ በመሆኑ መከላከል ባይቻልም ወንዙ ላይ የተለያዩ ግድቦችን በመሥራትና የቅድመ መከላከል ሥራ በማከናወን ችግሩን መቀነስ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በጎርፉ አደጋ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተፈናቃዮች በሚገኙበት አሳኢታ ተገኝተው ሁኔታውን የተመለከቱት የአፋር ክልል ቀይ መስቀል ቅርንጫፍ ጽፍፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሊ ሷሊህም፤ ማህበሩ የላከው 400 ኩንታል ምግብ እየተጓጓዘ መሆኑን ገልጸው አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልግ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ተፈናቃዮቹ በአሁኑ ውቅት በትምህርት ቤቶች ውስጥ ተጠልለው እንደሚገኙ የገለፁት አቶ አሊ ያሉበት ሁኔታ ለኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ አጋላጭ በመሆኑ ይህንንም በተወሰነ መልኩ ለማቃለል ከምግብ እርዳታው ጋር የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ፣ የእጅ ማጽጃ እና ንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን ማቅረብ እንደሚያስፈልግ አመልከተዋል።

የአዋሽ ወንዝ በየዓመቱ በዝናብ ወቅት ሞልቶ በሚያስከትለው የጎርፍ መጥለቅለቅ ሳቢያ በአፋር ክልል ተደጋጋሚ ጉዳት በየጊዜው ያደርሳል።