አውሮጳ፡ የፖርቹጋሉ ፕሬዚደንት በባህር ማዕበል ሲናወጡ የነበሩ ሁለት ሴቶችን ታደጉ

የፖርቹጋሉ ፕሬዚደንት ማርሴሎ ሬቤሎ ደ ሶውሳ በአልጋርቭ የባህር ዳርቻ

የፎቶው ባለመብት, RADIOTELEVISAO PORTUGUESA

የፖርቹጋሉ ፕሬዚደንት ማርሴሎ ሬቤሎ ደ ሶውሳ በአልጋርቭ የባህር ዳርቻ የሽርሽር ጀልባቸው ተገልብጣባቸው ነፍሳቸውን ለማትረፍ ሲታገሉ የነበሩ ሁለት ሴቶችን ሕይወት መታደጋቸው ተገለፀ።

የ71 ዓመቱ ፕሬዚደንት ቅዳሜ እለት በማዕበል እየተናወጡ የነበሩ ሴቶችን ለመታደግ ወደ ጀልባዋ ሲዋኙ የሚያሳይ ምስሎች ወጥተዋል።

ፕሬዚደንት ሬቤሎ ዲ ሶውሳ በእረፍት ላይ የነበሩ ሲሆን፣ ጊዜያቸውን ቱሪዝምን ለማስተዋወቅ የተለያዩ ቦታዎችን በመጎብኘት እያሳለፉ እንደሆነ ተገልጿል። በወቅቱም በአልጋርቭ የባህር ዳርቻ ነበሩ።

ሴቶቹ ከውሃው ለመውጣት ሲታገሉ የተመለከቱትም ከጋዜጠኞች ጋር እየተነጋገሩ ባለበት ጊዜ እንደነበር የጠቀሱት ፕሬዚደንቱ፤ በአቅራቢያ ካለ የባህር ዳርቻ በማዕበል ተገፍተው እንደመጡም በኋላ ላይ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

በመገናኛ ብዙኀን ይፋ የሆኑ ተንቀሳቃሽ ምስሎችም ፕሬዚደንቱ ሴቶቹን ለመርዳት እየዋኙ ሲሄዱ አሳይተዋል።

ሲደርሱ ግን ሌላ ሰው ቀድሟቸው እነርሱን ለመርዳት እየሞከረ ነበር ያገኙት። ከዚያም ሌላ ግለሰብ የሞተር ጀልባ ይዞ እርዳታ ለመስጠት በሥፍራው ደርሷል። የሞተር ጀልባ ይዞ የደረሰው ግለሰብም ጀልባዋን ወደ ባህር ዳርቻው ማውጣት ችሏል።

እርሳቸውም ጀልባዋን ወደ ነበረችበት ለመመለስ ፈታኝ እንደነበር ገልፀው፤ የሞተር ጀልባ የያዘው ግለሰብ እርዳታ እንዳደረገላቸው ተናግረዋል።

ለወደፊቱ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ሴቶቹን አሳስበዋቸዋል።

ፖርቹጋል በርካታ እንግሊዛዊያን ጎብኝዎች ያሏት ሲሆን በዓመት ከ3 ሚሊየን በላይ ጎብኝዎች የሚጎርፉትም ከዩናይትድ ኪንግደም ነው።

ከዩናይትድ ኪንግደም የሚመጡ ጎብኝዎችም በአብዛኛው የሚሄዱት ወደ አልጋርቭ ባህር ዳርቻዎች ነው።

ፖርቹጋል በዋናነት ኢኮኖሚዋ የተመሰረተው በቱሪዝም ኢንዱስትሪ ላይ ቢሆንም በዘንድሮው ዓመት ግን በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ ዘርፉ ከፍተኛ ተፅዕኖ ደርሶባታል።