በኢትዮጵያ የመጀመሪያ ነው የተባለ የእንስሳት አምቡላንስ ስራ ጀመረ

የቢሾፍቱ የጤናና ግብርና ኮሌጅ የእንስሳት አምቡላንስ

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የእንስሳት ሕክምናና ግብርና ኮሌጅ ለአገራችን ግንባር ቀደም የተባለውን የእንስሳት አምቡላንስ ሥራ አስጀምሯል።

አምቡላንሱ በሬ ወይም ግመል ሲታመም እንስሳቱ ያሉበት ድረስ ሄዶ ሕክምና ይሰጣል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የእንስሳት ሕክምናና ግብርና ኮሌጅ ኮሌጅ ዲን የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ሒካ ዋቅቶላ ስለ አምቡላንሱ ሲናገሩ፣ "በአገሪቱ እስካሁን የነበረው የሰው አምቡላንስ ነው። ይህ የመጀመሪያ የእንስሳት አምቡላንስ ነው" ብለዋል።

አክለውም አምቡላንሱ በቢሾፍቱ ከተማ እንዲሁም በከተማው ዙሪያ ባሉ የገጠር ከተሞች ለሚታመሙ እንስሳት አገልግሎት እንደሚሰጥ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አምቡላንሱ ማንኛውንም ሕክምና መስጠት የሚያስችል መሣሪያ የተገጠመለት ሲሆን እንስሳት በጠና ሲታመሙ ያሉበት ድረስ የህክምና ባለሙያ ይላካል ሲሉ ገልፀዋል።

እስካሁን ሥራ የጀመረው አንድ አምቡላንስ ብቻ መሆኑን የተናገሩት ፕሮፌሰር ሂካ፣ ከቢሾፍቱና አካባቢው በስተቀር አገልግሎት መስጠት አይችልም ብለዋል። በተጨማሪም "ይህ ጥሩ ጅማሮ ስለሆነ ለወደፊትም ተጨማሪ የእንስሳት አምቡላንሶች የመጨመር እቅድ አለ።"

ኢትዮጵያ በቀንድ ከብት ብዛት በዓለም አምስተኛ በአፍሪካ ደግሞ አንደኛ ናት።

እንደ ረዳት ፕሮፌሰር ሒካ ከሆነ በአሁን ወቅት የተሻሻለ ዝርያ ያላት ላም እስከ 50 ሺህ ብር ድረስ ስትሸጥ ግመል ደግሞ ከዚያ በላይ ያወጣል።

በቀላሉ መዳን የሚችሉ እንስሳት ሲሞቱ አርሶ አደሮች ከፍተኛ ችግር ውስጥ መውደቃቸውም አይቀርም የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ፣ "ስለዚህም የአምቡላንሱ ስራ መጀመር ለአርሶ አደሩ መልካም ዜና ነው።" ብለዋል።

ከዚህ በፊት እንስሳት ሲታመሙ ወደ ኮሌጁ ጤና ተቋም ይሄዱ ነበር። ከዚህ በኋላ ግን ባሉበት ህክምና እንደሚያገኙ ተባባሪ ፕሮፌሰር ሒካ ገልጸዋል።

"ምጥ ላይ ያለችን እንስሳ ወይም የታመመን እንስሳ ረዥም ርቀት ይዞ መሄድ ያስቸግራል። ስለዚህ አምቡላንሱ ላይ ባለው ስልክ ቁጥር አርሶ አደሮቹ ሲደውሉልን ያሉበት ድረስ ባለሙያዎች እንልካለን።"

የቢሾፍቱ የጤናና ግብርና ኮሌጅ ከዚህ ቀደም የፈረስ ሆስፒታል መክፈቱ ይታወሳል።

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ,

በዓመት ከ6 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ፈረሶች ነጻ ህክምና የሚሰጠው የፈረሶች ክሊኒክ