የሴቶች መብት፡ የገዛ ሴት ልጁን እየቀረጸ ወሲባዊ ጥቃት የፈጸመው ፍርድ ቤት ቀረበ

ጥቃት አድራሱ በፖሊስ ቁጥጥር ስር በዋለበት ወቅት

የፎቶው ባለመብት, AFP

በጀርመን ከፍተኛ ድንጋጤ የፈጠረ ጉዳይ ሆኗል፡፡ በኮሎን ከተማ የገዛ ሴት ልጁን በወሲባዊ ጥቃት ሲያሰቃይ የነበረው ሰው ፍርድ ቤት ቀርቧል፡፡

ከ2ኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ በልጆች ላይ የደረሰ ትልቅና ውስብስብ የወሲባዊ ጥቃት ፍርድ ሂደት ተደርጎ ተወስዷል፣ የዚህ ተጠርጣሪ ጉዳይ፡፡

ተጠርጣሪው ስሙ ለሴት ልጁ የወደፊት ጤና ሲባል አልተጠቀሰም፡፡ ሆኖም በሆቴል ቤት ምግብ አብሳይ እንደሆነ ተገልጧል፡፡

ይህ ሰው ሴት ልጁን ወሲባዊ ጥቃት እያደረሰባት በቪዲዮ ከቀረጸ በኋላ በህጻናት ወሲብ ሱስ ለተጠመዱ አስር ሺዎች አባል ለሆኑበት አንድ ሚስጥራዊ የኢንተርኔት ትስስር መድረክ ቪዲዮን ያጋራ ነበር ተብሏል፡፡

ቪዲዮን የሚያጋራው ትሪማ በተሰኘ ምስጢራዊ የትስስር መድረክ ላይ ነው፡፡

ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ላይ ፖሊስ ኮሎን በሚገኘው የሰውየው ቤት ላይ ድንገቴ ብርበራ ባደረገበት ወቅት ሌሎች በተመሳሳይ አስነዋሪ ድርጊት የሚፈጽሙ የወንጀለኛ ሰንሰለቶችን እንዲደርስባቸው የረዱ ፍንጮችን ማግኘት ችሏል፡፡

የድንገቴ ብርበራው ለጊዜው በ16 የጀርመን ክልሎች ውስጥ 87 ተጠርጣሪዎች እንዲደርስባቸው መንገድ ጠርጓል፡፡

የሕጻናት ላይ ጥቃት ፈጻሚዎቹ ከ3 ወር እንቦቀቅሎች አንስቶ እስከ 15 ዓመት አዳጊዎች ላይ ወሲባዊ ጥቃት ያደርሱ እንደነበረ የማያወላዳ የቪዲዮ መረጃ ተገኝቶባቸዋል፡፡

ይህንን መረጃ ተከትሎ ፖሊስ 50 ሕጻናትን ከወላጆቻቸው በመውሰድ ታድጓቸዋል፡፡

የዚህ ተጠርጣሪ ጉዳይ አሁን በፍርድ ቤት ሂደት ላይ ሲሆን የገዛ ሚስቱ በሰውየው ላይ ምስክርነት ትሰጣለች ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡

በዚህ እጅግ አሰቃቂና ፀያፍነቱ ወደር አልባ በተባለ የሕጻናት ወሲባዊ ጥቃት ዙርያ መርማሪ ሆነው ሲሰሩ የነበሩ ሦስት ጀርመናዊያን ባዩት ነገር የአእምሮ መረበሽ ደርሶባቸው እረፍት እንዲወስዱና የሥነልቦና ድጋፍ እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡

ይህ አባት በገዛ ሴት ልጁ ላይ በትንሹ 61 ጊዜ ጥቃት ፈጽሞባታል፡፡

የፍርድ ሂደቱ 11 ቀናትን እንደሚቆይ እና ተጠርጣሪውም እስከ 15 ዓመት እስር ሊፈረድበት እንደሚችል የጀርመን ሚዲያዎች እየዘገቡ ነው፡፡

በዚህ የሕጻናት ወሲባዊ ጥቃት ይዘት ያላቸው ቪዲዮዎችን በሚጋሩበት ምስጢራዊ የትስስር መድረክ በትንሹ 30 ሺህ ጥቃት ፈጻሚዎች አባል እንደሆኑበት ተጠቅሷል፡፡

በዚህ ምስጢራዊ የበይነ መረብ ትስስር መድረክ ላይ ተጠርጣሪውና ሌላ አንድ ወንጀለኛ የገዛ ልጆቻቸው ላይ እየተቀያየሩ ወሲባዊ ጥቃት ሲያደርሱ ይታያሉ፡፡