ጉዲፈቻ፡ ወላጆች የላቸውም በማለት ኡጋንዳውያን ህፃናትን በማደጎ የሸጡት አሜሪካውያን ለፍርድ ሊቀርቡ ነው

አንድ ጥቁር ህፃን እጅ የያዘ ፈረንጅ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በኡጋንዳ ህፃናትን ቤተሰብ የላቸውም በማለት ወደ አሜሪካ በማደጎ ሽፋን ሲሸጡ የነበሩት አሜሪካውያንን ክስ ሊመሰርት መሆኑን የአሜሪካ የፍትህ መስሪያ ቤት አስታውቋል።

በማጭበርበርና ህገ ወጥ የገንዘብ ማዘዋወር ክስ ይቀርብባቸዋል ተብሏል።

ማርጋሬት ኮልና ዴብራ ፓሪስ የተባሉ ሁለት አሜሪካውያንና ዶራህ ሚሬምቤ የተባለች ኡጋንዳዊ ጠበቃን ጨምሮ ተመሳጥረው ልጆቹን ከቤተሰቦቻቸው በመለየት ለአሜሪካውያን ቤተሰቦች በማደጎ እንዲሰጡ በማድረግ በመቶ ሺዎች ዶላር በማትረፍ ነው የተወነጀሉት።

የኡጋንዳዊቷ ጠበቃ ድርጅትም አቅማቸው ደካማ የሆኑ ቤተሰቦችን ራቅ ካለ ገጠራማ ስፍራዎች በመሄድ ወደ መዲናዋ ካምፓላ የተሻለ ህይወት እንደሚጠብቃቸው በመንገር በርካታ ልጆችን አምጥቷል።

የልጆቹን ቤተሰቦችም አሜሪካ የተሻለ ትምህርት ያገኛሉ በሚልም ቃል ገብተው ነው ሲወስዷቸው የነበረው።

ግለሰቦቹ ልጆቹን ለትምህርት መላክ ሳይሆን ወላጅ የሌላቸው ናቸው በማለት ወደ ፍርድ ቤት በመውሰድ በማደጎም ወደ አሜሪካ ልከዋቸዋል።

ግለሰቦቹ በቤተሰቦቹ ደካማ ጎን በመግባት ድህነታቸውን በመጠቀም ለልጆቻቸው መልካም የሚመኙትን ተስፋ የነጠቀ፤ እንዲሁም ወልደው ለመሳም የፈለጉ አሳዳጊ ቤተሰቦችንም እንዲሁ ልፋት መና ያስቀረም ነው ተብሏል።

የአሜሪካ የገንዘብ መስሪያ ቤት በኡጋንዳዊቷ ጠበቃ፣ ባለቤቷና፤ ሞሰስ ሙኪቢና ዊልሰን ሙሳሉ በተባሉ ሁለት ዳኞች ላይ ኢኮኖሚያዊ ዕቀባ ጥሏል።

እነዚህ ግለሰቦች ከአሜሪካውያኑ ጋር በመመሳጠር ገንዘብ በጉቦ በመቀበል የልጆቹ ቤተሰቦች ሞተዋል በማለት በማደጎ እንዲላኩ አሳልጠዋል።

ከሁለት ወራት በፊትም በኬንያ የሚገኙ ማደጎ ህፃናት ላይ ወሲባዊ ጥቃት የፈፀመው አንድ አሜሪካዊ ጥፋተኝነቱን አምኟል። የክርስቲያን ሚሲዮናዊ ነኝ የሚለው ግለሰብ በማደጎ የሚገኙ ሴቶች ህፃናት ላይ ወሲባዊ ጥቃት በመፈፀም ክስ የተመሰረተበትም በአሜሪካ ነው።

የ61 አመቱ ግሪጎሪ ዶው በአራት ወንጀሎችም ሲሆን የተከሰሰው ግለሰቡ አቋቁሞት የነበረው ማደጎ ቤት ከጎርጎሳውያኑ 2008- 2017 ድረስ አገልግሎት ሲሰጥ ነበር ተብሏል።

የፌደራል ቢሮ ምርመራ (ኤፍቢአይ) ከኬንያ ባለስልጣናት ጋር በመሆን ግለሰቡን ሲመረምሩት ነበር።