ሊባኖስ፡ ራፊቅ ሐሪሪን ማን ገደላቸው? ዛሬ ምላሽ ያገኛል

ራፊቅ ሐሪሪ ከባለቤታቸው ጋር

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ራፊቅ ሐሪሪ የቀድሞው የሊባኖስ ጠቅላይ ሚኒስትር ነበሩ፡፡

ሞታቸው በአካባቢው ብዙ ቀውስ አስከትሏል፡፡ ማን ገደላቸው የሚለው ለብዙ መላምት በር ከፍቷል፡፡

በመጨረሻም አራት ሰዎች በሌሉበት ክሳቸው መታየት ጀምሮ ከተራዘመ ሂደት በኋላ ዛሬ ፍርድ ያገኛሉ፡፡

ሐሪሪ የተገደሉት እንደ አውሮጳዊያኑ በ2005 ዓ.ም ነበር፣ ከ15 ዓመት በፊት ነበር፡፡

ተጠርጣሪዎቹ የሊባኖስ የሺኣ ታጣቂ ክንፍ አባላት ናቸው፡፡

የሐሪሪን ሞት ተከትሎ ቁጣ በመቀስቀሱ ሶሪያ በሊባኖስ ለ29 ዓመታት ያሰፈረችውን ጦር እንድታስወጣ ምክንያት ሆኗል፡፡

ሐሪሪ ከሞታቸው ቀደም ብሎ ሶሪያ ጦሯን ከሊባኖስ እንድታስወጣ በተደጋጋሚ ይጠይቁ ነበር፡፡

ጉልበተኛው የጦር ክንፍ ሒዝቦላም ሆነ የበሽር አል አሳዷ ሶሪያ በሐረሪ ሞት እጃችን የለበትም ይላሉ፡፡

ራፊቅ ሐሪሪ የተገደሉት እሳቸውን የያዘው መኪና በሚያልፍበት ጎዳና ተቀጣጣይ ፈንጂ በተጠመደበት ሚኒባስ እንዲፈነዳ በመደረጉ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሞቱበት አደጋ 220 ተጨማሪ ሰዎች ከባድና ቀላል የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸዋል፡፡ ፍንዳታው በጣም ከፍተኛ እንደነበረም ይነገራል፡፡

የርሳቸው መገደል የሊባኖስን ፖለቲካ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ለውጦታል፡፡ ተገዳዳሪ ኃይሎች እንዲነሱም ምክንያት ሆኗል፡፡

የራፊቅ ሐሪሪ ልጅ ሰአድ ሐሪሪ ያን ጊዜ የጸረ ሶሪያ አቋም ይዞ የምዕራባዊያንን ድጋፍ በማግኘቱ ለሦስት ተከታታይ የግዛት ዘመን የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሆን ችሏል፡፡

በዚህ የፍርድ አሰጣጥ ሂደት ሰአድ ሐሪሪ ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የሊባኖስን ጉዳይ የሚመለከተው ልዩ የፍርድ ሸንጎ የተቋቋመው በኔዘርላንድስ ከሄግ በቅርብ ርቀት በምትገኝ አንዲት መንደር ውስጥ ነው፡፡

የሐሪሪን ግድያ አቀነባብረዋል ተብለው የተጠረጠሩት አራቱ ሰዎች እስከዛሬ የት እንዳሉ አይታወቅም፡፡

ሐሪሪ በሊባኖስ ውስጥ ትልቅ ስም የነበራቸው የሱኒ ፖለቲከኛና ቢሊየነር ነበሩ፡፡

በቀብራቸው ሥነ ሥርዓት በሺዎች የተገኙ የነበረ ሲሆን ሞታቸውን ተከትሎ ሚሊዮኖች አደባባይ ወጥተው የሶሪያ ጦር ሊባኖስን በአስቸኳይ ለቆ እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡

ይህ 15 ዓመታትን የወሰደው የፍርድ ሂደት መጨረሻ የሚሰማው ሊባኖስ የቤይሩት ወደቡ ፍንዳታ ቁስል ባልጠገገላትት ወቅት መሆኑ አነጋግሯል፡፡

ለበርካታ የአካባቢው ፖለቲካ ተንታኞች የሊባኖስ ቀጣይ እጣ ፈንታ ፈተኝና መላቅጡ የጠፋበት ሆኖ ይታያቸዋል፡፡