የቫይረሱ መነሻ የሆነችው ዉሃን ወደ ቀደመ ድምቀቷ ተመለሰች

ዉሃን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በቻይናዋ ዉሃን በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ትከሻ ለትከሻ ተደጋግፈው፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ሳያደርጉ በውሃ ላይ መንሳፈፊያዎች ላይ ሆነው በሙዚቃ ድግስ ሃሴት ሲኣደርጉ ታይተዋል።

ይህ የሆነው ባሳለፍነው ቅዳሜ እና እሁድ የኮሮናቫይረስ መነሻ እንደሆነች በምትታመነው ዉሃን ከተማ ነው።

በዉሃን ማያ ባህር ዳርቻ የውሃ ፓርክ የታየው ይህ ትዕይንት ሌላው ዓለም በበሽታው ፍዳውን እያየ እርሷ ግን ሙሉ ለሙሉ ከበሽታው የተላቀቀች አስመስሏታል። ይህም በርካቶችን አነጋግሯል።

ጥር ወር ላይ በወረርሽኙ ሳቢያ የእንቅስቃሴ ገደብ ጥላ የነበረችው ከተማዋ፣ ጭርታዋ ሰው የሚኖርበት ከተማ አትመስልም ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የእንቅስቃሴ ገደቡ የተነሳው ሚያዚያ ወር ላይ ሲሆን ከግንቦት ወር አጋማሽ ጀምሮ በሁቤ ግዛትም ሆነ በከተማዋ ዉሃን ከሕብረተሰቡ ውስጥ በቫይረሱ የተያዘ ሰው አልተገኘም።

በከተማዋ ለወራት ተጥሎ የቆየው የእንቅስቃሴ ገደብ መላላት ሲጀምር የገበያ ቦታዎችና የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት ጀመሩ። ሰዎችም ቀስ በቀስ ወደ እንቅስቃሴ ተመለሱ፤ ይሁን አንጂ አሁንም አካላዊ ርቀትን መጠበቅና የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ ግድ ነው።

ሚያዚያ ወር መጀመሪያ ላይ የእንቅስቃሴ ገደቡ በተነሳበት ወቅት የሰርጋቸውን ቀን አራዝመው የነበሩ ጥንዶችም ለሰርጋቸው መጣደፍ ያዙ።

ቀስ በቀስ ትምህርት ቤቶችም ተከፈቱ። ሕይወትም ወደ ቀደመው መልኳ መመለስ ጀመረች።

ይሁን እንጂ ግንቦት ወር ላይ ስድስት ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው መረጋገጡን ተከትሎ ከተማዋ ሁሉንም ሕዝቦቿን ለመመርመር እቅድ ያዘች።

በቅርቡም ቫይረሱን ተቆጣጠረች።

ሰኔ ወር ላይ ፊልም ማሳያ ቤቶች፣ የምሽት ገበያ ቦታዎች ፣ ፓርኮች፣ ቤተ-መፅሐፍትና ሙዚየሞች በተወሰነ መልኩ እንዲከፈቱ ተደረገ። ትልቅ ስብሰባዎችን ለማካሄድም ፈቃድ ተሰጠ።

ዉሃን የቀደመው ሕይወቷን መልክ እየያዘች መጣች።

ዛሬ ሕዝቦቿ በፓርኮች በብዛት ተሰባስበው ለመዝናናት በቅተዋል።

የውሃ ፓርኩ ምክትል ሥራ አስኪያጅ በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት 15 ሺህ የሚጠጉ ጎብኝዎች እንደነበሩ ተናግረው፤ ይህ ቁጥር በባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ግማሽ ነበር ብለዋል።

የቻይና ማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች በከተማ በዚህ መልኩ በርካቶች እንዲሰባሰቡ መፈቀዱን አድንቀዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ይህ አደገኛ ነው ሊታሰብብት ይገባል ያሉም አሉ።

በዉሃን ከግንቦት ወር አጋማሽ ጀምሮ በሕብረተሰቡ ውስጥ በኮሮናቫይረስ የተያዘ ሰው አልተመዘገበም።

ከተማዋም 9.9 ሚሊየን የሚሆኑ ሕዝቦቿን መርምራለች።

ባለሙያዎች ግን አሁንም በከተማዋ በቫይረሱ የተያዘ ሰው ባይኖርም፤ ከውጪ ሊገባ ይችላል፤ በመሆኑም በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች አንድ ላይ መሰባሰባቸው አደገኛ ነው ሲሉ እያስጠነቀቁ ነው።