አዲስ አበባ፡ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ሆነው ተመረጡ

ወ/ሮ አዳነች አቤቤ
የምስሉ መግለጫ,

ወ/ሮ አዳነች አቤቤ

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የኢፌድሪ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ የነበሩትን ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አድርጎ ሾሟል።

ወ/ሮ አዳነች የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አባል ስላልሆኑ ነው ምክትል ከንቲባ በመሆን የከንቲባ ኃላፊነትን የሚወጡት።

ወ/ሮ አዳነች፤ ከ85 የምክር ቤት አባላት በ77 ድጋፍ በ6 ተቃውሞ እና በ2 ድምጸ ተዐቅቦ ሹመታቸው በአዲስ አበባ ምክር ቤት ጸድቋል።

የቀድሞ ምክትል ከንቲባ ኢ/ር ታከለ ኡማ የማዕድን እና ኢነርጂ ሚንስትር ሆነው መሾማቸው ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በዛሬው ዕለት አዳዲስ ሹመቶችን መስጠታቸው ይታወሳል። ከሰሞኑ ከኦሮሚያ የብልፅግና ፓርቲ ማዕከላዊ አባልነታቸው የታገዱት አቶ ለማ መገርሳ ከመከላከያ ሚነስትርነታቸው ተነስተዋል።

በአቶ ለማ ምትክ ቀንዓ ያደታ (ዶ/ር) የመከላከያ ሚንስትር ሆነው መሾማቸውን ከጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ፌስቡክ ገፅ ከሰፈረው መረጃ መረዳት ተችሏል።

ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ወደ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ካቢኔ የመጡት የገቢዎች ሚኒስትር መሆን ነበር። ከዚያም የሃገሪቱ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ በመሆን አገልግለዋል።

ወ/ሮ አዳነች ወደ ሚኒስትርነት ቦታ ከመምጣታቸው በፊት የአዳማ ከንቲባ እንዲሁም የኦዴፓ ማዕከላዊ ፅህፈት ቤት ኃላፊ ሆነው አገልግለዋል።