ሊባኖስ፡ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ሐሪሪን በመግደል ከተጠረጠሩት አንደኛው ጥፋተኛ ተባለ

ሃሪሪ ግድያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የሊባኖስን የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስተር በመግደል ከተጠረጠሩት መካከል አንደኛው ጥፋተኛ ተባለ።

ከ15 ዓመታት በፊት በቤይሩት የቀድሞ የሌባኖስ ጠቅላይ ሚኒስትርን በመግደል ከተጠረጡ አራት ግለሰቦች አንዱ ጥፋተኛ ሆኖ ተገኘ።

የሺያ ታጣቂ ቡድን ክንፍ የሆነው ሄዝቦላ አባል የሆኑት ሳሊም አያሽ እና ሌሎች ከ6 ዓመታት በፊት አንስቶ ጉዳያቸው በሌሉበት ሲታይ ቆይቶ ዛሬ ፍርድ አግኝቷል።

በሱኒ ሙስሊሞች ዘንድ ዝነኛ የነበሩት የፖለቲከኛው ራፊቅ ሐሪሪ ግድያ በአገሪቷ ከፍተኛ ቀውስ አስከትሎ ነበር።

ዛሬ ፍርዱ የተሰማው ሊባኖስ በኢኮኖሚ እና ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ ባለችበት ወቅት ነው።

ሳሊም አያሽ የተባለው ግለሰብ ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘው ከ15 ዓመታት በፊት በፈረንጆቹ የካቲት 14 በመኪና ላይ ቦምብ በማጥመድ፤ የሽብር ጥቃት በመፈፀም፣ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩን በመግደል እና ለ21 ሰዎች ሞት እና ከ226 ሰዎች በላይ ጉዳት ማድረስ በሚል ነው።

ዳኛው የሄዝቦላህ ከፍተኛ አመራሮችም ሆነ ለሄዝቦላ የፍይናንስ ድጋፍ የሚያደርገው የሶሪያ መንግሥት በግድያው ተሳትፎ እንዳላቸው የሚያረጋግጥ ማስረጃ አልተገኘም ብለዋል።

ሄዝቦላህ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ በጠቅላይ ሚንስትሩ ግድያ እጄ የለበትም ሲል በተደጋጋሚ አስተባብሏል።