አሜሪካ፡ ሰባት ጥይት የተተኮሰበት ጃኮብ ከእንግዲህ ቆሞ መራመድ አይችልም ተባለ

የ29 ዓመቱ ጃኮብ

የፎቶው ባለመብት, BENCRUMP.COM

የጃኮብ ቤተሰብ ጠበቃ፤ ጃኮብ ሕይወቱ ብትተርፍ እንኳን ከእንግዲህ ቆሞ ለመራመድ ተአምር ይጠበቃል ብለዋል፡፡

የ29 ዓመቱ ጃኮብ በዊስኮንሲን ግዛት ኬኔሾ ከተማ ወደ መኪናው በር ከፍቶ ሲገባ ከኋላ በቅርብ ርቀት በፖሊስ ጥይት ተተኩሶበት ነበር ለዚህ ጉዳት የተዳረገው፡፡

በጃኮብ ላይ ከተተኮሱበት ጥይቶች አንደኛዋ አከርካሪው ላይ ሳትሰነቀር አልቀረችም፡፡

የጃኮብን ጉዳት ተከትሎ በአንዳንድ ከተሞች ላይ ቁጣ ተቀስቅሷል፡፡

የዊስኮንሲን አገረ ገዥ ወደ ኬኖሻ ልዩ ኃይል (ናሽናል ጋርድ) እንዲገባ አድርገዋል፡፡

ጃኮብ በፖሊስ በዚያ ሁኔታና ቅርበት ሲተኮስበት ትንሽ ልጁ መኪና ውስጥ ቁጭ ብሎ እየተመለከተ መሆኑ የብዙዎችን ስሜት የጎዳ ሆኗል፡፡

ጃኮብ ሽባ መሆኑ አይቀርም ከመባሉ ባሻገር ሌሎች ጥይቶቹ ኩላሊቱን፣ ሆዱን እና ጉበቱን ጎድተውታል፡፡ ትንሽ አንጀቱና ደንዳኔው ከጥቅም ውጭ በመሆኑ መውጣት ይኖርበታል ብለዋል፣ ሐኪሞቹ፡፡

እናቱ ጁሊያ ጃክሰን ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ልጃቸው ጃኮብ ‹በነፍስ ውጪ፣ ነፍስ ግቢ ሁኔታ ላይ ነው ያለው፡፡ ሆኖም አሁን የሱን ጥቃት ተከትሎ ወጣቶች ውንብድናና አላስፈላጊ ጥፋት እያደረሱ መሆኑን ቢያውቅ ደስ ይለዋል ብዬ አልገምትም› ብለዋል፡፡

መቶ ሺህ ሰዎች በሚኖሩባት ከተማ በተነሳው ብጥብጥ በርካታ መኪናዎች ወድመዋል፤ ሕንጻዎችም በእሳት ተያይዘዋል፡፡ ተቃውሞው ላለፉት ሁለት ቀናት ሳይቋረጥ ቀጥሏል፡፡

አገረ ገዥው ቶኒ ኤቨርስ ተጨማሪ ልዩ ኃይል አባላትን ወደ ኬኖሻ እንደሚያስገቡ ተናግረዋል፡፡ የእሳት አደጋ ተከላካዮችም በብዛት ገብተዋል፡፡ ይህም በይበልጥ የመንግሥት ንብረቶችንና ሕንጻዎችን ለመከላከል ነው፡፡

በዊስኮንሰን ግዛት በአሁኑ ጊዜ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል፡፡

ጆርጅ ፍሎይድ ባለፈው ግንቦት ወር በሚኒሶታ በነጭ ፖሎስ ማጅራቱ ታንቆ መገደሉ ዓለም አቀፍ ተቃውሞ ቀስቅሶ እንደበር አይዘነጋም፡፡