ሰሜን ኮሪያ፡ ታመዋል ሲባሉ የነበሩት የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ድንገት ተከሰቱ

የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ታመዋል ከሚለው ጀምሮ፣ አብቅቶላቸዋል፣ ሞተዋል እየተባለም ብዙ ይወራባቸው ነበር፡፡

ድንገት በፓርቲ ስብሰባ ተከስተው መመርያ ሰጥተዋል፣ ትናንት፡፡

ሰሜን ኮሪያ ትልቅ አደጋ ከፊቷ ተደቅኗል ያሉት ኪም ሕዝቡ በተጠንቀቅ እንዲሆን አዘዋል፡፡ ትልቅ አደጋ እየመጣ ነው ያሉት ኪም አደጋዎቹ በዋናነት ሁለት መሆናቸውን አውስተዋል፡፡

አንዱ ኮሮና ቫይረስ ሲሆን ሌላው ደግሞ አውሎ ንፋስ ነው፡፡

ኪም ከሰሞኑ ጠፍተው ስለነበር የጤናቸው ሁኔታ አሳሳቢ ስለነበረ ምናልባት ሞተው ይሆን? ሲባል ነበር፡፡

ሰሜን ኮሪያ እስካሁን አንድም ሰው በኮቪድ-19 አልተያዘብኝም ስትል ታስተባብላለች፡፡ አይበለውና ወረርሽኙ ወደዚያች አገር ቢገባ ባላት ደካማ የጤና መሰረተ ልማት ከፍተኛ አደጋ ሊያጋጥማት ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሯል፡፡

ይህ በእንዲህ ሳለ ባቪ የሚሰኝ አደገኛ አውሎ ነፋስ በዚህ ሳምንት መጨረሻ ሰሜን ኮሪያን ሊመታት ይችላል ተብሎ ተሰግቷል፡፡

የፖሊትቢሮ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት ኪም በስብሰባው ላይ ንግግር እያደረጉ ሲያጨሱ ይታዩ ነበር፡፡

በዚህ ንግግራቸው ኮቪድን በተመለከተ አንዳንድ ችግሮች ተስተውለዋል ብለዋል፡፡ ምን ማለታቸው እንደሆነ ግን የሚያውቅ አልተገኘም፡፡

ፒዮንግያንግ ለረዥም ጊዜ ወረርሽኙ እኔ ጋ ድርሽ አላለም ስትል እያስተባበለች ቆይታለች፡፡ ነገር ግን ይህን የሰሜን ኮሪያን አስተያየት ብዙዎች በጥርጣሬ ነው የሚመለከቱት፡፡

አንድም በቫይረሱ የተጠቃ ሰው የለም ስትል የነበረው ሰሜን ኮሪያ በቫይረሱ አጠባበቅ ዙርያ ችግሮች ታይተዋል ማለቷ ብዙዎችን ግራ አጋብቷል፡፡

ሰሜን ኮሪያ ከጥርጣሬ የተነሳ አንዲት የድንበር ከተማ ሰዎች ተገለው እንዲቀመጡ ያደረገች ሲሆን ነገር ግን ከዚህ የዘለለ ስለተያዘ አንድም ሰው ተጠቅሶ አያውቅም፡፡

ኪም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ክብደት እየጨመሩ ስለሆነ በወጣትነታቸው ሊቀጠፉ ይችላሉ የሚሉ ስጋቶች በስፋት ይሰነዘሩ ነበር፡፡ በቅርቡም ለእህታቸው ኪም ዮ ጆንግ በርከት ያሉ ሥልጣኖችን ሰጥተዋት ነበር፡፡

ይህንን ሁኔታ እንደ ኑዛዜ የወሰዱት ሚዲያዎችም ነበሩ፡፡

ሰሜን ኮሪያ 25 ሚሊዮን ዜጎች አሏት፡፡

10 ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎቿ የረሀብ አደጋ ገጥሟቸዋል ይላል የተባበሩት መንግሥታት፡፡

የረባ የንግድ ግንኙነት ከአገራት ጋር ያልመሰረተችው ሰሜን ኮሪያ ከቻይና ጋር የምታደርገው ንግድ ወሳኝ ተደርጎ ይታሰባል፡፡ ይህም በኮሮና ምክንያት እክል ገጥሞታል፡፡

በፒዮንግያንግ መቀመጫቸውን ያደረጉ በርካታ ግብረሰናይ ድርጅቶችና የኤምባሲ ሰራተኞች አገሪቱን ለቀው እንደወጡ ተዘግቧል፡፡