ኢትዮጵያ፡ የ2013 የትምህርት ዘመንን ለማስጀመር ምን እየተሰራ ነው?

ተማሪዎች በትምህርት ላይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በ2013 የትምህርት ዘመን ተማሪዎች ለኮቪድ-19 እንዳይጋለጡ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

የትምህርት ሚኒስቴር ኮሙኑኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሐረግ ማሞ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ትምህርት ከመጀመሩ በፊት እንዴት ይጀመር ተብሎ ሲታሰብ ከግምት ውስጥ ከገቡ ጉዳዩች አንዱ ለተማሪዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማቅረብ፣ የክፍል ውስጥ ጥግግትን ለማስቀረት ትምህርት በፈረቃ ይሁን አይሁን የሚሉት ናቸው።

የሚኒስቴሩ የኮሙኑኬሽን ዳይሬክተር ለቢቢሲ እንደገለፁት፣ አንድ ትምህርት ቤት የኮሮናቫይረስን ከመከላከል አንጻር ምን ማድረግ አለበት የሚለውን በተመለከተ ትምህርት ሚኒስቴር ሲያስብ የተማሪዎች በአንድ ክፍል ውስጥ ያላቸው ቁጥር አንዱ ነው።

ትምህርት ሚኒስቴር "ትምህርት በፈረቃ ይሁን አይሁን፣ ተማሪዎችን እንዴት አድርገን አራርቀን እናስቀምጥ" የሚሉና የተማሪዎች ጤንነት መጠበቂያ መሳሪያዎችን በተመለከተ ምን መደረግ እንዳለባቸው የት መቀመጥ እንዳለባቸውና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ውይይት እየተደረገ መሆኑን ጨምረው ገልፀዋል።

ትምህርት ሚኒስቴር መጪው ዓመት የትምህርት ዘመን ሲጀምር ምን መደረግ አለበት የሚለውን ከጤና ሚኒስቴርና ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በመሆን እየሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ከኮሮናቫይረስ መከላከያ መንገዶች አንዱ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ በመሆኑ ምን ማድረግ አለብን የሚለውን ትምህርት ሚኒስቴር ከሚመለከታቸው የባለድርሻ አካላት ጋር እየተነጋገረ መሆኑን ኃላፊዋ ገልፀዋል።

ትምህርት ከመጀመሩ በፊት ለትምህርት ማህበረሰቡ አጠቃላይ፣ መረጃ እንደሚሰጥ የገለፁት የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተሯ፣ ይህንን ጨምሮ ሌሎች ጉዳዮችን በተመለከተ እንደሚያሳውቁ ገልፀዋል።

የትምህርት ሚኒስቴሩ በትናንትናው ዕለት ከአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኀን ጋር በነበራቸው ቆይታ ወደ መማር ማስተማር ተግባር በሚገባበት ወቅት ለተማሪዎች ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር እንደሚሠራ ገልጸው፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ፣ የእጅ ማፅጃ እና መሰል አቅርቦቶችን ከባላድርሻ አካላት ጋር በመሆን ለማቅረብ በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ተናግረው ነበር።

የሚኒስቴሩ ኮሙኑኬሽን ዳይሬክተር በበኩላቸው ለቢቢሲ እንደገለፁት ይህንን ታሳቢ በማድረግ ውይይት እና ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

ኃላፊዋ ትምህርት ሚኒስቴር እስካሁን ድረስ የ2013 የትምህርት ዘመን መቼ እንደሚጀመር አለመወሰኑን በመግለጽ ትምህርት የሚጀመርበትን ወቅት ለማሳወቅ "የስርጭቱ መጠንና የመንግሥት ውሳኔ ይወስነዋል" ሲሉ ገልፀዋል።

ትምህርት ቤቶች ምዝገባ በሚያካሄዱበት ወቅት የኮሮናቫይረስ ስርጭት እንዳይከሰት ተማሪዎች፣ መምህራንና ወላጆች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ፣ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ እና እጅን በመታጠብ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚኖርባቸው ወ/ሮ ሐረግ ማሞ ጨምረው ገልፀዋል።

የተማሪዎች ምዝገባው እስከ መቼ ድረስ ይካሄዳል ለሚለው የቢቢሲ ጥያቄ ኃላፊዋ ሲመልሱ፣ እንደ ትምህርት ቤቶቹ ተጨባጭ ሁናቴ የሚወሰን መሆኑን ገልፀዋል።

በትምህርት ቤቶች ውስጥ ከምዝገባ ጀምሮ የኮቪድ-19 በመከላከል ረገድ ኃላፊነቱ የሁሉም ነው ያሉት ወ/ሮ ሐረግ "ተማሪዎች፣ ወላጆች፣ የትምህርት ማህበረሰቡ ኃላፊነት አለበት" በማለት "በተለይ ደግሞ በትልቁ መምህራን ኃላፊነት አለባቸው" ሲሉ ተናግረዋል።

እንዲሁም መምህራንን ተማሪዎች እንደ ወላጅ ስለሚመለከቷቸው መምህራን ተማሪዎቻቸውን ከኮሮና ራቸውን እንዲከላከሉ በማድረግ ረገድ " እጥፍ ድርብ ኃላፊነት አለባቸው" ብለዋል።

በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በኮሮና ወረርሽኝ ከተከሰተ ወዲህ በለይቶ ማቆያነት ያገለገሉ እንዲሁም በአገሪቱ ውስጥ በተከሰቱ አለመረጋጋቶች የተለያዩ አገልግሎት የሰጡ ትምህርት ቤቶች ምዝገባ ከመጀመራቸው በፊት በሚገባ መጽዳት እንዳለባቸውና ትምህርት ቤቶችም ይህንን ማረጋገጥ እንዳለባቸው በመግለጽ፣ የምዝገባ ጊዜው ሰፋ የተደረገው ይህንን ታሳቢ በማድረግ መሆንም ለቢቢሲ ጨምረው አስረድተዋል።

ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ እስከ 12ኛ ክፍል ላሉት ተማሪዎች በ2012 የትምህርት ዘመን በ2ኛ ሴሚስተር ያለፋቸውን ትምህርቶች ማካካሻ ለመስጠት መታሰቡንም ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ ትናንት ከአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኀን ጋር በነበራቸው ቆይታ ወቅት መግለፃቸው ይታወሳል።

በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰቱ ከታወቀ ወዲህ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት በሚል ከመጋቢት ሰባት 2012 ዓ.ም ጀምሮ ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸው ይታወሳል።

ትምህርት ሚኒስቴር ከስምንተኛ ክፍል እና የ12 ክፈል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና ወሳጆች ውጪ ቀሪዎቹ ተማሪዎች በግማሽ ዓመት ውጤታቸው ወደ ቀጣዩ ክፍል እንዲዛወሩ መወሰኑ ይታወቃል።

እስካሁን ድረስ የስምንተኛም ሆነ የ12 ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና መቼ እንደሚካሄድ አልታወቀም።