የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ጉዳት ለደረሰባቸው ከ12 ሺህ በላይ ቤተሰቦች የገንዘብ ድጋፍ አደረገች

አቡነ ማትያስ

የፎቶው ባለመብት, Anadolu Agency

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን የሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ በተከሰተው አለመረጋጋት በአስር አገረ ስብከት ለተጎዱ ምዕመኖቿ የ40 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገች።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎችን መልሶ ለማቋቋም በሚል የተደራጀው ኮሚቴ አባል የሆኑት ቀሲስ ሙሉቀን ብርሃኑ ለቢቢሲ እንዳሉት እርዳታው በአስሩ አገረ ስብከት የሚገኙ 2170 አባወራዎች፣ ወይንም 12 ሺህ 719 ቤተሰብ አባላትን ተጠቃሚ ያደርጋል።

ለግለሰቦቹ በዚህ ወቅት ድጋፍ ማድረግ ያስፈለገበትን ምክንያት ሲገልፁም በዚህ ሳምነት አርብ ለሚለው በዓል እንዲሁም ተመልሰው ወደ ሥራ መግባት የሚችሉ ከሆነ እንዲገቡ በሚል በአስቸኳይ ወጪ ተደርጎ መሰጠቱን ተናግረዋል።

እነዚህን የተለያየ ጉዳት የደረሰባቸውን ግለሰቦች ለመደገፍ በአጠቃላይ 44.5 ሚሊየን ብር ከቤተክርስቲያኒቱ ካዝና መውጣቱን እንዲሁም ከምዕመናን በልግስና መሰብሰቡን ገልፀዋል።

በአሁኑ ሰዓት ከተሰጠው 40 ሚሊዮን ብር ቀሪው 4.5 ሚሊየን ብር በመረጃ ክፍተት ምክንያት የተዘለሉ ግለሰቦች ካሉ ለመጠባበቂያ መቀመጡን ተናግረዋል።

እርዳታው ለግለሰቦቹ የተሰጠው እንደ የጉዳት መጠናቸው መሆኑን የተናገሩት ቀሲስ ሙሉቀን፣ ሞት የገጠማቸው፣ ቋሚ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው፣ በሕክምና ሊመለስ የሚችል ጉዳት የደረሰባቸው በሚል መለየታቸውን ተናግረዋል።

አክለውም ድጋፉ በባለሙያ የተሰላው ቤተሰቡ እንዳጋጠመው ጉዳት መጠን መሆኑን በመግለጽ ሙሉ በሙሉ የወደመባቸው፣ በከፊል እንዲሁም መለስተኛ ጉዳት ንብረታቸው ላይ የደረሰው ተለይተው ድጋፉ ተሰልቷል ብለዋል።

ጉዳት የደረሰባቸው ግለሰቦች ዝርዝር መረጃ እና አድራሻ ተይዞ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በመነጋገር የቁጠባ ሒሳብ በስማቸው በመክፈት የገንዘብ ድጋፉ በቀጥታ ገቢ መደረጉንም ተናግረዋል።

እነዚህ አስር አገረ ስብከቶች የሚገኙት በምዕራብ እና ምሥራቅ አርሲ፣ በምዕራብና ምሥራቅ ሐረርጌ፣ ባሌ፣ ምሥራቅ ሸዋ፣ ኢሉአባቦራ ፣ ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ እንዲሁም ጅማ መሆኑን ገልፀዋል።

ይህ ድጋፍ የመጀመሪያ ዙር መሆኑን የገለፁት ቀሲስ ሙሉቀን፤ በቀጣይ ሌሎች ጉዳት የደረሰባቸው አገረ ስብከቶች ላይም ጥናት እየተሰራ በመሆኑ ድጋፍ እንደሚደረግ ገልፀዋል።

በአሁኑ ወቅት በጥናት ላይ ያሉ የአገረ ስብከቶች ከጉጂ እንዲሁም ከመተከል አገረ ስብከቶች ላይ የመጡ መረጃዎች መሆናቸውን ጨምረው አስረድተዋል።

እነዚህን ሰዎች በዘላቂነት ለማቋቋም፣ የጠፋባቸውን ንብረት ለመመለስ፣ የወደመባቸውን ቤት በነበረበት ይዘት ለመመለስ የ3 ቢሊዮን ብር ድጋፍ ለማሰባሰብ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑንም አክለዋል።

ቤተክርስቲያኒቱ በእምነታቸው ምክንያት ከጥቅምት እስከ ሰኔ ወር ድረስ በተለያዩ ስፍራዎች ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ለማቋቋም መወሰኗን ቀሲስ ሙሉቀን ጠቅሰዋል።

በቀጣይም የእምነቱ ተከታይ በመሆናቸው ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች፣ "ከየትኛውም አገረ ስብከት መረጃውና ማስረጃው እስከመጣ ድረስ ኮሚቴው የማቋቋም ሥራ" እንደሚሰራ ተናግረዋል።