የኤርትራ መንግሥት በሃይማኖታቸው ምክንያት ያሰራቸውን 20 ያህል ግለሰቦች ለቀቀ

ከርቸሌ

የኤርትራ መንግሥት በእምነታቸው ምክንያት ለዓመታት አስሯቸው የነበሩ ከ20 በላይ ግለሰቦችን መለቀቁን የተለያዩ ምንጮች ለቢቢሲ ገለፁ።

ታሳሪዎቹ አብዛኞቹ ከወንጌላውያን እና ጴንጤቆስጣል ቤተ እምነቶች እንደነበሩ ጨምረው አረጋግጠዋል።

ከእነዚህ ግለሰቦች መካከል የተወሰኑትም ከአስመራ ውጪ ታስረው መቆየታቸው ቢቢሲ ያገኘው መረጃ ያሳያል።

ኑሮው በአሜሪካ የሆነው እና በኤርትራ ስላለ የእምነት ነጻነት የሚከራከረው ሃኒባል ዳንኤል እንደሚለው ከሆነ ከእስር ከተለቀቁት ግለሰቦች መካከል ለ16 ዓመታት ታስረው የቆዩ ይገኙበታል።

የኤርትራ መንግሥት በይፋ ስለ እስረኞቹ መለቀቅ ያለው ነገር የለም።

ቢቢሲ ኤርትራ ውስጥ ካሉ ምንጮች እንዳጣራው ግለሰቦቹ የዋስትና መብታቸው ተጠብቆላቸው ነው የተለቀቁት።

ለዋስትና ማስያዣነት የተጠየቀው የቤት ባለቤትነት ወይንም የንግድ ፈቃድ መሆኑንም ምንጮቻችን ጨምረው ገልፀዋል።

የእምነት ነጻነት እንዲኖር የሚሰሩ አካላት በበኩላቸው በኤርትራ ሶስት የይሖዋ እምነት ምስክር አባላት ከ25 ዓመት በላይ በእስር ላይ እንዳሉ ይናገራሉ።

እንደ ሃኒባል ከሆነ ለእስረኞቹ መፈታት ምክንያት ሊሆን የሚችለው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭት ይሆናል ሲል ግምቱን ሰጥቷል።

በኤርትራ መንግሥት እውቅና ያላቸው የኦርቶዶክስ ክርስትና፣ ካቶሊክ፣ ሉትራን እና እስልምና ሃይማኖቶች ብቻ ናቸው።

እኤአ ከ2002 ጀምሮ ከእነዚህ ሃይማኖቶች ውጪ ያሉ በአጠቃላይ እምነታቸውን በይፋ ለማካሄድ ህጋዊ እውቅና ተነፍገዋል።

የኤርትራ መንግሥት በ1994 ላይ የጴንጤቆስጤ አብያተ ክርስትያናትን ሙሉ በሙሉ መዝጋቱ ይታወሳል።

በዚህም የተነሳ ለአምልኮ ስርዓት ወይንም የተለያዩ ማህበራዊ ህይወቶቻቸውን ተሰባስቦ ማከናወን መከልከላቸውን የዓለም አቀፍ ሃይማኖቶች ነጻነት ላይ የሚሰራው የአሜሪካው ተቋም፣ USCIRF ገልጿል።

የኤርትራ መንግሥት በአገሪቱ አለ ስለሚባለው የሃይማኖት ነጻነት ጥሰት ውንጀላ ያስተባብላል።

የአሜሪካ ውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት በኤርትራ 1,200 እስከ 3,000 የሚሆኑ ሰዎች በእምነታቸው የተነሳ መታሰራቸውን ይገምታል።

የሰብዓዊ መብት ቡድኖች የኤርትራ መንግሥት በሺህ የሚቆጠሩ ግለሰቦችን በሐይማኖት እና ፖለቲካ ምክንያት አስሯል ሲሉ ይወቅሳሉ።

በጉዳዩ ዙሪያ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የኤርትራ መንግሥትን ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።