የኬንያ ፖሊሶች የደንብ ልብሳችሁን ገዝታችሁ ልበሱ ተባሉ

የኬንያ ፖሊስ

የፎቶው ባለመብት, Consumers Federation of Kenya

በኬንያዋ መዲና የሚገኙ ፖሊሶች የደንብ ልብሳቸውን በራሳቸው ወጪ በመግዛት ላይ ናቸው።

ፖሊሶቹ ከሰኞ ጀምሮ የተቀየረውን የመለዮ ልብስ (ዩኒፎርም) መልበስ እንዳለባቸው የተነገራቸው ሲሆን በገበያውም ላይ የአቅርቦት ችግር እንደተፈጠረም የአገሪቱ ሚዲያዎች ዘግበዋል።

አንዳንድ ፖሊሶች አዲሱን የደንብ ልብስ ሳይለብሱ በቀድሞው መምጣታቸውን ተከትሎ ወደቤታቸው እንዲመለሱ መደረጋቸውንም የአገሪቱ ጋዜጦች ደይሊ ኔሽንና ስታንዳርድ በዘገባቸው አስነብበዋል።

ብሄራዊ የፖሊስ አገልግሎት እንዲሁም የአገር ውስጥ ሚኒስቴር ለሪፖርቱ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

በዘገባው ላይ ዋቢ የተደረጉት ፖሊሶች እንደተናገሩት ልብስ ሰፊዎች ጋር ሄደው እንዲያሰፉ ትዕዛዝ ተሰጥቷቸዋል።

መንግሥት ለአዲሱ ደንብ ልብሳቸው ወጪያቸውን ሳይሸፍን የቀረ ሲሆን ልብስ ሰፊዎቹም ወደ 2 ሺህ ብር ገደማ እንዳስወጣቸውም ደይሊ ኔሽን ዘግቧል።

አዲሱን መመሪያ ተከትሎም አንዳንድ ፖሊሶች የደንብ ልብሱን ለመግዛት አቅም ያጥረናል በሚልም ቤታቸው ቀርተዋል።

አዲሱ ሰማያዊ መለዮ ልብስ ከሁለት አመት በፊት ነበር የፖሊስ እንዲሆን የተወሰነው።