ብልጽግና፡ "የታሰሩ ስላሉ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ተጎድቷል የሚለውን አንቀበልም" ዶ/ር ቢቂላ ሁሪሳ

ዶ/ር ቢቂላ ሁሪሳ

የፎቶው ባለመብት, EPA

በዚህ ሳምንት ማክሰኞ እለት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ተራዝሞ የነበረው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ እንዲካሄድ ወስኗል።

አንዳንድ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ለቢቢሲ በሰጡት ቃል ግን ከወረርሽኙ በላይ፤ በአገሪቷ የሚታየው የፀጥታ ችግር ሳይፈታ ምርጫ ማካሄድ የማይሆን ነው ሲሉ ይናገራሉ።

በብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት የዓለም አቀፍና ሕዝብ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ዶ/ር ቢቂላ ሁሪሳን፤ በእርግጥ የንጹሃን ሰዎች መገደል፣ መፈናቀል፣ ንብረት መውደም እየተሰማበት ባለበት በዚህ ሰዓት ምርጫ ማካሄድ ይቻላል? ስንል ጠይቀናቸው ነበር።

ዶ/ር ቢቂላ፡ በኢትዮጵያ ምርጫ ማድረግና የኢትዮጵያን ከባቢያዊ ሁኔታ ማሻሻል፣ ማዘመን ኢትዮጵያ ውስጥ ረዥም ታሪክ የተጓዘ፣ አንገብጋቢ አገራዊ አጀንዳ መሆኑ ይታወቃል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት በኢትዮጵያ ያለውን ፖለቲካዊ ሁኔታ በአግባቡ መፈተሽና ዘመናዊ እንዲሆን በተለይ ደግሞ አመኔታን ያተረፈ ምርጫን በማካሄድ ተቀባይነትና አመኔታን ያገኘ መንግሥት መመስረት አስፈላጊ ነው የሚለው ጉዳይ የሁሉም ማኅበረሰቡ ጉዳይ መሆኑ ይታወቃል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዛሬ ሁለት ዓመት በበዓለ ሲመታቸው ወቅት ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያን የፖለቲካ ከባቢያዊ ሁኔታን በእጅጉ በማሻሻል ነጻ፣ ዲሞክራሲያዊና ተቀባይነት ያለው ምርጫ በማካሄድ በኢትዮጵያ ዘመናዊ የፖለቲካ ሥርዓት እንገነባለን ብለው ነበር።

ይንን ተከትሎ ባለፉት ሁለት ዓመታት የተደረጉ ድርጊቶችና የተወሰኑ ውሳኔዎች እጅግ በጣም ወሳኝ ናቸው ብለን ነው የምናምነው።

አንደኛ ለዘመናት በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ መብረር እንኳ የማይችሉ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሁም ደግሞ በከፍተኛ ሁኔታ በፖለቲካ ምክንያት ብቻ እስር ቤት የነበሩ ሰዎች እንዲለቀቁ ተደርገዋል።

በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከውጪ አገር ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ ተደርገዋል። እኔ እስከማስታውሰው ድረስ በውጪ አገር የቀረ የፖለቲካ ፓርቲ የለም።

የሚዲያ ከባቢው እንዲሰፋ፣ ተዘግተው የነበሩ ድረገጾች እንዲከፈቱ እንዲሁም ደግሞ የአገር ውስጥ ሚዲያዎች በነጻነት እንዲሰሩ የሲቪል ሶሳይቲ ሕጉም እንዲሻሻልና . . .

ቢቢሲ፡ [በማቋረጥ] እነዚህ ነገሮች በተደጋጋሚ ሲገለፁ ነው የቆዩት። ጥያቄው አሁን ያለው ነባራዊ ሁኔታ ምርጫ ለማድረግ ያስችላል ወይ? ነው።

ዶ/ር ቢቂላ፡ የእኛ አቋም፤ ባለፉት ሁለት ዓመታት የተወሰኑ ውሳኔዎችና የተሄደባቸው ሁኔታዎች የኢትዮጵያን የፖለቲካ መድረክ ወይም ከባቢን አሻሽለውታል ብለን ነው የምናስበው።

ለውጥ በሚመጣበት ወቅት ለውጡ ወደፊት እንዲሄድ የሚፈልግ አካል አለ። ይህ የለውጥ ባህሪ ነው። ለውጡ እንዲሳካና የተፈለገውን አላማ እንዲመታ የሚፈልግ አካል አለ። የዚያኑ ያህል ደግሞ ለውጡ እንዳይሳካና የተፈለገለትን አላማ እንዳይመታ የሚያደርግ አካልም አለ።

ከዚህ ጋር ተያይዞ በአገራችን አሁን የምንመለከተው የግጭት፣ የሰዎች መፈናቀል በየቦታው የጉልበተኝነት ባህሪ እና በተደራጀ ሁኔታ ይህ ለውጥ እንዲቀለበስ የሚያደርግ ኃይል እንቅስቃሴ ነው ብለን ነው የምናምነው።

በመሆኑም በየቦታው የታዩ የሰላም እጦቶች እንዲሁም ደግሞ በሰው ልጆች ላይ እየደረሱ ያሉ ችግሮች፤ ለውጡን የመቀልበስ አላማ አድርገን ስለምንመለከት እርሱን ቦታ ማስያዝ፣ በዚሁ ውስጥ የሚሳተፉ አካላትን በቁጥጥር ስር ማዋልና በሕግ ብቻ እንዲመሩ ማድረግ ያስፈልጋል።

ይህንን የመቆጣጠር ሁኔታ በተለይ ደግሞ ሕግና ሕግን ብቻ የተከተለ፣ የሕግ የበላይነትን ማስከበር ሥራ እንዲሰራ ማድረግ በጣም ወሳኝ ነገር ነው።

ስለዚህም እዚህም እዚያም የሚታይ ችግር አገራችን እንድትቆምና ምርጫ እንዳታካሂድ፣ የመሻገር ሥራ እንዳትሰራ፣ የኢትዮጵያ የምርጫ ፖለቲካ ከባቢ መሻሻል እንዳያሳይ፤ ስለዚህም በየቦታው የሚከሰቱ ግጭቶችን ብቻ ቆመን እያየን እንድንቆዝም ለማድረግ የታሰቡ ናቸው።

ነገር ግን እኛ ከዚህ ባሻገር ለግጭቱ ምክንያት የሆኑ አካላት፣ ይህንን ከጀርባ ሆነው የሚያስተባብሩ፣ የሚያቀናጁ፣ የሚያቅዱና ስፖንሰር የሚያደርጉ አካላትን ሕግ ፊት እንዲቀርቡና የሕግ የበላይነት እንዲከበር በማድረግ በየቦታው ለዚህ አስተዋጽኦ ያደረጉ፤ የብልጽግና አመራርንም ጭምር ካሉ በሕግ እንዲጠየቁ እያደረገ ነው።

በዚህም የሕግ የበላይነት እንዲከበር በማድረግ የአገሪቱ ፖለቲካ በማዘመን ሥራ በማከናወን በሕዝብ ተቀባይነት ያለው መንግሥት እንዲመሰረትና ምርጫ ሕግና ሥርዓቱን ተከትሎ እንዲካሄድ የማድረጉን ተግባር ግን መቀጠል አለብን ብለን ነው የምናስበው።

ስለዚህ እያከናወንን ያለው ሁለት ሥራ ነው ማለት ነው። አንደኛው የሕዝብን ደኅንነትን መጠበቅ፣ ፀጥታን ማስከበር፣ የሕግ የበላይነትን በማስከበር እዚህም እዚያም የሚታዩ የደኅንነት ችግሮችን ፈር ማስያዝ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ እንዲካሄድ ማድረግ ተገቢ ነው ብለን ነው የምናስበው።

ቢቢሲ፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ በእስር ላይ የነበሩ ፖለቲከኞች ከእስር ተለቅቀዋል፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ወደ አገር እንዲገቡ ተደርገዋል። አሁን ላይ ግን ጠንካራ ተፎካካሪ የሚባሉ ፓርቲዎች አመራሮች እስር ላይ ይገኛሉ። አንዳንዶቹ እንደውም እስራቸው ፖለቲካዊ እንደሆነ ይናገራሉ። ይህ ባለበት ሁኔታስ ምን አይነት ምርጫ ነው ማካሄድ የሚቻለው?

ዶ/ር ቢቂላ ቀደም ሲል እንዳልኩት የሁለት ነገሮችን ሚዛን ማስጠበቅ ያስፈልጋል። ይህ በጣም በአቋም የምንናገረው ነገር ነው። አንደኛ በአንድ አገር ውስጥ የፍትህና ሕግ ሥርአቱ መስራት መቻል አለበት። ይህ ማለት ምን ማለት ነው፤ በአንድ አገር ውስጥ ከወንጀል ጋር የተያያዙ፣ ከፍትህ ጋር የተያያዙ፣ ከሕግ የበላይነት ጋር ተያያዙ ነገሮችን የአገሪቱ ሕግ በሚፈቅደው መሰረት ለፍትህ ሥርዓቱ መተው ጥሩ ነው።

ስለዚህ በእያንዳንዷ ነገር የፖለቲካንና የፍትህን፣ የሕግን ጉዳይ እየቀላቀልን አንድ አድርጎ በአንድ ኮሮጆ ከትተን የምንመለከት ከሆነ እጅግ በጣም አስቸጋሪ ነው የሚሆነው። ከዚህ አንጻር ስንመለከተው፤ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ከባቢያዊ ሁኔታ እንዲሻሻል መንግሥት ቁርጠኝነት ነው፤ ገዢው ፓርቲም ቁርጠኛ ነው።

ከዚህ ጋር በተያያዘ በምንም አይነት መንገድ ለሕዝብ የተገባው ቃል አይቀለበስም። ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ለማካሄድ የተቻለውን ሁሉ ያደርጋል።

እዚህ ጉዳይ ውስጥ ግን በሕግ ጉዳያቸው የተያዘ፤ የአገሪቱ የፍትህ ሥርዓት የምጠረጥረው ነገር አለና በፍርድ ቤት አቅርቤ፣ መረጃ አስቀርቤ፣ የተሰራ ወንጀል አለ ያ ወንጀል የሕግ የበላይነት መከበር ስላለበት በሕግ መጠየቅ አለብን ብሎ የፍትህ ሥርዓቱ ሲጠይቅ ይህንን ለፍትህ ሥርዓቱ መተው ያስፈልጋል።

ነገር ግን በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ለሕዝብ የተገባው በአገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የመገንባቱ ነገር እንዴት ይቀጥል የሚለውን ሚዛኑን አስጠብቆ መሄድ ያስፈልጋል።

ከዚህ ውጪ በእያንዳንዷ ነገር የታሰሩ ሰዎች ስላሉ ብለን፤ ምርጫ አይካሄድም ወይንም ቢካሄድም ሕጋዊ አይሆንም ብሎ መናገር በጣም በጣም የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሥርዓት ይጎዳዋል። በዚህ መንገድ መሄድ የለበትም።

ስለዚህ እኛ የፍትህን ጉዳይ ለሕግ ሰዎች፣ ለፍርድ ቤት፣ ለዐቃቤ ሕግ፣ ለፖሊስ ትተን፤ ፊት ለፊታችን ያለውን የሕዝብ ጥያቄ፣ የአገሪቱን ፖለቲካ የማዘመን ጥያቄ፣ ነጻ ፍትሃዊ ምርጫ የማድረግ ጥያቄ እንዴት አድርገን ሚዛኑን አስጠብቀን እናስኪድ የሚለውን መመልከት ይገባል።

ስለዚህ የታሰሩ ሰዎች ስላሉ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ተጎድቷል የሚል በፍፁም እንደ ፓርቲ አንቀበልም፤ እኔም በግሌ አልቀበልም።

ቢቢሲ አገራዊ ምርጫውን ለማካሄድ መንግሥት ምን ያህል ዝግጁ ነው። አገሪቱስ ምን ያህል ዝግጁ ናት?

ዶ/ር ቢቂላ በአጠቃላይ መንግሥት የመንግሥትነት ድርሻ ነው የሚወጣው። . . . የመንግሥትነት ድርሻ ማለት ከፀጥታ ጋር፣ ከሕዝብ ደኅንነት ጋር የተገናኙ የሕዝቡን ሰላም ማስጠበቅ፣ ምርጫ ለማካሄድ የሚሆን የፀጥታና የመረጋጋት ተግባርን ማከናወን የመንግሥት ሥራ ነው።

ከዚህ ጋር በተገናኘ ምርጫን ለማካሄድ የሚሆን ተቋም እንዲቋቋም፣ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ በማድረግ ሂደት ውስጥ የመንግሥት ተቋማት ለዚህ የሚያስፈልገውን ድጋፍ እንዲያደርጉ የማድረግ እንዲሁም ደግሞ ተቋማቱ ነጻና ፍትሃዊ ሆነው እንዲንቀሳቀሱ፣ ሙያዊ ሥራቸውን እንዲሰሩ የማድረግ ሥራ ከመንግሥት ይጠበቃል ብለን ነው የምናምነው።

ስለዚህም መንግሥት ከሌሎች ፓርቲዎች በተለየ ሁኔታ በእጅጉ ትልቅ ኃላፊነት አለበት ብዬ አስባለሁ፤ በዚያም አምናለሁ። ነገር ግን መንግሥት ብቻውን የኢትዮጵያን ፖለቲካ ሥርዓት ያሻሽላል ብዬ አላስብም።

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ እጅግ ብዙ ተዋናዮች ናቸው ያሉት። እነዚህ ተዋናዮች ሁሉ የሚጠበቅባቸውን ግዴታ ከተወጡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሁኔታ ይሻሻላል ብዬ አምናለሁ።

የኢትየዮጵያ ሰማይም ሰላም፣ ዲሞክራሲ፣ ነጻነትና ልማት የነፈሰበት ይሆናል ብዬ አምናለሁ።