ኮሮናቫይረስ፡ በኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች በሦስት ዙር እንዲከፈቱ እንደሚደረግ ተጠቆመ

ተማሪዎች በመማር ላይ

የፎቶው ባለመብት, DEA / C. SAPPA

የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል በዓለም የጤና ድርጅትና በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የተቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎችን በሦስት ሳምንታት ውስጥ ያሟሉ ትምህርት ቤቶች ትምህርት እንዲጀምሩ መወሰኑን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

በዚህም መሠረት ትምህርት ቤቶች ከመከፈታቸው በፊት በጸረ ተህዋስ መድኃኒት እንዲጸዱ ማድረግና የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል፣ የእጅ ማጽጃ ማሟላት እንዲሁም አካላዊ ርቀትን ማስጠበቅ የሚያስችላቸውን ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

በተጨማሪም እንደየ ትምህርት ቤቶቹ ነባራዊ ሁኔታ ትምህርት በፈረቃ እና አንድ ቀን በመዝለል በተራ የማስተማር ሥራቸውን ማከናወን ይችላሉም ተብሏል።

የተማሪዎችን ቁጥር በተመለከተም ሚኒስቴሩ ባስቀመጠው መስፈርት መሰረት በአንድ ክፍል ውስጥ ከ20 እስከ 25 ተማሪዎችን ማስተማር እንደሚቻል ፈቅዷል።

በተጨማሪም በአገሪቱ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች በሦስት ዙር ትምህርት እንዲጀምሩ ሊደረግ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ተቋርጦ የነበረውን ትምህርት ቤቶችን ዳግም መክፈት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት እየተደረገ ባለው ውይይት ላይ ይህ ምክረ ሃሳብ መቅረቡን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጠቁሟል።

ውይይቱ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀን ጨምሮ፣ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊዎችና ሌሎች ሚኒስትሮችም የተገኙ ሲሆን፤ የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁንም በሦስት ዙር የሚከናወነውን ትምህርት የማስጀመር ሂደትን በተመለከተ ምክረ ሐሳባቸውን አቅርበዋል።

በዚህም መስረት በገጠር ወረዳና ቀበሌ ከተሞች የሚገኙ ትምህርት ቤቶች መጀመሪያ በተባለው ዙር ጥቅምት 9/2013 ዓ.ም፣ በሁሉም ዞንና የክልል ከተሞች የሚገኙ ትምህርት ቤቶች በ2ኛው ዙር ጥቅምት 16/2013 እንዲጀምሩ ሃሳብ ቀርቧል።

ከዚህም በተጨማሪ በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ክልል ልዩ ዞን የሚገኙት ደግሞ ትምህርት ሚኒስቴር በሦስተኛ ዙር ብሎ ባስቀመጠው ጥቅምት 30/2013 ዓ.ም ይጀምሩ የሚል ምክረ ሐሳብ ማቅረቡ ተገልጿል።

የብሔራዊ ፈተና የሚወስዱት የ8ኛና የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ሁሉም ለፈተና እንዲቀመጡና የ8ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናም ህዳር 22 እና 23/2013 ዓ.ም እንዲወስዱ ታቅዷል።

ፈተና ላይ መቀመጥ የሚችሉት ተማሪዎች የ7ኛ ክፍልን ተምረው ያጠናቀቁና የ8ኛ ክፍል አንደኛ መንፈቀ ዓመት ትምህርትንም የተከታተሉ ሊሆኑ እንደሚገባም ሚኒስቴሩ ጠቁሟል።

በተመሳሳይ መልኩ ለ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና መቀመጥ የሚችሉትም የ11ኛ ክፍልን አጠናቀው ያለፉና የ12ኛ ክፍል የመጀመሪያ መንፈቀ ዓመት ትምህርት የተከታተሉ ሊሆኑ ይገባል ብሏል።

የ12ኛ ክፍልም መልቀቂያ ፈተና ወቅትም ከህዳር 28 አስከ ታህሳስ 1/2013 ዓ.ም እንደሚሆንም በምክረ ሐሳቡ መጠቀሱን ሚኒስቴሩ አመልክተወል።

የትምህርት አሰጣጡን ሂደት በተመለከተ ለመንግሥት ትምህርት ቤቶች የሚወጣው መመዘኛ በግል ትምህርት ቤቶች ተፈፃሚ እንደሚሆን ያሰፈረ ሲሆን በምክረ ሐሳቡ ላይ የሚደረገው ውይይት እንደቀጠለ መሆኑም ተገልጿል።

ባለፈው ዓመት የኮሮናቫይረስ በኢትዮጵያ መገኘቱ ከተረጋገጠ በኋላ ትምህርት በቶች በመጀመሪያ ለሁለት ሳምንታት እንዲዘጉ ተደርጎ የነበረ ሲሆን፤ በተከታይነት የበሽታውን መስፋፋት ለመግታት በወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መሰረት አስካሁን ተዘግተው መቆየታቸው ይታወሳል።