ሕግ ፡ አዲሱ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ምን ይዞ ይመጣል?

የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ-ስርዓት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ለ60 ዓመታት ገደማ በሥራ ላይ የቆየው የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ እንዲሻሻል ረቂቅ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲቀርብ የሚንስትሮች ምክር ቤት መስከረም 16/2013 ባካሄደው ስብሰባ መወሰኑ ይታወሳል።

ይህን ሕግ የማሻሻሉ ሥራ ከ1990ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ ሲከናወን የቆየ መሆኑን በዚሁ ሥራ ላይ ለአስር ዓመታት ከተሳተፉት ባለሙያዎች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ሙሉወርቅ ሚደቅሳ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ጉንማሻሻል ለምን አስፈለገ?

ከ1954 ጀምሮ በሥራ ላይ የነበረውን ይህንን ለማሻሻል አስፈላጉ ከሆኑባቸው ምክንያቶች መካከል የተወሰኑትን የሕግ ባለሙያው አቶ ሙሉወርቅ ሚደቅሳ ለቢቢሲ አብራርተዋል።

በ1987 ዓ.ም የኢፌድሪ ሕገ-መንግሥተ ከጸደቀ በኋላ "ነባር ሕጎችን ከሕገ-መንግሥቱ ጋር ማጣጣም" የሚል ፕሮጅክት መጀመሩን የሕግ ባለሙያው ያስታውሳሉ። በዚህ ፕሮጅክትም የወንጀል ሕጉን እና የቤተሰብ ሕግን ጨምሮ በርካታ ሕጎች ተሻሽለዋል። የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግን የማሻሻሉ ሥራም የዚሁ ፕሮጅክት አካል መሆኑን ይጠቅሳሉ።

በሕግ ሥርዓት ውስጥ ሁለት አይነት ሕጎች እንዳሉ የሚናገሩት አቶ ሙሉወርቅ፤ እነዚህም መሠረታዊ ሕግ እና የሥነ ሥርዓት ሕግጋት ይባላሉ።

የእነዚህን ሕጎች ምንነት በተመለከተም "መሠረታዊ ሕግ መብት እና ግዴታን የሚደነግግ ሲሆን፤ የሥነ ሥርዓታ ሕግጋት ደግሞ የተደነገጉ ሕጎች ተግባራዊ የሚደረጉበት ነው" እንደይላሉ የሕግ ባለሙያው አቶ ሙሉወርቅ።

ይህ እንዲሻሻል እየተደረገ ያለው ሕግም የሥነ-ስርዓት ሕግ መሆኑን ይገልጻሉ።

ኢትዮጵያ የወንጀል ሕጓን ያሻሻለችው በ1996 ዓ.ም ሲሆን አሁን የሚሻሻለው የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕግ እና የማስረጃ ሕግጋት የወንጀል ሕጉ ማስፈጸሚያ መሆናቸውን ባለሙያው ይናገራሉ።

"እናት ሕጉ ስለተሻሻለ የሥነ ሥርዓት ሕጉም መሻሻል አለበት። እንዲያውም ዘግይቷል። እስካሁን አገሪቱ ስትጠቀምበት የነበረው በ1954 የወጣውን የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ን ነው።"

በቅርብ ዓመታት የወጡ አዋጆች የራሳቸውን የሥነ ሥርዓት ድንጋጌዎች ይዘው መውጣታቸውን የሚገልጹት አቶ ሙሉወርቅ፤ ለምሳሌም የጸረ-ሙስና አዋጁ እና የጸረ-ሽብር አዋጁ የየራሳቸውን የሥነ ሥርዓት ድንጋጌዎች እንዳሏቸው ጠቅሰዋል።

ከዚህ አንጻርም "አዲስ የወንጀል ድንጋጌዎች በመጡ ቁጥር ዋናው የሥነ-ሥርዓት ሕግ ሊሻሻል ባለመቻሉ የራሳቸውን ሥነ ሥርዓት እየያዙ ወጡ። በዚህም የሥነ ሥርዓት ሕጉ ተበታተነ" በማለት አሁን የታሰበው ተግባር ይህንን ለማስቀረት ያለለመ መሆኑን ይናገራሉ።

ያለውን የሥነ ሥርዓት ሕግ ማሻሻል አስፈላጊ ከሆኑባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ እነዚህን የተበታተኑትን የሥነ ሥርዓት ድንጋጌዎች አንድ ቦታ የመሰብሰበው እና የተጠቃለለ የሥነ ሥርዓት ሕግ እንዲኖር ማድረግ እንደሆነ ያስረዳሉ።

"በአጠቃለይ ረቂቅ ሕጉ ሲተገበር አብዛኛውን ሥራ ለፖሊስ እና ለዐቃቤ ሕግ በመስጠት ፍርድ ቤት ላይ የሚኖረውን ጫና ይቀንሳል፣ ተጠርጣሪዎች እና ተከሳሾች ረዥም ጊዜ ፍትሕ ሳያገኙ የሚቆዩበትን ጊዜ ያስጥራል፣ በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ ፖሊስ ተጠርጣሪዎችን አስሮ ከመመርመር ይልቅ ምርመራ አከናውኖ ወደ መያዝ እንዲቀየር ያደርጋል" ይላሉ።

ምን አዲስ ነገር ይዞ ይመጣል?

የጥፋተኝነት ድርድር

በዚህ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት እና የማስረጃ ሕግ ረቂቅ አዋጅ ላይ ከዚህ ቀደም በአገሪቱ ሕግጋቶች ውስጥ የሌሉ አዳዲስ አሰራሮች መካተታቸውን አቶ ቀለምወርቅ ይናገራሉ። ከእነዚም መካከል አንዱ የጥፋተኝነት ድርድር (plea bargaining) ነው።

የጥፋተኝነት ድርድር በዳበሩ የፍትሕ ሥርዓቶች ውስጥ በስፋት ይተገበራል የሚሉት የሕግ ባለሙያው፤ አንድ ግለሰብ ክስ ተመስርቶበት ዐቃቤ ሕግ ግለሰቡ ጥፋተኝነቱን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ካለው ተጠርጣሪውን "ጥፋትህን እመን ይህን ያክል ፍርድ የወሰንብሃል" በሚል ያስማማል።

ለምሳሌ በርካታ ክሶች የሚመሰረቱባቸው ተከሳሾች ይኖራሉ፤ ከእነርሱ ጋር ዐቃቤ ሕግ ሊደራደር ይችላል። በዚህም መሠረት ይህን ያህል ወንጀል ፈጽመሃል፤ በዚህ በዚህ ጉዳይ ላይ ማስረጃ አለኝ።

ይህንን ይዘን ወደ ፍርድ ቤት ብንሄድ ክርክሩ እና የፍርድ ቤት ውጣ ውረዱ ብዙ ዓመት ይፈጃል፤ ስለዚህ የቀረቡብህን ክሶች እመን ዝቅ ያለ ቅጣት ይተላለፍብሃል የሚል ድርድር ሊካሄድ የሚችልብት ዕድል አለ።

"ይህ ግን በፍርድ ቤት ስር የሚያልፍ ነው። ዐቃቤ ሕግ ድርድሩን ካካሄደ በኋላ ፍርድ ቤት ወስዶ ነው የሚያጸድቀው። ምክንያቱም አንድ ሰው ጥፋተኛ የሚባለው እና ቅጣት የሚጣልበት በፍርድ ቤት ብቻ ስለሆነ ድርድሩ ከዐቃቤ ሕግ ጋር ቢደረግም፤ ሂደቱ የጥፋተኝነት ድርድር ሥነ ሥርዓቱን ተከትሎ መካሄዱ በፍርድ ቤት መረጋገጥ አለበት" ይላሉ።

ረቂቁ ተከሳሹ የጥፋተኝነት ድርድር ሲያደርግ የሕግ ባለሙያ ይዞ መሆኑ እንዳለበትም አስቀምጧል።

ይህ የሚደረገው በፍርድ ቤት ላይ የሚኖረውን ጫና እና የክርክር ጊዜ ለመቀነስ መሆኑን የሕግ ባለሙያው ይናገራሉ። ተከሳሹም ጉዳዩ ፍርድ ቤት ከደረሰ ሊወሰንበት ከሚችለው ቅጣት ያነሰ ቅጣት ይሰጠዋል።

ባህላዊ የፍትሕ ርዓቶች ቦታ ያገኛሉ

በዚህ ረቂቅ አዋጅ ላይ ከተካተቱት አዳዲስ ጉዳዮች መካከል ሌላኛው ባህላዊ የፍትሕ ሥርዓቶች ወደ ወንጀል ፍትሕ ሥርዓቱ መካተታቸው ነው።

"ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በሚያወጣቸው መመሪያዎች አንዳንድ ጉዳዮች በባህላዊ የፍትሕ ስርዓቶች ሊታዩ እንደሚችሉ አዲሱ የሥነ ሥርዓት ሕግ ያስቀምጣል" ይላሉ የሕግ ባለሙያው።

ለምሳሌ በአንዳንድ ማህበረሰቦች ውስጥ አንድ ሰው ግድያ ፈጽሞ ፍርድ ቤት ሄዶ ተፈርዶበት ፍርዱን ጨርሶ ከእስር ቤት ከወጣ በኋላም እርቅ ካልተፈጸመ ተበዳይ ፍትህ አልተሰጠኝም ብሎ ያስባል።

በዚህም ፍትሕ መሰጠቱን ማረጋገጥ ስለማይቻል መሠረታዊ የሚባሉ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችን የማይጻረሩ እስከሆነ ድረስ ከመደበኛ የፍትሕ ሥርዓቱ ውጪ በባህላዊ ሥርዓት ጉዳዮች መፍትሄ የሚያገኙበት አዲስ አሰራርን ያስተዋውቃል።

ምን ይቀየራል?

ሕጉን በማርቀቅ ሂደት ለረጅም ጊዜ የተሳተፉት አቶ ሙሉወርቅ እንደሚሉት፤ በረቂቅ አዋጁ የሚቀየሩ ጉዳዮች መኖራቸውን ይገልጻሉ።

ከእነዚህም መካከል የዋስትና መብት፣ የጊዜ ቀጠሮ እና የቅጣት አፈጻጸሞች ላይ ለውጦች እንደሚኖር ጠቁመዋል።

  • የዋስትና መብት

ብዙ ጊዜ ጠበቆች 'ድንበኛዬ ተጠርጥሮ የታሰረበት ወንጀል የዋስትና መብት የሚያስከለክል አይለደም' ሲሉ ዐቃቤ ሕግ በተቃራኒው 'የዋስትና መብት መሰጠት የለበትም' የሚል መከራከሪያ ሲያቀርቡ መስማት የተለመደ ነገር ነው።

የሕግ ባለሙያው አቶ ቀለምወርቅ ሚደቅሳም የዋስትና መብት ብዙ አጨቃጫቂ ነገሮች እንደሉት ይናገራሉ። ይህ ረቂቅ አዋጅም አጨቃጫቂ የሚባሉ የዋስትና መብት ጉዳዮችን ግልጽ ለማድረግ እንደሚያግዝ ይጠቅሳሉ።

በኢትዮጵያ እስካሁን የተለመደው የገንዘብ ዋትስና መሆኑን በማስታወስም፤ በዚህ ረቂቅ አዋጅ ላይ ተጠርጣሪው በየቀኑ ወይም በየሳምንቱ ወደ መንግሥት ተቋም እየቀረበ ሪፖርት እያደረገ ከዚያ ውጪ ሥራውን እንዲሰራ የሚደረግበት ሁኔታ እንዲፈጠር እንደሚያደርግ ይናገራሉ።

  • የምርመራ የጊዜ ቀጠሮ

መርማሪ ፖሊስ በያዘው ተጠርጣሪ ላይ ምርመራ ለማደረግ ፍርድ ቤትን በተደጋጋሚ የምርመራ ጊዜ ሲጠይቅ ይስተዋላል።

ነባሩ የሥነ ሥርዓት ሕግ መደበኛው በሚባለው ወንጀል የ14 ቀን በጸረ-ሽብር ደግሞ የ28 የምርመራ ጊዜ ሊፈቀድ እንሚችል ያስቀምጣል። ይሁን እንጂ ነባሩ ሕግ ገደብ አያስቀምጥም። "ለምን ያክል ጊዜ ነው የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ያሚያስቀምጠው የሚለው ላይ ገደብ የለም" ይላሉ።

አዲሱ ሕግ ግን ለወንጀሎቹ ዝቅተኛ ወንጀል፣ መካከለኛ ወንጀል እና ከፍተኛ ወንጀል የሚል ደረጃ በማውጣት የምርመራ ቀን ብዛት እና ገደብ ላይ ጣራ ማውጣቱን ይናገራሉ።

"ይሄ ከተከሳሾች መብት አንጻራ ጠቃሚ ድንጋጌ ነው። ለምሳሌ መካከለኛ ለሚባሉ ወንጀሎች መርማሪ ፖሊስ ከሁለት ጊዜ በላይ የምረመራ ጊዜ መጠየቅ አይችልም።"

በተቻለ መጠን አንድ ተጠርጣሪ ከመያዙ በፊት ፖሊስ ማስረጃ እንዲሰበሰብ ጥረት የሚያደርግ ሕግ ነው ይላሉ አቶ ሙሉወርቅ።

"ተጠርጣሪው ምርመራ እየተደገበት እንደሆነ አውቆ አራሱን ለመሰወር እና ማስረጃ ለማጥፋት የሚሞክርበት ሁኔታ እስካልተፈጠረ ድረስ ፖሊስ የምረመራ ሰራውን ጨርሶ ነው መያዝ ያለበት። ተጠርጣሪን ይዞ ማስረጃ የመፈለግ ሂደት መቀየር አለበት የሚል አካሄደን ይፈጥራል።"

  • የቅጣት አፈጻጸም

ነባሩ የሥነ ሥርዓት ሕግ ላይ የቅጣት አፈጻጸም ዝርዝር ነገሮች የሉትም። ለምሳሌ ብዙ ጊዜ ተፈጻሚ ባይሆንም የሞት ቅጣትን ፍርድ ቤቶች እንደሚያስተላልፉ የሕግ ባለሙያው ይናገራሉ።

ይህ የሞት ቅጣት በምን መንገድ ነው መፈጸም ያለበት? የሞት ቅጣት የተበየነበት ሰው የሞት ፍርዱ ወደ የእድሜ ልክ እስራት ሳይቀየርለት ወይም የሞት ቅጣቱ ተፈጻሚ ሳይሆንበት ለምን ያህለ ጊዜ ይቆያል? በሚሉት ጉዳዮች ላይ አዲሱ ሕግ ዝርዝር የአፈጻጸም ድንጋጌዎች ይዟል።

ከሞት ቅጣት በተጨማሪ ዝርዝር የሆነ የገንዘብ ቅጣት እና የእስራት ቅጣት ላይ ዝርዝር የአፈጻጸም ድንጋጌዎችን መያዙን አቶ ቀለምወርቅ ለቢቢሲ አስረድተዋል።