ፕሬዚደንታዊ ክርክር፡ ከትራምፕና ባይደን ክርክር በኋላ የክርክር መመሪያው ሊቀየር ነው

በትራምፕና በባይደን መካከል የተደረገውን ክርክር ከተጠበቀው በታች እጅግ በጣም አነስተኛ ተመልካች ነው የተከታተለው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ማክሰኞ ሌሊት ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕና ተፎካካሪያቸው ጆ ባይደን ያደረጉትን ፕሬዚደንታዊ ክርክር የተመለከተው የፕሬዚደንታዊ ክርክር ኮሚሽን፤ በመጭው የሚካሄዱ ክርክሮችን መልክ ለማስያዝ የክርክር ፕሮግራሙን ቅርፅ እንደሚቀይር አስታወቀ።

አንደኛው የሚወሰደው እርምጃም ማይክራፎን መዝጋት ሊሆን እንደሚችል ተነግሯል።

ይህም አንዱ ተወዳዳሪ በሚናገርበት ጊዜ ሌላኛው ተወዳዳሪ ንግግሩን እንዳያቋርጠው ታስቦ የታቀደ መላ ነው።

እዚህ ውሳኔ ላይ የተደረሰው ማክሰኞ ዕለት የተካሄደውንና ዘለፋ የበዛበትና መደማመጥ ያልታየበትን ክርክር ተከትሎ ነው።

በዚያ ክርክር ትራምፕና ባይደን በክሊቭላንድ፣ ለ90 ደቂቃ ዱላ ቀረሽ ትንቅንቅ አድርገዋል።

ትራምፕ ባይደንን ብቻ ሳይሆን የክርክሩን አጋፋሪ እያቋረጡ መናገር፣ እኔን ብቻ ስሙኝ ማለት አብዝተው ነበር።

ትራምፕና ባይደን የተከራከሩባቸው አበይት ነጥቦች በጤና መድኅን፣ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ ሹመት፣ በኮሮናቫይረስ፣ የአሜሪካ ምጣኔ ሀብት፣ ዘረኝነትና የምርጫ ሂደትና የምርጫ ገለልተኝነት ነበሩ።

ትራምፕ ባይደንን የክፍልህ ሰነፉ ተማሪ ነበርክ፣ አሳፋሪ ነህ ሲሉ፤ ባይደን በበኩላቸው አሜሪካ እንዳንተ የከንቱ ከንቱ መሪ አይታ አታውቅም ሲሉ መልሰዋል።

ባይደን ትራምፕን ‹ቀጣፊ› ብለዋቸዋል። ወደ ካሜራው በቀጥታ በመዞርም ‹ይህ ሰውዬ የሚላችሁን ታምኑታላችሁን?› ሲሉ የአሜሪካን ሕዝብ ጠይቀዋል።

በዚህ ክርክራቸው ትራምፕ ባይደንን 73 ጊዜ አቋርጠዋቸዋል። ትራምፕ ለ38 ደቂቃ የተናገሩ ሲሆን ባይደን ደግሞ 43 ደቂቃ ተጠቅመዋል። ከዚህ ውስጥ 20 ደቂቃ ወስደው የተነጋገሩት በኮቪድ-19 ጉዳይ ነው።

የመጀመሪያው ፕሬዚደንታዊ ክርክርም በአሜሪካም ሆነ በመላው ዓለም ትችት ዘንቦበታል።

የፕሬዚደንት ትራምፕ ቡድን የኮሚሽኑን እቅድ ተችቶታል።

ለቀጣዩ ፕሬዚደንታዊ ክርክር የታሰበው ምንድን ነው?

የፕሬዚደንታዊ ክርክሩ ኮሚሽን ባወጣው መግለጫ የመጀመሪያው ፕሬዚደንታዊ ክርክር፤ የሚካሄደው ሙግት ሥርዓት ባለው መንገድ በሚነሱ ጉዳዮች ላይ ለመሟገት ተጨማሪ የቅርፅ ለውጦች መጨመር እንዳለባቸው አሳይቷል ብሏል።።

መግለጫው አክሎም ኮሚሽኑ ለውጦቹን በትኩረት በማጤን እርምጃዎቹን በአጭር ጊዜ እንደሚያሳውቅ ገልጿል።

ኮሚሽኑ የፎክስ ኒውሱን የክርክሩን አጋፋሪ ክሪስ ዋላስ፤ ሙግቱን ለመምራት ባሳየው ሙያዊ ብቃትና ችሎታ ያመሰገነ ሲሆን፤ ቀሪዎቹን ሙግቶች ለማካሄድ ግን ተጨማሪ ሕጎች መቀመጣቸውን ማረጋገጥ ያሻል ብሏል።

በመጀመሪያው ውይይታቸው ፕሬዚደንት ትራምፕ በተደጋጋሚ ጆ ባይደንን ሲያቋርጧቸውና አላናግር ሲሏቸው ተስተውሏል፤ ይህም ሁለቱም ተወዳዳሪዎች ያለ መደማመጥ አንዳቸው ባንዳቸው ላይ እየተደራረቡ፤ የክርክሩን መልክ ወደ ጫጫታ ለውጦታል።

በክርክሩ ወቅት ፕሬዚደንት ትራምፕ የባይደንን ጉብዝና ጥያቄ ውስጥ የከተቱት ሲሆን፤ ባይደንም ትራምፕን 'ቀልደኛ' ሲሉ ዝም እንዲሉላቸው " አንዴ አፈዎትን ይዘጉልኛል ሰውዬ!" ብለዋቸዋል።

በዚህም ሳቢያ ኮሚሽኑ ቀጣዮቹን 48 ሰዓታት ለቀጣይ ክርክሮች አዲስ መመሪያዎችንና ሕጎችን ለማውጣት እንደሚያውል ሲቢኤስ ኒውስ ምንጮቹን ጠቅሶ ዘግቧል።

በመሆኑም አንዳቸው የአንዳቸውን ሃሳብም ሆነ የአጋፋሪውን ሃሳብ እንዳያቋርጡ ለማድረግ የተወዳዳሪዎቹን መነጋገሪያ ማይክራፎን መቆጣጠር ከታሰቡ መመሪያዎች ዋነኛው እንደሚሆን ኮሚሽኑ ተናግሯል።

ሁለቱም የዘመቻ ቡድኖች ሕጉ የሚነገራቸው ሲሆን ጉዳዩ ለድርድር ክፍት አለመሆኑን ምንጮች ጨምረው ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ ገለልተኛ ሲሆን ከጎርጎሮሳዊያኑ 1988 ጀምሮ የፕሬዚደንታዊ ምርጫ ክርክሮችን ያዘጋጃል።

የተሰጠው ግብረ መልስ ምንድን ነው?

የትራምፕ የምርጫ ዘመቻ ኮሚዩኒኬሽን ዳሬክተር ቲም ሙርታጅ የማክሰኞ ዕለቱን ጭቅጭቅ የበዛበት ክርክር "ነፃ የሃሳብ ልውውጥ" ሲሉ በመግለፅ የኮሚሽኑን እቅድ ተችተዋል።

"ይህን የሚያደርጉት ሰውያቸው ነጥብ ስለጣለ ነው [ ስለተረቱ] ነው" ብለዋል።

አክለውም "ፕሬዚደንት ትራምፕ ተፅዕኖ ፈጣሪ ነበሩ፤ በጨዋታ መሃልም ሕግ መቀየር የለበትም" ሲሉም ሞግተዋል።

የጆ ባይደን ዘመቻ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ኬት ቤዲንግፊልድ በበኩላቸው የቀድሞ ምክትል ፕሬዚደንት ጆ ባይደን፣ የዶናልድ ትራምፕን ባህሪ ለመቆጣጠር ሲል ኮሚሽኑ በሚያወጣቸው በማንኛውም ሕግ ውስጥ ሆነው እንደሚወዳደሩ ተናግረዋል።

" ፕሬዚደንቱ በዘመቻው ለመራጮች መመለስ የሚገባቸውንና ያልመለሷቸውን ጥያቄዎች ከመመለስ ወይም የባለፈውን ምሽት ረባሽ ክርክራቸውን ከመድገም መምረጥ አለባቸው" ብለዋል።

ቀጣዩ ክርክር ከ5 ቀናት በኋላ በፍሎሪዳ ሚያሚ እንደሚደረግ ቀን ተቆርጦለታል።