ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ፡ "በታሰርኩበት ጊዜ በከዘራ እየመጣ ይጠይቀኝ ነበር"- ርዕዮት አለሙ

ፕሮፌሰር መስፍን

የፎቶው ባለመብት, FB

"አንድ ትውልድ ይወለዳል በጊዜው እንደጊዜው ያድጋል፤ ያልፋል፤ በሌላ ትውልድ ይተካል፤ አዲሱም ትውልድ የተረከበውን ቅርስ ይዞ ይነሣና በራሱ ጥረት አዳዲስ ሥራዎችን ሠርቶ ይጨምርበትና ያድጋል፤ አዲስ ነገርን ትቶ ያልፋል፤ የቀደመው ትውልድ ተፈጥሮና ኑሮው ከሚያስገድደው በላይ ለሚቀጥለው ትውልድ መስዋት መሆን አይችልም፤ አይጠበቅበትምም፤ በምጽዋትና በሞግዚት አስተዳደር የሚኖር ትውልድ ሊሚቀጥለው ትውልድ የሚያስተላልፈው ዕዳ ብቻ ነው"

ይህ የተወሰደው በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ለአስርት ዓመታት ያህል በፅሁፋቸው፣ በንግግራቸው ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ሰላማዊ ትግልን ዋና ማዕከል አድርገው ሲሞግቱ ከነበሩት የአደባባዩ ምሁር ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም ከፃፉት ነው።

ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ከሁለት ሳምንት በፊትም "ትውልዶች" ብለው በፌስቡክ ገፃቸው መጨረሻ አካባቢ ከፃፉት የተቀነጨበ ነው።

በርካቶች የቀለም ቀንድ ብለው የሚጠሯቸው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች፣ ደራሲ፣ ፖለቲከኛ፣ የጂኦግራፊ መምህሩ ፕሮፌሰር የአገሪቱን ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊና መፃኢ ተስፋንም በተመለከተ "ተዝቆ ከማያልቀው" ዕውቀታቸው ሙያዊ ትንታኔን በመስጠት ዘመናትን ተሻግረዋል።

በቅርብ የሚያውቋቸውና ለሰዓታት ውይይት ያደረጉ ሰዎች እውቀታቸው ባህር ነው ይሏቸዋል። በተደጋጋሚ በሚያደርጓቸው ቃለ መጠይቆች ነፃነት በምንም የማይለወጥ መሆኑን፣ ለሆድ መገበር የሚለውን አጥብቀው ሲቃወሙም ይሰማሉ።

ለሚያምኑበት ነገር የማይደራደሩ፣ በአቋማቸው የፀኑ፣ ለአላማቸው ሟች የሚባሉት ፕሮፌሰር መስፍን በዘመናት ውስጥም በፅሁፋቸው፣ በአስተምህሮታቸው እንዲሁም የእድሜ ባለፀጋ ከሆኑ በኋላም የመጣውን ፌስቡክ ተቀላቅለው በተገኘው መድረክ ሁሉ ሲፅፉ፣ ሲተቹ ኃይለ ቃልም በመናገር ይታወቃሉ።

በዚህም ሁኔታ በአስተሳባቸው በርካቶች የአገር ዋርካ፣ ጭቆናን የሚጠየፉ፣ ትውልድን ለማንቃት የማይታክቱ የአፃፃፍ ችሎታቸውን በማወደስ፣ የሰብዓዊ መብት ፋና ወጊ የሚሏቸውን ያህል የመርማሪ ኮሚሽን ሊቀ-መንበርነታቸው ጋር ተያይዞም ከ60ዎቹ ግድያ ጋር ነቀፌታቸውን የሚያሰሙ አሉ።

"ኢትዮጵያዊ ሁሉ መብቱ እንዲከበር የታገለ ሰው"- ዶክተር ኃይሉ አርአያ

ፕሮፌሰር ወይም የቀድሞ ተማሪዎቻቸው እንደሚጠሯቸው ጋሽ መስፍን በአደባባይ በመሞገትና ሃሳባቸውንም በማንፀባረቅ በርካታ ትውልዶችን ማስተሳሰር እንዲሁም ሃሳቦችም ማምጣት የቻሉ ሰው መሆናቸውንም ለበርካታ አስርት ዓመታት የሚያውቋቸው ዶክተር ኃይሉ አርአያ ይናገራሉ።

ኢህአዴግ ስልጣን በተቆጣጠረ ማግስት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ)ን ያቋቋሙት ፕሮፌሰር መስፍን በአገሪቱ ውሰጥ ይደረግ የነበረውን የመብት ጥሰት ይፋ በማውጣት መስራታቸውንም በማስታወስ "ኢትዮጵያዊ ሁሉ መብቱ እንዲከበር የታገለ ሰው ነው" ይሏቸዋል።

ለዓመታትም መሰረታዊ የሚባለውን የሰብዓዊ መብት እንዲከበርም ከፍተኛ ጥረትና አስተዋፅኦ እንዳደረጉም ዶክተር ኃይሉ ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ።

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህርነት ጀምሮ ወደ ፖለቲካው መድረክም ጎራ ባሉበት ወቅትም በአንድነት ፓርቲ አብረዋቸው የነበሩት ዶክተር ኃይሉ ፕሮፌሰሩ ሃሳባቸውን የሚገልፁበት መንገድና ስለ ቀናነታቸው አውርተው አይጠግቡም።

"በብዙ መንገድ ነው መስፍንን የማውቀውና የምወደው። አንዱ እሱን የምወድበት አቋም በሚያምነው ነገር የመፅናቱ ጉዳይ ነው" የሚሉት ዶክተር ኃይሉ የሚያስቡትንም ሆነ የሚያምኑበትን ከመናገር ወደ ኋላ የማይሉ፣ እውነትና ትክክለኛ ነው ብለው ያሰቡትንም ማንም ቢቃወም ከመግለፅ ወደ ኋላ አይሉም ይሏቸዋል።

"ሐሳቡን በትክክልና ቀና በሆነ መንገድ በሚያቀርብበት ጊዜ ሰዎች ይነካሉ፤ ይቆጣሉ። የተለየ ባህርይ ነው የሚሰጡት፣ ሰውንም ያስቀይማል ግን እውነቱንና ትክክለኛ ነገር ነው የሚናገረው" ይላሉ።

አንዳንዶች ፕሮፌሰሩ የሚናገሩትን ጉዳይ በተሳሳተ መንገድ የሚተረጉሙት በመኖራቸውም በሃሳብ ከሰዎች ጋር እንደሚጋጩ የሚናገሩት ጓደኛቸው ዶክተር ኃይሉ ብቻ አይደሉም። ስለሳቸው በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚባሉና የሚፃፉ ጉዳዮችም ለዚህ አባሪ ናቸው።

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ስፍራ በተሰጠው ምርጫ 1997 ጋርም ተያይዞ ቀስተ ደመና የተባለ የፖለቲካ ፓርቲ የመሰረቱት ፕሮፌሰሩ በአንድነት ፓርቲ ውስጥም ከዶክተር ኃይሉ ጋር አንድ ላይ ነበሩ።

በሃሳብ ከፓርቲውም ጋር ሆነ ከሳቸው ጋር ቢለያዩም፤ እንዲሁም ትክክል አይደለም ብለው ቢያምኑም "የተናገረው ነገር በእኔ ሃሳብ፣ በእኔ በኩል ትክክል አይደለም። ነገር ግን የሚያምንበትን ነገር በመግለፁ አቋሙን አደንቅለታለሁ፤ አከብርለታለሁኝ" ይላሉ።

በሃሳብ መለያየት እንዳለ ሆነ በቅንነትና በምሉዕነት መግለፃቸውን ለሳቸው ከበሬታ እንዲኖራቸው እንዳደረጋቸውም ደጋግመው ዶክተር ኃይሉ ይናገራሉ።

"ሃሳቡን የመግለፁን መንፈስ፣ ቅንነቱን አደንቅለታለሁ። በዚህ ምክንያት በጣም እወደዋለሁ" የሚሉት ዶክተር ኃይሉ የፕሮፌሰር መስፍን ዋናው ትኩረታቸው የተሻለች ኢትዮጵያ፣ በድህነትና በጭቆና የሚደቆሰው ሕዝብ የተሻለ ኑሮና ነፃነትን የሚያገኝበትን የወደፊትን መፍጠር ህልማቸው ነበር።

በአንዳንዶች ዘንድ 'የኔታ' ተብለው የሚጠሩት ፕሮፌሰር ዕድሜያቸውን በሙሉ ከወጣቶች ጋር ያሳለፉ፣ በዕድሜ የልጅ ልጆቻው ከሚሆኑ ጋር የቅርብ ጓደኝነት ያፈሩና በአገሪቱ ራዕይም አብረው የሚወጥኑና የሚሟገቱም ናቸው።

"በታሰርኩበት ጊዜ በከዘራ እየመጣ ይጠይቀኝ ነበር"- ርዕዮት አለሙ

ከነዚህም መካከል ጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙ አንዷ ናት።

በከፍተኛ ሃዘን ተውጣ ያለችው ርዕዮት አለሙ ስለ ፕሮፌሰር መስፍን ጥቂት ነገር ንገሪን ብሎ ቢቢሲ በጠየቃት ወቅትም "ጥሩ ስሜት ላይ ስላልሆንኩኝ መገለፅ እንዳለበት ላልገልፀው እችላለሁ" ብላለች።

ከፕሮፌሰር መስፍን ጋር በጣም ቅርበት የነበራቸው ሲሆን እሷ ብቻ ሳትሆን የእሳቸውን አላማ የሚደግፉ ወጣቶችም ጋር አብረው ይሰባሰቡም፤ ይገናኙም ነበር።

በተለይም ደግሞ በበዓላት ወቅት አብረው ያከብራሉ፤ የእሳቸውንም ልደት እንዲሁ አንዳንድ ዝግቶጅም ላይ አብረው ማሳለፋቸው ከፍተኛ ቅርበት እንደፈጠረላቸውም ርዕዮት ታስረዳለች።

"ትዝ የሚለኝ ትልልቅ መፃህፍት (እንግሊዝኛቸው ሁሉ ከበድ ከበድ የሚል) ይህንን አንብበሽ ጨርሰሽ እንወያይበታለን፤ እያለ በዚህ አይነት መንገድ ሁሉ ወጣቶችን ለማብቃት የሚያደርጋቸው ጥረት ትዝ ይለኛል" በማለት ሳግ በተናነቀው ድምጿ ትናገራለች።

በታሰረችበት ወቅትም በርካታ ጊዜዎች እንደጎበኟትም ታስታውሳለች።

"በታሰርኩ ጊዜ እንደዚያ ከዘራ ይዞ ሁሉ እየመጣ ይጠይቅ ነበር ከወጣቶች ጋር አብሮ፤ በታሰርኩባቸው ዓመታት ልደቶቼ ሲታሰቡ በተለያዩ ቦታዎች ይገኝ ነበር" ትላለች።

ስትፈታም እስር ቤት በር ላይ ቆመው ከጠበቋትና ከተቀበሏትም መካከል ፕሮፌሰር መስፍን አንዱ ነበሩ። መፅሃፏም ሲወጣ ከጀርባው ማስታወሻ የፃፉላት እሳቸው ናቸው።

"በዚያ እድሜው፤ ምን ያህል አገርሽን አክብረሻል ብሎ ሲያስብ? ምን ያህል እንደሚያከብርሽ እሱን የሚያህል ትልቅ ሰው። እኔ እንግዲህ ከእሱ ጋራ በምንም በምንም የማልወዳዳር ሰው በዚያ መጠን ሲያከብር ምን አይነት ሰው እንደሆነ መረዳት ይቻላል" በማለትም ለሰው ልጅ የነበራቸውን ከበሬታም ጥልቅ እንደነበረ ታዝባለች።

"ወገንተኝነትን የሚፀየፍ ነበር" የምተለው ርዕዮት "ኢትዮጵያ በማለት እድሜ ልኩን የኖረላት፣ የተሰቃየላት፣ ያከበራት ለእሱ ከምንም በላይ የሆነች አገር ነች።"

"እሱ ከዚህ ጎሳ ነው፣ ከዚህ ነው፤ የእሱ ጉዳይ አይደለም። ሰው የተባለ ፍጡር ሁሉ ተጎዳ ሲባል ራሱ እንደተጎዳ አድርጎ የሚያስብ፣ የሚያመው እንደዚህ አይነት ትልቅ ሰው ነው ያጣነው" ትላለች።

ከዚያም በተጨማሪ በአኗኗራቸው ላይ ለቁሳዊ ህይወትም ሆነ ለሃብት ምንም አይነት ቦታ የማይሰጡም እንደነበሩም ትናገራለች።

"አንዳንዴም የሚጠየፍ ነው የሚመስለኝ እና እንዴት ሆኖ እድሜ ልኩን በአንዲት አፓርትመንት እንደኖረ ሲታሰብ በእሱ የእውቀት ደረጃ የትኛውም ዓለማዊ ደረጃ ያሉ ሰዎች መድረስ የሚችሉበት ነገር ሲታሰብና እሱ እንዴት እንደኖረ ሳስብ በቃ ጉዳዩ አይደለም" በማለትም በሐዘን በተሞላ ድምጿ ታላቅ ስለምትላቸው ፕሮፌሰር ምን አይነት ሰው እንደነበሩም ትናገራለች።

በተለያየ ትውልድ ላይ ያሉት ዶክተር ኃይሉም ሆነ ርዕዮት የሚሉትም ፕሮፌሰሩ "ራሳቸውን ሆነው የኖሩ" ሃሳባቸውን በግልፅ የሚያንፀባርቁ ነበሩ።

"በምንም አይነት ሁኔታም ሆነ ጉዳይ አለማመቻመች፤ ሃሳቡ ጋር መስማማት አለመስማማት ይቻላል። እሱ ላመነበት እውነት ነው ላለው ነገር፤ ደረስኩበት ላለው እውነት መኖር የሚችል ራሱን ሆኖ የኖረ ሰው ነው" በማለትም ያላትን ክብርና ፍቅር ትገልፃለች።

ከእሷም ጋር ቢሆን የሃሳብ ልዩነቶች ያሏቸው ሲሆን በአንዳንድ መድረኮችም ላይ በግልፅ ተነጋግረዋል። በልዩነቶቻቸውም መካከል ተከባብረውም ቀጥለዋል።

ቅርበታቸው ከርዕዮት ጋር ብቻ ሳይሆን ከቤተሰቧም፣ ከእህቷምም፣ ከአባቷም ከእናቷም ጋርም በጣም ቅርብ ግንኙነት ነበራቸው ነው።

"ነጻ ሆኖ መኖር፣ ድፍረት ማሰብን ያስተማሩን" አቶ ይልቃል ጌትነት

"ጋሽ መስፍንን የማውቃቸው" ይላል ፖለቲከኛው ይልቃል ጌትነት (ኢንጂነር) ስለ ፕሮፌሰር መስፍን ሲናገር። እርሱ ፕሮፌሰር ብሎ ጠርቷቸው እንደማያውቅ በመግለጽም ማዕረግ ስለሚያራርቅ "እንደ አንድ ወዳጅ ፣ መምህር፣ የልብ ወዳጅ" ጋሼ መስፍን በማለት እንደሚጠራቸው ይገልጻል።

አቶ ይልቃል ፕሮፌሰር መስፍንን በቅርበት ማወቅ የጀመረው በምርጫ 97 እስር ቤት ገብተው ከወጡ በኋላ መሆኑን ያስታውሳል።

በወቅቱ አንድነት ፓርቲን ለመመስረት ዝግጅት ላይ እንደነበር የሚያስታውሰው ይልቃል (ኢንጂነር)፣ እውቂያቸው ለ12 ዓመት ያህል እንደሚያውቋቸው ጊዜውን በማስላት ይናገራል።

ፕሮፌሰር ከይልቃል (ኢንጂነር) ጋር በነበራቸው ወዳጅነት ወቅት ልዩ ጥልቅ ፍላጎት እንዳላቸው የሚነግሩኝ የነበረው በማለትም የኀብረተሰብን እና የግለሰብን ሥነልቦና ማወቅ እንደሆነ ይገልጻል።

ጋሽ መስፍን የሚያምኑበትን በድፍረት የሚናገሩ ሰው ብቻ አይደሉም ያለው ይልቃል "ኃላፊነት የሚሰማቸው፣ የሚያስተምሩትና የሚናገሩት ነገር ላለው ማኅበራዊ ስሪት ምን ይጠቅማል ብው የሚያስቡ፣ አንዳንድ ጊዜ እውነትም ቢሆን እንኳ ለአገርና ለሕዝብ ጉዳት አለው ብለው ካመኑ የማይናገሩ፣ ኃላፊነት የሚሰማቸው የአደባባይ ምሁር ነበሩ" ይላል።

ይልቃል ፕሮፌሰር መስፍን በሕንድ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ሲሰሩ በዋናነት ጂኦግራፊ ያጥኑ እንጂ ፍልስፍናንም መማራቸውን በማንሳት እና ብዙ ያነበቡ መሆናቸውን በመጥቀስ ያላቸው እውቀት ዘርፈ ብዙ የሆነ እንደሆነ ይገልጻል።

ለማስተማር፣ ለማሳወቅ፣ ብቻ ለመቆም ያላቸው ጽናትን ከሚያደንቁላቸው መካከል መሆኑን ይናገራል።

በኢትዮጵያ ስለድርቅ ለሰባት ዓመት ያህል በማጥናት የጻፍዋቸው ጥናቶች ከድርቅ ባሻገር ችጋርን (Famine) በማንሳትም፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደ ማጣቀሻ ሆኖ ለማስተማሪያነት እንደሚያገለግል ገልፀዋል።

በጥናታቸው መደምደሚያ ላይ ነጻነትና ችጋር ተያያዥ መሆናቸውን በማንሳት የኢትዮጵያ ገበሬ ነጻ እስካልወጣ ድረስ ችጋር ከአገሪቱ አይጠፋም ብለው በጥናታቸው መደምደማቸውን፣ የችግሮቻችን ምንጭ ከፖለቲካ እና ነጻነት ማጣት መሆኑን በእነዚሁ ጥናቶቻቸው በሚገባ መግለጻቸውን ያስታውሳል።

ስለ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት፣ እውነትንና ሳይንስን መሰረት አድርጎ በመናገር ፣ የሕብረተሰብ ሥነልቦናን፣ የማስተማር ልዩ ችሎታ፣ አድማጭን በሚዋጅ መልኩ ኅብረተሰብን ተገንዝቦ የማስተማር ችሎታቸው የላቀ መሆኑን ከሚያስታውሳቸው መካከል መሆኑን ይመሰክራል።

ነጻ ሆኖ የመኖር፣ በድፍረት የማሰብ፣ ትልቅ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች መሆናቸውን የእርሳቸው መገለጫዎች መሆናቸውንም ያክላል።