ኮቪድ-19 ፡ ደቡብ አፍሪካ ለአፍሪካ አገራት ድንበሮቿን ከፈተች

የደቡብ አፍሪካው አየር መንገድ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላካል ድንበሮቿን ዘግታ የቆየችው ደቡብ አፍሪካ፤ ለአፍሪካ አገራት ድንበሮቿን መክፈቷን አስታወቀች።

ይሁን እንጅ ዩናይትድ ኪንግደም፣ አሜሪካና ሩሲያን ጨምሮ በቫይረሱ የተያዙ ከፍተኛ ሰዎች ቁጥር ላለባቸው አገራት አሁንም ገደቡ አልተነሳም።

አገሪቷ በወረርሽኙ ሳቢያ ድንበሯን የዘጋችው መጋቢት ወር ላይ ነበር።

አሁን ግን ከሐሙስ ዕለት ጀምሮ የየብስ ድንበሮቿን እና ሦስት ዋና ዋና አየር ማረፊያዎቿን፤ ኬፕታውን፣ ደርባን እና ጆሃንስበርግን እንደምትከፍት ገልጻለች።

የአገሪቷ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናሌዲ ፓንዶር እንዳሉት ሁሉም ወደ አገሪቷ የሚገቡ መንገደኞች ከኮቪድ-19 ነፃ መሆናቸውን የሚያሳይ የሕክምና የምስክር ወረቀት መያዝ የሚጠበቅባቸው ሲሆን እዚያ ሲደርሱም ምርመራ ይደረግላቸዋል።

በበሽታው በተያዙና በሞቱ ሰዎች ቁጥራቸው ከደቡብ አፍሪካ ከሚበልጡ አገራት የሚመጡ መንገደኞች ግን ለመዝናናት ወይም ለእረፍት ወደ አገሪቷ እንዲገቡ አይፈቀድላቸውም ተብሏል።

ወደ አገሪቷ እንዲገቡ የሚፈቀድላቸውም ባለሃብቶች፣ ዲፕሎማቶች፣ ከፍተኛ የበሽታው አደጋ ካለባቸው አገራት የሚመጡ የንግድ ሰዎች፣ ልዩ ቪዛ ያላቸው [high-skills visa holders] ብቻ መሆናቸውን ሚኒስትሩ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

የበሽታው ምልክት የታየባቸው አሊያም በሽታው የተገኘባቸውም የሕክምና ወጪያቸውን መሸፈን እንደሚጠበቅባቸውም ተነግሯል።

ደቡብ አፍሪካ በቫይረሱ ክፉኛ የተጠቃች አፍሪካዊት አገር ናት። እስካሁንም 674 ሺህ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል።

ይህ ቁጥር በአጠቃላይ በአህጉሪቷ ከተመዘገበው ግማሽ ያህሉ ነው።