አንበጣ መንጋ፡ በምሥራቅ ሐረርጌ ጸረ አንበጣ ኬሚካል በመርጨት ላይ የነበረ አውሮፕላን ወደቀ

አነስተና አውሮፕላን ወድቆ

የፎቶው ባለመብት, Jarso Wereda communucation

በኦሮሚያ ክልል በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ጃርሶ ወረዳ የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከል ኬሚካል በመርጨት ላይ የነበረ አነስተኛ አውሮፕላን ዛሬ ሐሙስ መውደቁ ተገለጸ።

የጃርሶ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አብዱል ቃድር ደዚ ለቢቢሲ፣ አውሮፕላኗ ዛሬ ሐሙስ፣ ከቀኑ ስድስት ሰዓት አካባቢ ጊደያ በሃ በምትበል ቀበሌ ውስጥ የአንበጣ መንጋ ለመከላከል ኬሚካል ለመርጨት በቅኝት ላይ የነበረ አነስተኛ አውሮፕላን መውደቁን ለቢበሲ ተናግረዋል።

"የአንበጣ ወረርሽኝ በቀበሌዋ ከተከሰተ አራተኛ ቀኑን ይዟል። አንበጣው በጣም ከመብዛቱ የተነሳ በአራት ቀበሌዎች በሚገኝ ሰብል ላይ ጉዳት እያደረሰ ነበር። ለዚህም አውሮፕላኑ በመምጣት እየዞረ እያለ ድንገተኛ አደጋ ገጥሟታል" ብለዋል።

ዛሬ በምሥራቅ ሐረርጌ ጃርሶ ወረዳ ጊደያ በሃ ቀበሌ በደረሰው አደጋ በአውሮፕላኑ ውስጥ አብራሪው ብቻ የነበረ መሆኑን አስተዳዳሪው ገልፀው፣ ምንም አይነት ጉዳት እንዳልደረሰበት ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

"ወዲያውኑ እኛ ከወረዳው አምቡላንስ አስመጥተን የነበረ ቢሆንም ሌላ አውሮፕላን መጥቶ ይዞት ሄዷል" ሲሉም አክለዋል።

"አብራሪው አልተጎዳም፤ በጥሩ ሁኔታ ላይ ነው ወደ ድሬዳዋ የተወሰደው፤ አውሮፕላኑ ጎማው ላይ ብቻ ጉዳት የደረሰበት ሲሆን ቀሪው የአካል ክፍሉ ላይ ምንም ጉዳት አልደረሰም" ሲሉ ተናግረዋል።

በጃርሶ ወረዳ በሚገኙ አራት ቀበሌዎች ውስጥ የአምበጣ መንጋ በማሽላ እና በቆሎ የመሳሰሉ የሰብል አይነቶች ላይ ጉዳት ማድረሱንም አቶ አብዱል ቃድር ለበቢሲ ጨምረው አስረድተዋል።

ባለፈው ሳምንት፣ መስከረም 22/2013 ዓ.ም በአማራ ክልል ወረባቦ ወረዳ የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከል ኬሚካል በመርጨት ላይ የነበረ አውሮፕላን ፍራንጉል በሚባል ቦታ ወድቆ መከስከሱ ይታወሳል።

በወቅቱ የወረዳው የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሳዳም ሽመልስ ለቢቢሲ እንደተናገሩት በአደጋው በሕይወት ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን ገልፀው፣ የሄሊኮፕተሩ አብራሪ መጠነኛ ጉዳት አጋጥሞት በሰመራ ሆስፒታል የሕክምና ክትትል እየተደረገለት እንደነበር አመልክተዋል።

በምሥራቅ አማራ ሰሜን እና ደቡብ ወሎ ዞኖች የተከሰተው የአንበጣ መንጋ እንዲሁ በሰብል ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው።

በደቡብ ወሎ ዞን ወረባቦ ወረዳ የተከሰተው መንጋ የጉዳት መጠኑ ከፍተኛ መሆኑን የወረዳው ኃላፊዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በወረዳው የተከሰተው የበረሃ አንበጣ መንጋ 24 ሺህ ሄክታር የሚሆን መሬት የወረረ ሲሆን በወረዳው በ11 ቀበሌዎች ይገኝ የነበረ ሰብል ላይ ከ10 እስከ 100 በመቶ ጉዳት አድርሷል።

በተመሳሳይ የአንበጣ መንጋው በትግራይ ክልል ደቡባዊ ትግራይ ዞን ሦስት ወረዳዎች ማለትም ራያ አዘቦ፣ ራያ አላማጣ ፣ ራያ ጨርጨር ተከስቷል።

በዞኑ የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ በባህላዊ መንገድ ለመከላከል ኅብረተሰቡ ጥረት እያደረገ ይገኛል።