ባይደን የሚቀለብሷቸው የትራምፕ ውሳኔዎች የትኞቹ ናቸው?

ባይደን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን 50 ዓመታት በፖለቲካው ውስጥ አሳልፈዋል።

በአስተዳደር ዘመናቸው ይወስዷቸዋል ተብለው ከሚጠበቁ እርምጃዎች አንዱ አሜሪካን ወደ ፓሪሱ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት መመለስ ነው።

የቀድሞው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ያስተላለፏቸው አወዛጋቢ ውሳኔዎችን ባይደን ይቀለብሳሉ ተብሎም ይጠበቃል።ከነዚህ መካከል በሙስሊም አገራት ዜጎች ላይ ተጥሎ የነበረው የጉዞ እገዳ ይገኝበታል።

ከባይደን አጀንዳዎች አንዱ አሜሪካን ወደ ዓለም ጤና ድርጅት አባልነቷ መመለስ ነው። ትራምፕ ድርጅቱ ለቻይና የወገነ ነው ብለው ከድርጅቱ መውጣታቸው አይዘነጋም።

ባይደን ከዓለም ጤና ድርጅት በተጨማሪ አሜሪካን ወደ ፓሪሱ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነትም ይመልሳሉ ተብሏል።

ከሙስሊም አገራት ወደ አሜሪካ የሚጓዙ ሰዎች ላይ ተጥሎ የነበረውን ክልከላ ባይደን ያነሳሉ።

ከነዚህ ባሻገር በወረርሽኙ ሳቢያ ከቤታቸው እንዲወጡ የተገደዱ ዜጎች ተጨማሪ የመኖሪያ ጊዜ ይፈቀድላቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።

ከባይደን ተጠባቂ እርምጃዎች ዋና ዋናዎቹን እንመልከት፦

ጭምብል ማድረግ ግዴታ ይሆናል

በወረርሽኙ ሳቢያ በአሜሪካ ከ400 ሺህ በላይ ሰዎች ሞተዋል። አዲሱ አስተዳደር በቀዳሚነት ከሚያተኩርባቸው ጉዳዮች አንዱም ኮሮናቫይረስ ነው።

ባይደን ወረርሽኙን "አስተዳደራችን ከሚገጥመው ፈተናዎች አንዱ ነው" ብለውታል። ቫይረሱን ለመከላከል የጥንቃቄ እርምጃዎችን ለመተግበርም ቃል ገብተዋል።

የመንግሥት ይዞታ በሆኑ ቦታዎችና በጉዞ ወቅት የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ማድረግ ከሚያስተላልፉት ውሳኔ አንዱ ይሆናል።

በእርግጥ ባይደን ይህንን ውሳኔ የሚተገብሩበት የሕግ ማዕቀፍ የለም። ስለዚህም አገረ ገዢዎችን በግል ጥረታቸው ለማሳመን አቅደዋል።

ባይደን ሥልጣን በያዙ በመጀመሪያዎቹ 100 ቀናት ውስጥ ለ100 ሚሊዮን ሰዎች ክትባት ለመስጠት ወጥነዋል።

ይህንን የሚተገብሩት ያሏቸውን ክትባቶች ባጠቃላይ ለዜጎች በማከፋፈል ሲሆን፤ ለሁለተኛ ዙር ክትባት ተብሎ የሚቀመጥ ጠብታ አይኖርም ማለት ነው።

የምጣኔ ሀብት ውሳኔዎች

ከቤታቸው በግድ እንዲወጡ ተወስኖባቸው ለነበሩ ሰዎች ጊዜ መስጠት ከባይደን አስተዳደር ከሚጠበቁ ውሳኔዎች ዋነኛው ነው።

መንግሥት ለተማሪዎች የሚሰተውን የገንዘብ ድጋፍ ያስቀጥላሉም ተብሏል

ካቢኔያቸው ለሠራተኛው ማኅበረሰብ እፎይታ የሚሰጥ የምጣኔ ሀብት ውሳኔ እንዲያሳልፍ ያዛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ኮሮናቫይረስ ጫና ላሳደረበት የአገሪቱ ምጣኔ ሀብት የ1.9 ትሪሊዮን ዶላር ድጋፍ ለማድረግ መታቀዱ ይታወሳል። ምክር ቤቱ እቅዱን ካጸደቀ አሜሪካውያን በነፍስ ወከፍ 1 ሺህ 400 ዶላር ያገኛሉ።

በቀጣይ 100 ቀናት ውስጥ ትምህርት ቤቶች ጥንቃቄ በተሞላው መንገድ ይከፈታሉ።

የትራምፕን አወዛጋቢ የግብር ቅነሳ ባይደን እንደሚቀለብሱ ተገልጿል።

እአአ 2017 ላይ ትራምፕ ያሳለፉት የግብር ቅነሳ ባልተገባ መንገድ ሀብታሞችን የጠቀመ ነው ሲሉ ባይደን ይተቻሉ።

ከዚህ ባሻገር ባይደን የአሜሪካ ድርጅቶች በውጪ አገራት በሚያደርጓቸው የንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ የሚጣለውን ግብር ለመጨመር ወጥነዋል። ይህ እውን እንዲሆን የግብር ፖሊሲያቸውን ምክር ቤቱ ማጽደቅ አለበት።

የአየር ንብረት ለውጥን በተመለከተ

ባይደን ሥልጣን በያዙበት የመጀመሪያው ቀን አሜሪካን ወደ ፓሪሱ የአየር ንብረት ለውጥ እንደሚመልሱ አስታውቀዋል።

የፓሪሱ ስምምነት የዓለምን የሙቀት መጠን ከ2.0 ሴንቲ ግሬድ በታች ማድረግን ያካትታል።

ትራምፕ አሜሪካን ከዚህ ስምምነት አስወጥተዋት ነበር።

ባይደን የአየር ንብረት ለውጥን በተመለከተ ጥብቅ እርምጃዎች እንደሚወስዱ ይጠበቃል። ይህም በመጀሪያዎቹ 100 የሥልጣን ቀናት ውስጥ የአየር ንብረት ለውጥ ውይይት ማካሄድን ያካትታል።

በ2050 የአሜሪካን የካርቦን ልቀት ዜሮ የማድረስ እቅድም አላቸው።

የስደተኞች ፖሊሲ ለውጥ

ትራምፕ ሥልጣን በያዙ በሰባተኛ ቀን ነበር በሙስሊም አገራት ዜጎች ላይ የጉዞ እገዳ የጣሉት።

እገዳው የኢራን፣ ሊቢያ፣ ሶማሊያ፣ ሶርያ፣ የመን ዜጎችን እንዲሁም የቬንዝዌላ እና የሰሜን ኮርያ ዜጎችን የሚያግድ ነው።

ይህ ውሳኔ በባይደን አስተዳደር ዘመን ይሻራሉ ተብለው ከሚጠበቁ መካከል ይጠቀሳል።

ከ11 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰነድ አልባ ስደተኞች ዜግነት ማግኘት የሚችሉበትን ሥርዓት ለምክር ቤት እንደሚልኩ ተገልጿል።

ወደ አሜሪካ የሚጓዙ ህጻናት ዜግነት የሚያገኙበት ዝርዝር ውስጥ የሚገቡበት አሠራር በባይደን ዘመነ መንግሥት እውን ይሆናሉ ተብለው ከሚጠበቁት አንዱ ነው።

ባይደን የምርጫ ቅስቀሳ ሲያደርጉ 545 ስደተኛ ልጆችን ከቤተሰቦቻቸው ጋር ለመመለስ ቃል ገብተው ነበር።

ትራምፕ በተደጋጋሚ ያወሩለት የነበረውን በአሜሪካና ሜክሲኮ መካከል የሚገነባውን የድንበር ግድግዳ ፕሮጀክት ባይደን ያስቆሙታል።

ዘረኛና ኢፍትሐዊ ውሳኔዎችን መሰረዝ

ዘረኛና ኢፍትሐዊ የተባሉና በርካቶችን ከቤት ባለቤትነት እንዲሁም ከጤና መድህን ተጠቃሚነት ያገዱ ውሳኔዎችን ባይደን ይሰርዛሉ ተብሏል።

በመጀመሪያዎቹ 100 ቀናት ከሚወስዷቸው እርምጃዎች መካከል የፖሊስ ተቋምን ዳግመኛ ማዋቀር ቀዳሚው ነው።

በወንጀል ተጠርጥረው በሚታሰሩ ሰዎች አነስተኛ የእስራት ጊዜ እንዲፈረድባቸው የሚያስችልና ማኅበረሰብ አቀፍ ፓሊስን የሚያስተገብር ፓሊሲም ከባይደን ይጠበቃል።

የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪዎች መብት

ባይደን የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪዎችን ከጥቃት የሚከላከሉ እንዲሁም በትምህርት ቤትና በወታደራዊ አገልግሎት ዘርፍ ያለውን መድልዎ የሚገቱ ውሳኔዎች ለማስተላለፍ ቃል ገብተዋል።

ይህንን ውሳኔ በምክር ቤቱ አማካይነት በምን ያህል ጊዜ ውስጥ እንደሚያሳልፉ ግን ግልጽ አይደለም።

ከባይደን ከሚጠበቁ ለውጦች ሌላው አሜሪካ ከወዳጅ አገሮቿ ጋር ያላትን ግንኙነት ማደስ ነው።