ፑቲን ቅንጡ ቤተ መንግሥት ማስገንባታቸውን 'የሚያጋልጠው' ቪድዮ

አሌክሴ ናቫልኒ

የፎቶው ባለመብት, YOUTUBE/ALEXEI NAVALNY

የሩስያው ፕሬዘዳንት ቭላድሚር ፑቲን ቅንጡ ቤተ መንግሥት ለመገንባት በሕገ ወጥ መንገድ ገንዘብ ማፍሰሳቸውን የሚያሳየው የምርመራ ቪድዮ በተለቀቀ በጥቂት ቀናት ውስጥ ከ20 ሚሊዮን በላይ ተመልካች አግኝቷል።

ቪድዮው የተለቀቀው በሩስያዊው ተቃዋሚ አሌክሴ ናቫልኒ ቡድን ነው።

ናቫልኒ ሩስያ፣ ሞስኮ ሲደርስ በቁጥጥር ስር የዋለው ከቀናት በፊት ነበር።

የምርመራ ቪድዮው እንደሚያሳየው፤ ቤተ መንግሥቱ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር ወጥቶበታል። "በታሪክ ትልቁ ጉቦ ነው" በማለት በቪድዮው ተገልጿል።

ክሬምሊን ቤተ መንግሥቱ የፑቲን አይደለም ብሏል።

በደቡብ ሩስያ ብላክ ሲ አካባቢ የሚገኘው ቤተ መንግሥት የሞኖኮ 39 እጥፍ ስፋት እንዳለው ተገልጿል።

ቪድዮው የተለቀቀው ናቫልኒ ከጀርመን ወደ ሩስያ ከሄደ ከሁለት ቀን በኋላ ነበር።

ናቫልኒ በቅድመ ምርመራ ለ30 ቀናት የታሰረ ሲሆን፤ ገንዘብ በመበዝበር የቀረበበትን ክስ በመጣሱ በቁጥጥር ስር መዋሉ ተገልጿል። እሱ ግን እስሩ ፖለቲካዊ ነው ይላል።

የፎቶው ባለመብት, YOUTUBE/ALEXEI NAVALNY

የ44 ዓመቱ ተቃዋሚ ባለፈው ነሐሴ ተመርዞ ለሞት ተቃርቦ ነበር። ለመመረዙ ተጠያቂው ፑቲን እንደሆኑ ቢናገርም፤ የሩስያ መንግሥት እጁ እንደሌለበት አስታውቋል።

ቪድዮው ምን ያሳያል?

የምርመራ ቪድዮው እንደሚያሳው ቤተ መንግሥቱ የተሠራው በፑቲን የቅርብ ሰዎች ሕገ ወጥ የገንዘብ ድጋፍ ነው። የነዳጅ ምርት ባለሥልጣኖች እና ቢሊየነሮች ከነዚህ መካከል ናቸውም ተብሏል።

ናቫንሊ በቪድዮው "በዚህ ገንዘብ ለአለቃቸው ቤተ መንግሥት ሠርተዋል" ብሏል።

የሩስያ ብሔራዊ የምርመራ ተቋም ቤተ መንግሥቱ ዙርያ ያለው 27 ስኩዌር ማይል መሬት ባለቤት እንደሆነም በቪድዮው ተጠቁሟል።

ሕንጻው ውስጥ ካዚኖ (መቆመሪያ)፣ የበረዶ ሆኪ መጫወቻና ወይን ማቀነባበሪያ ይገኛል ተብሏል።

"ለመጣስ የሚከብድ አጥር አለው። ራሱን የቻለ ወደብና ቤተ ክርስቲያን አለው። በረራ ማድረግ ክልክል ነው። የድንበር ላይ ጥበቃ ኃይልም አለው። ሩስያ ውስጥ ያለ ራሱን የቻለ አገር ነው" ሲል ናቫንሊ ተናግሯል።

ናቫንሊ በጸረ ሙስና ንቅናቄው ይታወቃል። እአአ 2018 ላይ ፑቲን ተቀናቃኝ ሆኖ ምርጫ ሊወዳደር ሲል ገንዘብ የመበዝበዝ ክስ ተመስርቶበታል።

ታዋቂው ሩስያዊ ተቃዋሚ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተከታዮች አሉት።

የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፐስኮቭ በቪድዮው ላይ የተባሉት ነገሮች "ሐሰት ናቸው" ብለዋል። ፕሬዘዳንቱ "ምንም ቤተ መንግሥት የላቸውም" ሲሉም ቃል አቀባዩ አስተባብለዋል።

22 ሚሊዮን ተመልካቾች ያገኘው የምርመራ ቪድዮ የሚገባደደው፤ ሕዝቡ ተቃውሞውን በአደባባይ እንዲገልጽ በማሳሰብ ነው።

"ከተበሳጩ ሰዎች 10 በመቶው እንኳን የተቃውሞ ሰልፍ ቢያደርጉ መንግሥት ምርጫውን ለማጭበርበር አይደፍርም" ሲል ናቫንሊ ተናግሯል።

ናቫንሊ የተመረዝኩት በፑቲን ነው ብሎ ወደ ሩስያ መመለሱ በርካቶችን አስገርሟል። ሆኖም ግን ማረሚያ ቤት ሆኖ ቪድዮው ከተለቀቀ በኋላ ደጋፊዎቹ ተቃውሞ እንዲካሄድ እያነሳሱ ነው።

የናቫንሊ እጣ ፈንታ ምን ይሆናል?

የካቲት 2 ናቫንሊ ፍርድ ቤት ይቀርባል።

2014 ላይ በፍርድ ቤት የተወሰነበት የሦስት ዓመት ተኩል እስር ስለመጽናቱም ውሳኔ ይተላለፋል።

ከሦስት ቀናት በኋላ በድጋሚ ፍርድ ቤት ቀርቦ የሁለተኛው ዓለም ጦርነት ጀግኖችን ስም የማጥፋት ክሱ ይታያል።

ናቫንሊ ከተመረዘ በኋላ ጀርመን ውስጥ ህክምና ሲከታተል ነበር።

ወደ ሩስያ ከተመለሰ እንደሚታሰር ማስጠንቀቂያ ቢሰጠውም ወደ አገሩ ከመመለስ ወደኋላ አላለም።

የቀረበበትን ክስ "ፍትሕ ላይ መቀለድ ነው። ሕገ ወጥነት መንሰራፋቱን ያሳያል" ሲል ተችቷል።

2018 ላይ የአውሮፓ የሰብአዊ መብት ፍርድ ቤት፤ የናቫንሊ ክስ "የዘፈቀደ ነው" ብሎ ነበር። መታሰሩ ከዚህ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ጋር የሚቃረን ነው የሚል ጥያቄ ተነስቷል።