ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ 44 የአማፂያን ታጣቂዎችን መግደሏን አሳወቀች

የሩዋንዳ ሰላም አስከባሪዎች

የፎቶው ባለመብት, FLORENT VERGNES

የማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ የጦር መኮንኖች መዲናዋ ባንጉይን ከበው ነበር ያላቸውን 44 የአማፂያን ታጣቂዎችን መግደላቸውን አሳውቀዋል።

አማፂያኑ በቅርቡ የተመረጡትን ፕሬዚዳንት ፎስ አርቸንግ ቱዋዴራ በኃይል ለመገልበጥ በሚል ከተማዋን እንደከበቡ ተነግሯል።

የመንግሥት ቃለ አቀባይ ለፈረንሳዩ ዜና ወኪል እንደተናገሩት ወታደሮቹ ከሩሲያ ልዩ ኃይል ጋር በመተባበር ቦዳ የተባለችውን ከተማ መቆጣጠር እንደቻሉ ነው።

ከመንግሥት በኩል የሞተ ሰው ባይኖርም ከአማፂያኑ በኩል ግን ከቻድ፣ ሱዳንና ፉላኒ ብሔር የተውጣጡ ቅጥር ወታደሮች እንደተገደሉ መንግሥት በፌስቡክ ላይ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ከመንግሥት የወጣውን መረጃ የሚያጣራ ነፃ አካል አልተገኝም።

አማፂው ቡድን ሶስት አራተኛውን የአገሪቱን ክፍል በቁጥጥር ስሩ ያለ ሲሆን በቅርቡም ቡድኑን ለመታገል በሚል የአገሪቱ መንግሥት ለአስራ አምስት ቀናት የሚሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አስተላልፏል።

በአገሪቱ ያሉ ስድስት ከፍተኛ ታጣቂ ቡድኖች በታህሳስ ወር ኃይላቸውን በማጣመር 'ኮኦሊሽን ኦፍ ፓትሪየትስ ፎር ቸንጅ' የሚባል አንድ ቡድን መስርተዋል።

ነገር ግን መዲናዋ ከ12 ሺህ በሚበልጡ ከተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከባሪ የተውጣጡ ወታደሮች፣ የማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ወታደሮችና የሩሲያና ሩዋንዳ ልዩ ኃይሎች በመተባበር በከባድ ጦር መሳሪያ እየጠበቋት ይገኛሉ።

የተባበሩት መንግሥታት አማፂ ቡድኖቹ ዋና መዲናዋን ለመቆጣጠር በሚል ከከተማዋ ጋር የሚያገናኙ ሶስት ዋና መንገዶችን ዘግተዋል በማለት አስጠንቅቋል።

አገሪቱ ባለፈው ወር ባደረገችው ምርጫ ለሁለተኛ ጊዜ ያሸነፉት ፕሬዚዳንት ፎስ አርቸንግ ቱዋዴራ ማሸነፋቸውን አማፂው ቡድን አይቀበለውም።

ከዚህም ጋር ተያይዞ በግጭት እየተናጠች ባለችው የማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቿም ወደ ጎረቤት አገር ተሰደዋል።