የፑቲንን አስተዳደር ሙስና የሚታገሉት የሩስያ ሴቶች

የፑቲንን አስተዳደር ሙስና የሚታገሉት የሩስያ ሴቶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ወንዶች ጎልተው የወጡበትን የሩስያ ፖለቲካ ለመለወጥ ሙስናን የሚቃወሙ ሴቶች ቆርጠው ተነስተዋል።

እነዚህ ሴቶች የለውጥ ተምሳሌት ተብለዋል። ከተቃዋሚው አሌክሲ ናቫልኒ ጋር ይሠራሉ።

ናቫልኒ የጸረ ሙስና ንቅናቄን ማዕከል ያደረገው ኤፍቢኬ ፓርቲውን ለፓርላማ ምርጫ ሲያዘጋጅ የእነዚህ ሴቶች ሚና ጉልህ ነው።

የሩስያ ፓርላማ ለፕሬዘዳንት ቭላድሚር ፑቲን ታማኝ ነው። አብላጫውን ቁጥር የያዙትም ወንዶች ናቸው። ከታህታይ ምክር ቤቱ የሴቶች ድርሻ 16% ሲሆን ከላዕላይ ምክር ቤቱ ደግሞ 17% መቀመጫ አላቸው።

በናቫልኒ ፓርቲ ወንዶችም ሴቶችም ቁልፍ ሚና አላቸው። በንቅናቄው ጎልተው የወጡ ሴቶች እነማን እንደሆኑ እናስተዋውቃችሁ።

ዩሊያ ናቫልኒያ

እአአ በ2000 ከናቫልኒ ጋር ትዳር የመሠረተችው ዩሊያ ሕይወቷ ፖሊስ ጣቢያና ፍርድ ቤት በመመላለስ የተሞላ ሆኗል። ቤቷም በተደጋጋሚ ተበርብሯል።

ቱርክ የተዋወቁት ጥንዶች ሁለቱም 44ኛ ዓመታቸውን ይዘዋል።

ዩሊያ ያጠናችው ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሲሆን፤ ባንክ ውስጥ ሠርታለች። ቤታቸው ሞስኮ ሲሆን፤ ሴት ልጃቸው ዳርያ አሜሪካ እየተማረች ነው።

ዩሊያ አሁን ከመገናኛ ብዙኃንና ከመንግሥት ስለላ ሸሽታ ጀርመን ነች።

በመላው ሩስያ እሷን የሚደግፉ ሴቶች ቀይ ለብሰው ፎቶ በመነሳት ኢንስታግራም ላይ ለጥፈዋል።

ባለቤቷ የሁለት ዓመት ከስምንት ወር እስር ሲፈረድበት ቀይ ለብሳ ነበር ፍርድ ቤት የተገኘችው። የፋሽን ጋዜጠኛዋ ካይታ ፌዶሮቫ ይህንን በማስመልከት ቀይ ከለበሰች ወዲህ ነው ሌሎች ሴቶች ቀይ በማድረግ ድጋፋቸውን ማሳየት የጀመሩት።

"አትዘኚ። የከፋ ነገር አይከሰትም" በማለት ነበር ባለቤቷ ናቫልኒ ከመታሰሩ በፊት የተሰናበታት።

ወደ ፓለቲካ ተሳትፎ የገባችው ባለፈው ነሐሴ ባለቤቷ ተመርዞ ለሞት በተቃረበበት ወቅት ነበር። ባለቤቷ ከተመረዘ በኋላ ከሰርቢያ ወደ ጀርመን እንዲወሰድ የወሰነችው እሷ ነበረች።

ከሰመመን ሲነቃ "ትራሴን ታስተካክልልኝ የነበረችው እሷ እንደነበረች አስታውሳለሁ። እስክትመጣ እጠብቃት ነበር" ብሏል ናቫልኒ።

ባለቤቷ አገግሞ ከጀርመን ወደ ሩስያ ሲመለስ ታስሯል። እስሩን በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ ካደረጉ አንዷ ደግሞ እሷ ነበረች።

የባለቤቷን ጸረ ሙስና ተቃውሞ የምትደግፈው ዩሊያ፤ ሰልፍ ከወጣች በኋላ 270 ዶላር ተቀጥታለች።

ሊቦቭ ሶቦል

የ33 ዓመቷ ጠበቃ በናቫልኒ ቡድን ውስጥ ከሚታወቁ አንዷ ናት። አሁን በቁም እስር ላይ ትገኛለች።

እሷና ሌሎችም የናቫልኒ ደጋፊዎች ከተቃውሞ ሰልፉ በኋላ ታስረዋል። ለመታሰራቸው ምክንያት የተባለው የኮቪድ-19 መከላከያ መርህን መጣስ ነው።

ናቫልኒ ሙስናን የሚያጋልጥበትን የዩቲዩብ ገጽ ፕሮዲውስ የምታደርገው ሊቦቭ ናት። ገጹ በሚሊዮኖች የሚቆጡ ተከታዮች አሉት።

እአአ በ2019 ባለሥልጣኖች ከሞስኮ የምርጫ ኮሚቴ ጎትተው ሲያስወጧት የሚያሳይ ቪድዮ ካሰራጨች ወዲህ ታዋቂነቷ ጨምሯል።

ከዚያ በኋላ ለአንድ ወር የረሀብ አድማ አድርጋለች። እሷና ሌሎችም የግል እጩዎች በሞስኮ ከተማ አስተዳደር ምርጫ እንዳይሳተፉ ታግደዋል።

መስከረም ላይ ለሩስያ ፓርላማ ምርጫ የመወዳደር እቅድ አላት።

ከ2011 ጀምሮ በናቫልኒ የጸረ ሙስና ፕሮጀክት ውስጥ ሠርታለች።

2014 ላይ ሚሮሳለቫ የተባለች ልጅ የወለደች ሲሆን፤ በሥራዋ ምክንያት በ2016 ባለቤቷ ጥቃት እንደደረሰበት ትናገራለች።

በጸረ ሙስና ንቅናቄ ምክንያት እሷም ናቫልኒም በተደጋጋሚ ክስ ተመስርቶባቸዋል።

ከከሰሷቸው መካከል ዩቭጌኒ ፕሪጎዚን የተባለው ባለሀብት ይጠቀሳል። ለክሬምሊን ቅርብ የሆነው ባለጸጋው "የፑቲን ሼፍ" በሚል ይታወቃል።

አንስቲዥያ ቫስሌይቫ

ዶክተር ናት። በዚህ ወር ፖሊሶች ቤቷን ሲበረብሩ ችላ ብላቸው የቤትሆቨንን ሙዚቃ ስትጫወት የሚያሳይ ቪድዮ ተለቆ ዝነኛ ሆናለች።

የ36 ዓመቷ አንስቴዥያ ለናቫልኒ ቅርብ የሆነ የሀኪሞች ቡድን ትመራለች። 2017 ላይ ናቫልኒ አይኑ ላይ ጉዳት ሲደርስበት እሷ ነበረች ያከመችው።

የሁለት ልጆች እናት ስትሆን፤ ናቫልኒን የሚደግፍ ሰልፍ በማካሄዷ የቁም እስር ላይ ትገኛለች።

ከዚህ ቀደም ከሞስኮ ታይምስ ጋር ባደረገችው ቃለ ምልልስ የሩስያ መንግሥት ለኮሮናቫይረስ የሰጠውን ምላሽ ተችታለች።

እናቷ ሀኪም እንደነበሩና የፖለቲካ ተሳትፎ ለማዳበር የተነሳሳችውም በዚህ ምክንያት እንደሆነ ትናገራለች።

"የአገራችን ጤና ሥርዓት ውስጥ ያለውን እያዩ ፖለቲካ ውስጥ አለመሳተፍ አይቻልም" ትላለች።

ኪራ ያርሚሽ

ከ2014 ጀምሮ የናቫልኒ ቃል አቀባይ ስትሆን፤ በቁም እስር ላይ ትገኛለች።

ወደተለያዩ አገሮች ሲጓዝ አብራው ትሄዳለች። ነሐሴ ላይ አውሮፕላን ውስጥ ሳለ ተመርዞ ራሱን ሲስትም አብረው እየተጓዙ ነበር።

የሞስኮ ዓለም አቀፍ ተቋምን የተቀላቀለችው የቴሌቭዥን የተሰጥኦ ውድድር አሸንፋ ሲሆን፤ ያጠናችው ጋዜጠኝነት ነው።

በጸረ ሙስና ንቅናቄ ከታሰረች በኋላ በማረሚያ ቤት ስለሚገኙ ሴቶች የሚያትት ረዥም ልቦለድ ጽፋለች።

በናቫልኒ የዩቲዩብ ገጽም ብዙ መሰናዶዎች መርታለች።

ኦልጋ ሚካሎቫ

የናቫልኒ ጠበቃ ናት። በአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ልምድ አላት።

2017 ላይ ሩስያ ናቫልኒን እና ወንድሙን ገንዘብ አጭበርብራችኋላ ብላ ከሳ ነበር። ፍርድ ቤቱ ግን ክሱን ውድቅ አድርጎ የሩስያ የፍትሕ ሚንስትር በሺዎች የሚቆጠር ዶላር ካሳ እንዲከፍል ወስኗል።

ናቫልኒ ከጀርመን ወደ ሩስያ ሲመለስ በቁጥጥር ሥር የዋለው ከዚህ ክስ ጋር በተያያዘ ነው።

ኢኮ ሞስኪቭ ከተባለ የራድዮ ጣቢያ ጋር ባደረገችው ቆይታ ሕገ አውጪውና ሕግ አስፈጻሚው መካከል ልዩነት የለም ስትል ተችታለች።

የአውሮፓ ትልቁ የሰብዓዊ መብት ፍርድ ቤት በሆነው ካውንስል ውስጥ ለናቫልኒ ጥብቅና የምትቆመውም ኦልጋ ናት።