የኒኪ ሚናጅ አባት በመኪና ተገጭተው ሞቱ

ኒኪ ሚናጅ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የኒኪ ሚናጅ አባት ኒው ዮርክ ውስጥ በአንድ አሽከርካሪ ተገጭተው ህይወታቸው ማለፉ ተገለጸ፡፡

ፖሊስ በሰጠው መግለጫ መሠረት ሮበርት ማራጅ አርብ ምሽት በሎንግ አይላንድ በሚገኝ አንድ መንገድ ላይ ሲጓዙ ነበር ተገጨተው ህይወታቸው ያለፈው፡፡

አሽከርካሪው ከአካባቢው ከተሰወረ በኋላ የ 64 ዓመቱ ግለሰብ ወደ ሆስፒታል ቢወሰዱም በሚቀጥለው ቀን ህይወታቸው አልፏል፡፡

የናሳው ካውንቲ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊዎች “ምርመራው እየተካሄደ ነው” ሲሉ የጠቀሱ ሲሆን ዘፋኟ ግን እስካሁን በጉዳዩ ላይ በይፋ ምንም ነገር አልተናገረችም፡፡

መግለጫው ሮበርት ማራጅ የኒኪ ሚናጅ አባት ናቸው ባይልም፣ የፖሊስ ቃል አቀባይ አባቷ መሆናቸውን ለኤኤፍፒ አረጋግጧል፡፡

በትክክለኛ ስሟ ኦኒካ ታንያ ማራጅ-ፔቲ ተብላ የምትጠራዋ ኒኪ ሚናጅ በትሪኒዳድ እና ቶቤጎ የተወለደች ሲሆን በኒው ዮርክ ከተማ ኩዊንስ በሚባለው አካበቢ ነው ያደገችው፡፡

ለ 10 ግራሚ በእጩነት የቀረበች ሲሆን አምስት የኤምቲቪ ቪዲዮ ሚዩዚክ አዋርድን አሸንፋለች።

በጎርጎሮሳዊያኑ 2019 ‘ጡረታ መውጣቷን’ አስታውቃ የነበር ቢሆንም ከዚያ በኋላም አዲስ ሙዚቃ ለቃለች፡፡

የ38 አመቷ ዘፋኝ በቅርቡ ከቅጂ መብት ውዝግብ ጋር በተያያዘ 450,000 ዶላር ለትሬሲ ቻፕማን በመክፈል ለጉዳዩ እልባት ሰጥታለች፡፡