"በምርጫ ወቅት በመመታቴ የስምንት ወር ፅንሴ ጨነገፈ" ፖለቲከኛዋ አስካለ

ወይዘሮ አስካለ

የፎቶው ባለመብት, Askale Haile

ሰኔ፣ 1984 ዓ.ም በኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፏቸው ሶስት አስርት አመታትን ላስቆጠሩት ወይዘሮ አስካለ ኃይሌ የምትረሳ ወር አይደለችም።

ፓርቲያቸውን ወክለው የመጀመሪያ ምርጫ የተወዳደሩባት እንዲሁም በሰደፍ ተመትተው የስምንት ወር ፅንሳቸው የጨነገፈችባት ወቅት ናት።

በአሁኑ ወቅት 29 አመት ይሆናት ነበር በማለትም በኃዘን " በሆዴ ውስጥ የነበረችው ልጅ አልተፈቀደላትም" ይላሉ ከቢቢሲ ጋር በስልክ በነበራቸው ቆይታ።

'ልጃቸውን' እንዴት አጡ?

ወቅቱ 1984 ዓ.ም ነበር። የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ግንባር ስልጣን መቆጣጠሩን ተከትሎ የሽግግር መንግሥት ተመሰረተ፤ በሽግግር ወቅቱም እንደ ህገ መንግሥት የሚያገለግል ቻርተር ፀድቋል።

በቻርተሩ መሰረት ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከታዋቂ ግለሰቦችና ከሌሎች አባላት የተውጣጡ ከ87 የማይበልጡ የምክር ቤት አባላትን ይዟል የሽግግር መንግሥቱ የተወካዮች ምክር ቤት።

ከዚህም ጋር ተያይዞ ነበር የብሔራዊ፣ ክልላዊ፣ የዞን እና የወረዳ ምክርቤት ምርጫዎችን ለማካሄድ ሰኔ ቀን ቀጠሮ የተቆረጠው።

የሽግግር መንግሥቱ ተሳትፎ የነበረው ኦነግ ለሰኔ የተቀጠረው ምርጫ የሚያበቃ ዝግጅት የለም ብሎ ከምርጫ የወጣበት ወቅት ነበር።

ወይዘሮ አስካለም የትጥቅ ትግል ያካሂድ የነበረውን የኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ ህብረት ኢዲዩን ወክለው ነበር የመጀመሪያ ምርጫ ላይ የተሳተፉት።

በወቅቱ ክልል 14 በነበረችው አዲስ አበባ ለወረዳ ምክር ቤት አባልነት ወረዳ 13 ቀበሌ 03ን ወክለው እጩ ተወዳዳሪ ነበሩ።

የምርጫው ቀንም ደረሰ። እሳቸውም ሆነ ሌሎች የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ከምርጫ ጣቢያው ገለል ብለው ነበር።

ወይዘሮ አስካለ እንደሚሉት የብሔራዊ፣ ክልላዊና የወረዳ ምክር ቤት አባላት ምርጫ አስፈፃሚ ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ መሰረት በምርጫው ቀን እጩ ተወዳዳሪዎች ከምርጫ ጣቢያው 500 ሜትር ርቀት መገኘት አለባቸው የሚል አንቀፅ አስፍሯል።

እሳቸውም ሆነ ሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች ይሄንን ህግ ቢያከብሩም የገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ እጩ ተወዳዳሪ በምርጫ ጣቢያ "እንደፈለገች እየገባች፣ እየወጣች ነው" ሲሉ ያስቀመጧቸው ታዛቢዎች ጥቆማ ላኩባቸው።

የምርጫው ጣቢያ ያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት አካባቢ ሲሆን ወይዘሮ አስካለ ሁኔታውን ሲሰሙ ወደቦታው አቀኑ።

በቦታው ለነበሩት የምርጫ ሂደቱን የሚቆጣጠሩት የፀጥታ ኃይሎች ለምን የገዢውን ፓርቲ እጩ ተወዳዳሪ እንደሚያስገቡ ጠየቁ።

"የሚታይ ሁኔታ ካለ እኛም እንይ አሉ" የፀጥታ ኃይሎቹ በምላሹ ዘወር በሉ ብለው ማስፈራራት ጀመሩ። እሰጣገባውም በዚያ መንገድ ተጀመረ።

እሳቸውም "በምን ምክንያት እኔን ብቻ ታባርረኛለህ? እኔ እኮ እጩ ነኝ። የኦህዴድ/ ኢህአዴግ እጩ ተወዳዳሪ ከገባች፤ እኔ የማልገባበት ምክንያት ምንድን ነው ብዬ ለመግባት ስሞክር ዘወር በይ ብሎ ገፋኝ፤ በሰደፉ ሆዴን መታኝ" ይላሉ።

"ያኔ ግብታዊ ነበሩ፤ ስርአት የላቸውም፤ ነገሩ ያኔም አሁንም ያው ናቸው። የመሳሪያ ባለቤትነት ያለው ሁሉ በኃይል ነው" ይላሉ

በወቅቱ የስምንት ወር ነፍሰጡር የነበሩት ወይዘሮ አስካለ በሰደፍ ከተመቱባት እለት ጀምሮ በትንሹ ደም ይፈሳቸው ጀመር።

"ያው ምንድን ነው እያልኩ እጨነቅ ነበር" የሚሉት ወይዘሮ አስካለ ከምርጫው አስራ አምስት ቀናት በኋላም የሚፈሳቸው ደም በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሮ፤ አንዲት ዕለት፣ ሐምሌ 5፣ 1984 ዓ.ም የደም አበላ አደረጋቸው። ነፍስ ውጪ፣ ነፍስ ግቢ ሆነ።

ወደ ህክምና ቦታ ተወሰዱ።

"እኔ ከሞት ተረፍኩኝ ግን በሆዴ ውስጥ የነበረችው ልጅ አልተፈቀደላትም" ይላሉ። እሳቸው በህክምና ኃይል ህይወታቸው ቢተርፉም በአጭር የተቀጨችውን ልጃቸውን ሲያስቡ ያንገበግባቸዋል።

ምንም እንኳን ህፃኗ በፅንስ ብትጨነግፍም ወይዘሮ አስካለ ፅንሷን ሴት እንደሆነች አድርገው ነው የሚናገሩት።

የፅንሱ መጨንገፍ የእግር እሳት ብቻ ሳይሆን ወደ ቆራጥ ትግል እንዲገቡ ምክንያት መሆኑንም በሙሉ ልብ ነው የሚናገሩት።

ከሽግግር መንግሥት ምስረታው እስካሁን ባለው የፖለቲካ ህይወታቸው ቆይታ ያዩት ውጣ ውረድ ይህ ነው የሚባል አይደለም።

የፎቶው ባለመብት, Askale Haile

የምርጫ ተሳትፎ

ሴቶችን ባገለለው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ መሳተፍ ብቻ ሳይሆን በምርጫ ለማሸነፍም በርካታ ትግሎችን አድርገዋል።

ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘ በኋላ አገሪቷ ባካሄደችው ብሔራዊ ምርጫዎች ተሳትፈዋል- ከ1987 ዓ.ም ምርጫ በስተቀር።

ሆኖም በተሳተፉባቸው ምርጫዎች እሳቸው ብቻ ሳይሆኑ የተቃዋሚ ፖለቲከኞች የሚያገኙት ድምፅ በቁጥር አናሳ ነው።

"1፣ 2፣3 እያሉ ነው የሚለጥፉልን፤ በጣም ከሚገርመኝና ከሚያስደንቀኝ ታሪክ ልንገርሽ፤ እኔ ባለቤቴ፣ ልጆቼ አይመርጡኝም? ጎረቤቴና እህቴ አይመርጡኝም፤ አምስት ቤተሰብ ቢኖረኝ የአምስቱ ድምፅ የት ሄደ? ጌታ ያሳይሽ እስቲ! እና እንዲህ አድርገው እየቀለዱብን አጫፋሪ ሆነን እንደ ሙሽራ አጅበናቸው ነው የኖርነው" ይላሉ።

"ትክክለኛ ምርጫ የተደረገው በ1997 ዓ.ም ነው፤ ከዛ በፊት የተደረጉ ምርጫዎች የይስሙላ ናቸው።" ይላሉ

ሆኖም ደከመኝ፣ ሰለቸኝ ሳይሉ ምርጫ ቅስቀሳዎችን አካሂደዋል።

የምርጫ ቅስቀሳ ወጎች

ለወይዘሮ አስካለ ቅስቀሳ ሲነሳ ዋነኛ መሰረት እድሮች እንደሆኑ ይናገራሉ። "መቼም መነሻችን የሴት እድር ናት" ይላሉ።

ከእድሮች በተጨማሪም እቁብ፣ ከጎረቤት ጋር ሆነው ቡና በማፍላት በዋነኝነት ሴቶችን በመጥራት ፓርቲያችን ያቀደውን ያስረዳሉ።

በየመንደሩም የየራሳቸውን ደጋፊ ሰዎች አሰማርተው በየወረዳው፣ በየቀበሌውና በየሰፈሩ በዚህ ሰዓት ለቅስቀሳ ይመጣሉ ተብሎ ይነገራል። በሚወዳደሩባቸው ወረዳዎች ላይ ከታዛቢዎች ጋር አብረው ይዞራሉ።

ምንም እንኳን የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆነ መንግሥት የሚከተሏቸው ርዕዮተ ዓለማትም ሆነ የሚያወጧቸው ፖሊሲዎችም ሆነ በተደጋጋሚ የሚሰሙ ቃላት ኒኦ ሊበራሊዝም፣ ዲሞክራሲ፣ ፌዴራሊዝም ከበርካታ ኢትዮጵያውያን የተነጠሉ ቢሆንም ወይዘሮ አስካለ ማህበረሰቡ በሚገባውና በሚረዳው መልኩ እንደሚያስረዱ ይናገራሉ።

አንድ መንደር ውስጥ ውሃ፣ ጤና ጣቢያ፣ ትምህርት ቤት ከሌለ ፓርቲያቸው በወረዳው ያለውን ችግር የሚቀረፍበትን ከምሁራኖች እንዲሁም ከመንግሥት ጋር በመደራደር ያስፈፅማል ይላሉ።

እሳቸውን ቢመርጡ የሴቶችን ጥያቄዎች ወደፊት በማምጣት እንዲሁም ኃገራዊ ጉዳዮችን ጥያቄ በማቅረብና በመከራከር ወደ ውጤት የሚገቡበትን መንገድ እንደሚቀይሱና ከተጠናከሩም ለመንግሥትነት የማይበቁበት ምክንያት እንደሌለም ያስረዳሉ።

በተለያዩ ቦታዎች ሲቀስቅሱ አንዳንድ ሴቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችም ያስደነግጣቸው እንደነበር ያወሳሉ።

"ምን ለራስሽ ጥቅም ነው ብትመረጭ፤ 'እዛ ከገባሽ በኋላ መች ዘወር ብለሽ ታይናለሽ? እኛ እንደሆነ ከዚች ከችግራችን አንወጣም፤ አውቃችሁ ነው፤ ደግሞ የናንተ የፖለቲካ ድርጅት ምን ያህል ከመንግሥት ጋርስ ተደራድሮ የማስፈፀም አቅም አለው ብለው ያስደነግጡሻል" የሚሉት ወይዘሮ አስካለ አንዳንዶችም

"እናንተ ዝም ብላችሁ እንዲያው ለራሳችሁ ጥቅም ነው። አንድ ስራ አጥ ስራ ለማስያዝ ከሆነ በጣም ጥሩ ነው እንመርጥሻለን" የሚሉ እንዲሁም "ከናንተ ጋር ስራ አንፈታም ብለው ጥለውንም የሚሄዱ ሰዎች አሉ" ይላሉ።

ለዘመናት በፖለቲከኞች ባዶ ቃል መግባት የተሰላቹ ነዋሪዎች በርካቶች እንደሆኑ ይናገራሉ።

የሴቶች ወደ አደባባይ መውጣት እንደ ነውር ተደርጎ በሚታይበት ሁኔታ እንዲሁም በአገሪቱ ውስጥ ያሉት ማህበራዊ፣ ሃይማኖታዊና ሌሎች መዋቅሮችም ሴቶች በፖለቲካው እንዳይሳተፉ እክል ሆነዋል።

ከዚህም በተጨማሪም በርካታ ሴቶችም ትዳር አጋሮቻቸውን ፍቃድ ማግኘት እንዲሁ ቁልፍ ነገር መሆኑንም ወይዘሮ አስካለ ይረዳሉ።

በአንድ ወቅት ፈረንሳይ ለጋሲዮን አካባቢ ጉራራ ጊዮርጎስ የሚባል ቤተክርስቲያን አካባቢ ቅስቀሳ እያካሄዱ ነበር። ቅስቀሳውን እያደረጉ የነበረው በህብረት ሲሆን እሳቸውን ጨምሮ ሶስት ወንዶችና ሶስት ሴቶች ሆነው ነው።

በቅርበት የሚያውቋትንም ጓደኛቸውንም የሰፈሩን ሴቶች ሰብስባ እንድትጠብቃቸው ነገሯት። ቤቷ አካባቢ ሲደርሱ "ማን አለ?" ብለው መልዕክተኛ ላኩ። እሷም ከግቢው ወጣ ብላ ተጨንቃ መጣች። በወቅቱ ባለቤቷ ለምሳ እንደመጣና እሱ ስራ እስኪሄድ እንዲጠብቁ ነገሯቸው።

ወይዘሮ አስካለ እንደሚሉት ባለቤቷ እንዲህ አይነት የፖለቲካ ተሳትፎ ውስጥ በጭራሽ እንድትገባ አይፈልግም።

ባለቤቷም እስኪሄድ ሌላ ሰፈር ሄደው የአካባቢውን ሴቶች ሰብስበው ምርጫ እንዴት እንደሚመረጥ፤ ስለ ምልክቶቹ ተናገሩ። ከትንሽ ቆይታ በኋላ ጓደኛቸው ልጆች ሄዶ ባለቤቷ እንደሄደና መምጣት እንደሚችሉ ተነገራቸው።

በቦታው ሲደርሱም በጓሯቸው በርካታ ሴቶችን ሰብስባ ጠበቀቻቸው፤ የምርጫ ቅስቀሳውም ሆነ እንዴት እንደሚመረጥ እየተወያዩ ባሉበት ወቅት የጓደኛቸው ባለቤት እቃ ረስቶ ተመልሶ መጣ። "ምን አባቴ ይዋጠኝ፤ የሰው ትዳር አፈረስኩ ብዬ ተጨነቅኩኝ" ይላሉ።

"እሱም አስካለ ምን ሆነሻል አለኝ? እዚህ ለቅስቀሳ መጥቼ ከእንግዶች ጋር ውሃ ጠምቶን ነው አልኩኝ የእህቴ ቤት ነው ብየ መጣሁ አልኩት፤ ውሃ ክፍል እኔ ቤት የተዘረጋ መሰላችሁ እንዴ አለኝ እና በዚህ አለባብሰን አለፍነው፤ እኛም ጨርሰን ወጣን። መቼም እድሜ ልኬን አልረሳውም። " ይላሉ

ከዚህ ቀደም በእግራቸው ቤት ለቤት በመዞር፣ በሴት እድር፣ በእቁብ፣ በመተዋወቅና በጓደኝነት የነበረው የምርጫ ቅስቀሳ የተቀየረው በ1997 ዓ.ም ምርጫ ነው።

የ1997 ዓ.ም ምርጫ ቅስቀሳዎች በይፋ የሆኑበትና በመኪናም እንዲሁም ያለ እረፍት የቀሰቀሱበት ወቅት ሲሆን መራጭም እንደዚያ የተነሳሳበት ወቅት የለም ይላሉ። በተናጠል ሳይሆን በተደራጀ መልኩ በራሪ ወረቀት እየበተኑ ይቀሰቅሱ ጀመር።

የ1997 ዓ.ም ቅስቀሳው ብቻ ሳይሆን የተለያዩ ፓርቲዎች ተደራጅተው የመጡበት ወቅት ነበር። የወይዘሮ አስካለ ፓርቲ ኢዲዩም የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሃይሎች ህብረት የተባለውን ፓርቲ ከመሰረተቱት 15 ፓርቲዎች መካከል አንዱ ነው።

ፓርቲያቸው በዚህ ወቅት በተለያዩ የክልል ከተሞች እንዲሁ እየተዘወዋወሩ ቀስቅሰዋል። ከዚህም በተጨማሪ ወይዘሮ አስካለ ከ15 በላይ የክርክር መድረኮች ከነ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ፣ ዶክተር መረራ ጉዲና ጋር በመሆን ከተለያዩ የኢህአዴግ ባለስልጣናት ጋርም በመድረክ ላይ ተከራክረዋል።

በተለይም የምርጫ ቅስቀሳዎች ሲነሱ ሚያዝያ 30፣ 1997 ዓ.ምን ያስታውሱታል። ቅንጅት ሰላማዊ ሰልፍ የጠራበትና ህዝቡ ግልብጥ ብሎ የተመመበትና፣ በረዶ፣ ዶፍ እየወረደበት ለለውጥ የዘመረበት ወቅት ነው ይላሉ።

ባለቤታቸውን በሞት ያጡት ወይዘሮ አስካለ አምስት ልጆቻቸውን የማሳደግ ኃላፊነቱም የተጣለው በሳቸው ላይ ነው።

በዚህ ወቅትም ሙሉ ቀን ሲቀሰቅሱ ይውላሉ። ሌሊት ምግብ ሰርተው ወደ 10፡30 አካባቢ ሲሆን አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪ ለነበረው ልጃቸው ምግብ ለማድረስና ለማየት ይሄዳሉ።

"ሌሊት እንቅልፍ አይወስደኝም፤ ጭንቀቱም ደግሞ ብዙ ነው፤ ልጄን አፍነው ወሰዱት ይሆን? እንዲህ አደረጉት ይሆን ? እያልኩ በጭንቀት እብሰከሰካለሁ "የምን እንቅልፍ አመጣሽብኝ፤ ያን ጊዜ ሳስበው በጣም ይሰማኛል፤ ስሜቴን ይነካኛል" በሳግ በተቆራረጠ ድምፅ

"ሴት ፖለቲከኛ መሆን ትልቅ አደጋ አለው" የሚሉት ወይዘሮ አስካለ በተለይም በርካታ ሴቶች የቤተሰብ፣ መስሪያ ቤት እንዲሁም ሌሎች ኃላፊነት አደራርበው በፖለቲካው መሳተፍ በጣም ከባድ እንደሆነም ይናገራሉ።

"ሆደ ሰፊነት፤ ልበ ሙሉነት ያስፈልጋል። ተስፋ ያለ መቁረጥ ያስፈልጋል። ይሄ ይገጥመኝ ይሆን? ራስሽን ማሳመን አለብሽ" ይላሉ

ማስፈራሪያዎችና ዛቻዎች

በባለፉት አመታት በርካታ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አባላት ቢሯቸው ከመዘጋት ጀምሮ፣ የአባላት እስር፣ ማስፈራራሪያዎች እንደሚደርስባቸው ይናገራሉ።

በተለይም ምርጫዎች በሚቃረቡበት ወቅት በየሰፈሩ ፓርቲያቸውን ለማጠልሸት ይሰሩ የነበሩ ስራዎች በርካታ ናቸው ይላሉ። የምርጫ ፖስተሮቻቸው ላይ ንብ በመለጠፍ እንዲሁም ሌሎችንም ተግባራት ያከናውኑ ነበር የሚሉ ሲሆን ምርጫ ቦርድም ጋር ከሰው ነበር።

በተለይ ሴት ተቃዋሚ አባላት ከሆኑ የሴቶች ማህበር መታወቂያ እንዳያገኙ በማድረግና ተቃዋሚ ሴቶችን በማግለል ጫና ያደርሱ እንደነበር ያስታውሳሉ።

በተለያዩ ማህበራት ውስጥ በሚገኙ ድርጅቶችም የተቃዋሚ ሴቶችን እንደ ጠላት በማሳየት "ሰውን በጥቅማጥቅም ይዘውት ነበር" ይላሉ።

"የኢህአዴግ ማስፈራሪያ ብትሰፍሪው ብትሰፍሪው የሚያልቅ አይደለም፤ አይደለም ሌላውን ህዝብ እንዳይመርጥሽ ማድረግ ይቅርና ቤተሰቦችሽ መሃል ገብቶ አንጃ ይፈጥርብሻል። ይሄ መንግሥት የመጣው ለናንተ ነው፤ የናታችሁ ለኢዲዩ ማገልገል፤ ኢዲዩ ዘውድ አስመላሽ ድርጅት ነው" ይላሉ

ኢዲዪ ፊውዳላዊና የቡርዧ ስርአት ከማለትም በተጨማሪ በ1997 ዓ.ም በነበረው ምርጫ በወቅቱ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የምጣኔ ኃብት ተማሪ የነበረው ልጃቸውን ጠርተው እንዳስፈራሩትም ይናገራሉ።

" የኢዲዩን እንዲሁም የእናትህን አላማ ትደግፋለህ ወይ ብለው አስፈራሩት፤ በእናትህ ላይ ሰላይ ሁን ነው የምትሉኝ፤ ብሎ ጠየቃቸው? አላደርገውም፤ እኔ የራሴ ምርጫ አለኝ ያንን ደግሞ አላደርገውም የሚል ምላሽ ሰጥቷቸዋል"

ማስፈራሪያና ዛቻ በሳቸው እንዲሁም በልጃቸው ላይ ደርሷል የሚሉት ወይዘሮ አስካለ "ቤተሰቦቼ ላይ ከፍተኛ ስቃይ አድርገዋል" ይላሉ።

እሳቸውም ቢሆን በየጊዜው በተደጋጋሚ ታስረዋልም፤ ተፈትተዋልም። አስራ አምስት ቀን፣ ሃያ ቀናት በተደጋጋሚ ይታሰራሉ፤ ከዚያም ይፈታሉ።

የፖለቲካ ህይወት

ወይዘሮ አስካለ ኃይሌ አለሙ ተወልደው ያደጉት አዲስ አበባ ሲሆን የፖለቲካ ህይወታቸውም የሚጀምረው በ1960ዎቹ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ወቅት ነው።

መሬት ላራሹ በሚል የትግል ችቦ ሲቀጣጠል በወቅቱ የፈለገ ህይወት ዮርዳኖስ ተማሪና ገና ፍሬ ልጅ ቢሆኑም "ድንጋይ ወርውሬያለሁ" ይላሉ።

ትምህርታቸውን ጨርሰው አዲስ አበባና ውሃና ፍሳሽ ከተቀጠሩ በኋላ "ሴት በሴትነቷ ትከበር፤ አይቻልምና ያለሷ ለመኖር" የሚሉ መዝሙሮች የሴቶችን ጥያቄዎች ላይ አጫሩባቸው።

የሴቶች የውይይት ክበብም ተሳታፊ ሆኑ፤ የማርክሲዝምና ሌኒኒዝም ፅንሰ ሃሳቦችና ትምህርቶች መውሰድ ጀመሩ። የኢትዮጵያ ሰራተኞች ማህበር የአብዮት ጥበቃም ስልጠናም ወስደዋል፤ "አብዮተኛም ሆንኩ" ይላሉ።

የሰራተኛው ጥቅም መከበር አለበት በሚልም ቋሚ ተከራካሪ ሆኑ፤ የወዛደሩንም ጥቅም ለማስከበር የሰራተኛ ማህበሩንም ተቀላቀሉ፤ ከመምሪያ ኃላፊዎችና ከስራ አስኪያጆች ጋርም መላተም ጀመሩ።

በዚህም መሃል ማግባትና መውለድ መጣ ትንሽ እረፍት መሃል ላይ ወሰዱ። ልጅም እያሳደጉ ትግላቸውን ቀጠሉ።

በስደት ላይ የነበረው የኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ ህብረት (ኢዲዩ)ፓርቲ ሃገር ውስጥ ሲገባ፤ ባለቤታቸውም የፓርቲው አቀንቃኝ ናቸው በሚል በተደጋጋሚ ለዘብጥያ ተዳርገዋል።

ባለቤታቸው ከሞቱ በኋላ ወይዘሮ አስካለ ኢዲዩን ተቀላቀሉ። በኢዲዩም ከታች እስከ ከፍተኛ አመራር ደርሰዋል።

በተለይም በ1997 ዓ.ም በኢዲዩ ከፍተኛ አመራር የነበሩት ወ/ሮ አስካለ ዋና ፀሐፊ መሆንም ችለው ነበር።

በአመታት ውስጥ በፖለቲካ ፓርቲ ተሳትፏቸው ያዩት ነገር ቢኖር ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ቢሆኑም ሴት አባላታቶቻቸውን ከቁጥር ማሟያ ውጭ እንደማያዩዋቸው ነው።

ሆኖም በተዘረጋው ስርአት ውስጥ የራሳቸውን አስተዋፅኦ ለማርበክት መታገላቸውን ይናገራሉ።

እስከ 2001 ዓ.ም ድረስም በኢዲዩ ሲታገሉ ነበር። ከዚያ በኋላ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች መሰነጣጠቅና መበታተንም ተከተለ። ብዙ የፖለቲካ ፖርተዎች ተበታተኑ የኢትዮጵያ ፍትህና ዲሞክራሲ ሃይሎች ግንባር፣ ኢፍድሃግን መሰረቱ ስራ አስፈፃሚ ነበሩ።

ድርጅቱ ለሁለት ተሰነጠቀ፤ ፍርድ ቤትም ደረጃ ተከራክረው ነበር። ከዚያ በኋላ ለአመታት ትንሽ ገለል ብለው ወደራሳቸው ንግድ ተመልሰው በወጪ ንግድ ተሰማርተው ነበር።

በግዞት ላይ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ አገር ውስጥ ተመለሱ ሲባል ከአራት አስርት አመታት በፊት የተመሰረተው ህብረ ህዝብምና ህብረትን ከመሰረቱት ውስጥ አንዱ የሆነው ፓርቲ ሲመለስ እሱን ተቀላቀሉ።

በፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና በአገር ውስጥም የድርጅቱ ተወካይ ናቸው። በአሁኑ ወቅት አገሪቷ ባለችበት የአለመረጋጋትና የፀጥታ ሁኔታ ምርጫ ቅስቀሳም ሆነ ለመወዳደደር ፈታኝ እንደሆነ የሚናገሩት ወይዘሮ አስካለ በአሁኑ ምርጫ እንደማይወዳደሩ ይናገራሉ።

ሆኖም በሌሎች መድረኮች ትግላቸውን እንደሚቀጥሉም አፅንኦት ይሰጣሉ።

"ሰው ሲፈጠር ለሞት ነው የተዘጋጀው፤ ተልከስክሶ ከመሞት ታሪክ ሰርቶ መሞት የተሻለ ነው" እኔ ዛሬም፣ ነገም አልተኛም ወጣቶቻችን እንዲወጡ ነው የምንፈልገው፤ ያ ትውልድ ተብለን እያለፍን ነው።"ይላሉ።