ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በካርቱም ተደራራቢ ችግር ውስጥ ነን አሉ

የካርቱም ከተማ

የፎቶው ባለመብት, Abdulmonam Eassa

በሱዳን ካርቱም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በራሳቸው ገንዘብ ነዳጅ እና ዳቦ እንኳ ለመግዛት በመከልከላቸው መቸገራቸውን ለቢቢሲ ተናገሩ።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው በካርቱም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች እንዳስረዱት በአለም ዓቀፉ የስደተኞች ጉዳይ ድርጅት የስደተኛ እውቅና አግኝተው ለረዥም ዓመታት በከተማው የኖሩ ቢሆኑም የአገሪቱ ፖሊስ እንግልት እያደረሰባቸው መሆኑን ጨምረው አስረድተዋል።

እነዚህ ስደተኞች እንደሚናገሩት ከሆነ በተለይም ኢትዮጵያና ሱዳን በድንበር ይገባኛል የተነሳ ውዝግብ ውስጥ ከገቡ በኋላ ደግሞ በብዙ ፍራቻና ስጋት ውስጥ እንደሚኖሩ ይናገራሉ።

ስደተኞቹ ከኢትዮጵያ በተለያየ ምክንያት የወጡና ለአመታትም ሱዳንን መኖሪያቸው ያደረጉ ናቸው።

በአገሪቱ ፖሊስ የሚደርስባቸውን እንግልት በመጥቀስ ለጥያቄያችን መልስ አልተሰጠንም ያሉት ስደተኞቹ፣ የተባበሩት መንግሥታት የሥደተኞች ጉዳይ ኮሚሽን /ዩኤንኤችሲአር/ ግቢ ውስጥ ለሶስት ወራት ከኖሩ በኋላ በመኪና ተወስደው የካርቱም የከተማው ቆሻሻ የሚደፋበት ስፍራ ላይ እንዲቆዩ መደረጋቸውንም ይናገራሉ።

ስደተኞቹ አክለውም አሁን እንዲኖሩበት የተደረገው ይህ ስፍራ ከካርቱም ውጪ አፍሪካ ኢንተርናሽናል ዩኒቨርስቲ በስተጀርባ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በስፍራው ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ብቻ ከ700 በላይ አባወራዎች እንደሚገኙ ገልፀው የኮንጎ፣ ብሩንዲ፣ ኤርትራ እና ሌሎች አፍሪካ አገራት ስደተኞች ይገኛሉ ሲሉ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው በሱዳን ካርቱም የሚኖሩት ስደተኞች እያጋጠማቸው ባለው ችግር ሴቶችና ሕጻናት የበለጠ ተጎጂ መሆናቸውን ይናገራሉ።

እነዚህ ስደተኞች የተሟላ የስደተኛ ሰነድ ያላቸው ቢሆንም ችግር እየደረሰባቸው መሆኑንም ጨምረው አስረድተዋል።

በጎዳና ላይ በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ የአገሪቱ ፖሊስ የተለያዩ የመብት ጥሰቶች እንደሚያደርስባቸውም ይገልጻሉ።

ቢቢሲ ካነጋገራቸው ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ከልጆቻቸው ጋር እየተቸገሩ መሆኑን የገለፁት የአራት ልጆች እናት የሆኑት ኩለኒ በየነ ላለፉት 28 ዓመታት በሱዳን ካርቱም ኖረዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽን ስር ተመዝግበው የስደተኛ እውቅና ቢሰጣቸውም አሁን ግን የከፋ ችግር ውስጥ እንዳሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ወ/ሮ ኩለኒ በኢትዮጵያ እና ሱዳን መካከል የድንበር ይገባኛል ውዝግብ ከተነሳ ወዲህ የሚደርስባቸው እንግልት መጨመሩን ያስረዳሉ።

ሌላዋ ቢቢሲ ያነጋገራቸውና የሰባት ልጆች እናት የሆኑት ወ/ሮ የሺ ከበደ ደግሞ "ልጆችን ይዤ መንገድ ላይ እየተቸገርኩ ነኝ፤ ባለቤቴ ብቻ ነው እየሰራ ያለው፤ ልጆቻችንን የምናሳድግበት አጥተን እየተቸገርን ነው" ሲሉ ያሉበትን ሁኔታ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

አቶ ዮሐንስ ሳሙዔል በምስራቅ ሱዳን ከሰላ አካባቢ በሚገኘው የስደተኞች ካምፕ ለስድስት ዓመታት ከቆዩ በኋላ ካርቱም ገብቶ ሁሉንም የስደተኝነት መስፈርት በማሟላቱ ረዥም ዓመታት ቢኖሩም በአሁኑ ሰዓት ግን መብታቸው እየተገፈፈ መሆኑን ይናገራሉ።

"በምሽት ፖሊሶች መጥተው በብዙ መኪና ጭነውን ከከተማ አውጥተውን ካርቱም ከተማ ቆሻሻ የሚጣልበት ስፍራ ጥለውን ተመለሱ። . . . የምንጠለልበት የለም፤ የሚሰጠን ድጋፍም የለም፤ አሁን የግል ኮንቴይነር አግኝተን በጋራ እየኖርን ነው" ብለዋል አቶ ዮሐንስ።

ኢትዮጵያን ጨምሮ ከስድስት አገራት የመጡ ስደተኞች በዚህ ስፍራ እንደሚገኙም አቶ ዮሐንስ ጨምረው አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ አንዳንድ ዜጎች የሚደርስባቸውን ሲናገሩም "ዳቦ ለመግዛት በምንሰለፍበት ከሰልፉ ያባርሩናል፤ ነዳጅ ለእኛ አይሸጡም። የድንበር ግጭቱ ከተከሰተ በኋላ ደግሞ ከመኪና ውስጥም ያስወርዱናል" ብለዋል።

በካርቱም የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ስደተኞች ያላቸውን ስጋት እንደሚያውቅ ገልፆ፣ በኢትዮጵያ ስደተኞች ላይ በተለየ በአገሪቷ መንግሥት እውቅና የደረሰ ችግር ባይኖርም "ውስጥ ውስጡን ጉዳት እየደረሰ መሆኑን እናውቃለን" ብሏል።

ካርቱም በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የዳያስፖራዎች ጉዳይ ኃላፊ አቶ ሚካኤል ጦብያስ በከተማ የሚኖሩት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይ የሚደርሰውን ችግር ለአገሪቷ መንግሥት አሳውቀው መፍትሄ እንዲያገኝ እየሰሩ መሆኑንም ተናግረዋል።

አቶ ሚካኤል በካርቱም ከተማ ውስጥ በተለያየ ሥራ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን ችግሮች እንደሚገጥማቸው እንደሚያውቁ ለቢቢሲ አስረድተዋል።

የሱዳን ፖሊስም በእነዚህ ስደተኞች ላይ የመብት ጥሰትን እየፈፀመ እንደሚገኝ በመናገር 'በድፍረት እንዳንጠይቅ ወይንም እንዳንከራከር ብዙዎቹ ከሕግ ውጪ ወደ አገሪቷ መግባታቸውን' እንዳገዳቸው ይገልጻሉ።

የአገሪቷ የሰብዓዊ መብቶች እና የፍትህ አሰጣጥ ሂደት ደካማ ስለሆነ ፖሊስ በሰጠው ማስረጃ እና ቃል ብቻ ፍርድ ቤቱም ፍርድ ሲሰጥ እንደቆየ ጨምረው አስረድተዋል።

በዚሁ አካሄድ ብዙ ሰዎች ከአገር እንዲወጡ ተደርጓል ሲሉ አቶ ሚካኤል ተናግረዋል።

"ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥብቻ በዚህ መንገድ 220 የሚሆኑ ሰዎች ተይዘው ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ተደርጓል፤ ሌሎች ሰዎችን ደግሞ ያለፈቃድ ሰርታችኋል በማለት ፖሊስ ሲቀጣቸው ቆይቷል።"

አቶ ሚካኤል እንደሚሉት የኢትዮጵያ ስደተኞችም ሆነ ሌሎች በቁጥጥር ስር በሚውሉበት ጊዜ በእስር የሚቆዩበት ሁኔታ የጤናና ምግብ አገልግሎት ችግር እንዳለበት ይናገራሉ።

በኢትዮጵያ ኤምባሲ በኩልም በሕገወጥ ወደ አገሯ የገቡን የተወሰኑትን እያሩሌሎቹ ደግሞ እየመለሰች መሆኑን ተስተውሏል።

የኢትዮጵያ ስደተኞች ስጋት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየጨመረ የመጣው በሁለት ምክንያት መሆኑን የዲያስፖራ ጉዳይ ኃላፊው አቶ ሚካኤል ያብራራሉ።

የመጀመሪያው የአገሪቷ ምጣኔ ኃብት መዳከም ጋር ተያይዞ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ያጋጠመ ሲሆን የሚቀርበው ዳቦ እና ነዳጅ ከፍተኛ እጥረት ማጋጠሙን ገልፀዋል።

ከዚህም የተነሳ የአገሪቷ ዜጎች ስደተኞች ናቸው ስራ እየቀሙን በማለት እንደሚቃወሙ ይናገራሉ።

ሌላኛው ምክንያት ብለው የሚጠቅሱት በኢትዮጵያ እና በሱዳን ድንበር አካባቢ በተፈጠረው አለመግባባት የተነሳ ሲሆን 'ድንበር ላይ ሰዎቻችንን ትገድላላችሁ፤ እዚህ ደግሞ ዳቦችንን እየተሻማችሁ ትበላላችሁ' በማለት ጫና አያደረጉ መሆናቸውን መስማታቸውን ተናግረዋል።

በሳምንት ቢያንስ ወደ አስር የሚሆን አውቶብስ ስደተኞች በመተማ በኩል ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመለሱ አቶ ሚካኤል ጨምረው አስረድተዋል።

በዩኤን ኤችሲአር ስር ተመዝግበው ያሉ ስደተኞች ወደ ኤምባሲ ስለማይመጡ መርዳት እንደማይችሉም አሳስበዋል።

"ቢሆንም ግን ዜጎቻችን ስለሆኑ መብቶቻቸው እንዲከበሩ የአገሪቷን መንግሥት ስናሳስብ ቆይተናል" ብለዋል።

በእነዚህ ስደተኞች የቀረበውን ቅሬታ ይዘን የዩኤን ኤች ሲአር ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም።