ሰሜን ኮሪያ ሁለት የባሊስቲክ ሚሳኤሎችን ወደ ጃፓን ባሕር አስወነጨፈች

ኪም ጆንግ ኡን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ሰሜን ኮሪያ ጆ ባይደን የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ከሆኑ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ሁለት የባሊስቲክ ሚሳኤሎችን በጃፓን ባህር ላይ እንደተኮሰች አሜሪካ እና ጃፓን ገለጹ።

በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔ መሠረት ፒዮንግያንግ አስጊ መሳሪያዎች ተደርገው የሚቆተሩትን የባሊስቲክ ሚሳኤሎችን ከመሞከር ታግዳለች።

ጃፓን እና ደቡብ ኮሪያ ሙከራውን አውግዘዋል።

የአሁኑ ሙከራ ሰሜን ኮሪያ ባሊስቲከው ያልሆኑ ሁለት ሚሳኤሎችን መተኮሷ ከተዘገበ ከጥቂት ቀናት በኋላ ነው።

ጃፓን በግዛቷ ውስጥ በሚገኝ የውሃ አካል ውስጥ ምንም ስብርባሪ እንዳልተገኘ ገልጻለች።

በእስያ-ፓስፊክ አካባቢ የሚገኙ ወታደራዊ ኃይሎችን በበላይነት የሚቆጣጠረው የአሜሪካ የፓስፊክ እዝ ሙከራው "የሰሜን ኮሪያ ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ መርሃ ግብር ለጎረቤቶቿ እና ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚያደርሰውን ሥጋት" አጉልቶ ያሳያል ብሏል።

ይህን ሙከራ ተከትሎ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በጉዳዩ ላይ እስካሁን ያሉት ነገር የለም።

ባይደን ከቀናት በፊት ሰሜን ኮሪያ ያከናወነችውን ባሊስቲክ ያልሆነ ሚሳኤል የማስወንጨፍ ሙከራ አሜሪካ እንደነገር ቀስቃሽ አትቆጥረውም ብለው ነበር።

በዕለቱ ሰሜን ኮሪያ ያስወነጨፈቻቸው የአጭር ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳኤሎች፤ በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔዎች ያልታገዱ እንደሆኑ ይቆጠራል።

የሀሙስ ሙከራም የተከናወነው ማሌዥያ ሙን ቾል ሚዩንግ ተብሎ የሚጠራ የሰሜን ኮሪያ ዜግነት ያለው ነጋዴን ለአሜሪካ አሳልፈ ከሰጠች ከቀናት በኋላ ነው።

ሙን የአሜሪካን የገንዘብ ስርዓት ተጠቅሞ ገንዘብ በሕገ-ወጥ መንገድ በማዘዋወር የቅንጦት መገልገያዎችን ወደ ሰሜን ኮሪያ አስገብቷል የሚል ክስ ቀርቦበታል።

ክስተቱ ሰሜን ኮሪያን ያስቆጣ ሲሆን ከማሌዥያ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትም እንድታቋርጥ አድርጓል።

የጃፓን ባለሥልጣናት ሰሜን ኮሪያ ሁለቱን ሚሳኤሎች ሐሙስ እንዳስወነጨፈች ተናግረዋል። ከጃፓን ብቸኛ የኢኮኖሚ ቀጠና ውጭ ባሉ ውሃዎች ውስጥ ከመድረሳቸው በፊት 420 ኪ.ሜ. በላይ ተጉዘው አርፈዋል። በመርከቦች ወይም በአውሮፕላኖች ላይ የደረሰ ጉዳትም የለም።

በተያያዘ ዜና የባይደን አስተዳደር ከሰሜን ኮሪያ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማድረግ ያደረገው ሙከራ አለመሳካቱን አስታውቋል።

ፕዮንግያንግ ለባይደን ፕሬዝዳንትነት እውቅና ያልሰጠች ሲሆን ሁለቱ አገራት በሰሜን ኮሪያ የኒውክሌር እና የባሊስቲክ ሚሳኤል መርሃግብሮች ላይ አልተግባቡም።