ዋልያዎቹ በቀጣዩ የአፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ ወሳኝ 90 ደቂቃዎች ቀራቸው

የብሔራዊ ቡድኑ ደጋፊዎች

የፎቶው ባለመብት, Visionhaus

የምስሉ መግለጫ,

የብሔራዊ ቡድኑ ደጋፊዎች

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ማደጋስካርን በሰፊ የግብ ልዩነት ካሸነፈ በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ውድድር ለመግባት አንድ ቀጣይ ጨዋታ ብቻ ቀረው።

ብሔራዊ ቡድኑ በአሁኑ ጊዜ የምድቡን መሪነት የያዘ ሲሆን በቀጣይ ከኮትዲቯር ጋር የሚያደርገውን ጨዋታ ማሸነፍ ከቻለ ከዓመታት በኋላ በአፍሪካ ዋንጫ ውድድር የመሳተፍ እድል ይኖረዋል።

ዋልያዎቹ ረቡዕ መጋቢት 15/2013 ዓ.ም ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ በባሕር ዳር ላከተማ ባደረገው ጨዋታ የማደጋስካር አቻቸውን ማሸነፋቸውን ተከትሎ በቀጣዩ የአፍሪካ ዋንጫ የመሳተፍ እድላቸው ከፍ ብሏል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ትናንት ከሰዓት በባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታድየም በተካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የምድብ ጨዋታ ማዳጋስካርን 4 ለ 0 በማሸነፍ የደረጃ ሰንጠረዡን መምራት ጀምሯል።

ግቦቹን አማኑኤል ገብረሚካኤል ፣ጌታነህ ከበደ፣ አቡበከር ናስር እና ሽመልስ በቀለ አስቆጥረዋል።

በዋሊያዎቹ ምድብ ውስጥ የሚገኙት ኮትዲቯር እና ኒጀር ነገ የሚጫወቱ ሲሆን፤ የጨዋታው ውጤት እስከሚታወቅ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የደረጃ ሰንጠረዡን በ9 ነጥብ መምራቱን ይቀጥላል።

በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከኮትዲቯር፣ ማደጋስካር እና ኒጀር ጋር የተመደበችው ኢትዮጵያ፤ በመጀመሪያው ጨዋታ በማደጋስካር አንድ ለባዶ ተሸንፋ የነበረ ሲሆን በቀጣይ በባሕር ዳር በተደረገ ጨዋታ ኮትዲቯርን ሁለት ለአንድ በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችላለች።

በመቀጠል ዋልያዎቹ ወደ ኒጀር ተጉዘው፤ አንድ ለባዶ ቢሸንፉም በመልሱ ጨዋታ ሦስት ለባዶ ማሸነፍ ችለዋል።

በወዳጅነት ጨዋታ በቀላሉ ማላዊን በሰፊ የጎል ልዩነት ያሸነፉት ዋልያዎቹ ከማደጋስካር ጋር በነበራቸው የምድብ ጨዋታ ደግሞ አራት ለባዶ በማሸነፍ ነው ምድቡን በዘጠኝ ነጥብ መምራት የቻሉት።

በምድቡ ወሳኝ ጨዋታ ነገ አርብ ኮትዲቯር ከኒጀር የሚያደርጉት ሲሆን ጨዋታው በኮትዲቯር አሸናፊነት የሚጠናቀቅ ከሆነ ኢትዮጵያ በምድቡ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ዝቅ ትላለች።

ጨዋታው በኒጀር አሸናፊነት አልያም አቻ የሚጠናቀቅ ከሆነ ደግሞ ዋልያዎቹ መሪነታቸውን አስጠብቀው ወደ መጨረሻው የምድብ ጨዋታ ይጓዛሉ ማለት ነው።

ዋልያዎቹ በምድቡ የመጨረሻ ጨዋታቸውን መጋቢት 21/2013 ዓ.ም ወደ ኮትዲቯር ተጉዘው የሚያደርጉ ሲሆን ማደጋስካር ከኒጀር የሚያደርጉትም ጨዋታ በጉጉት የሚጠበቅ ነው።

ኢትዮጵያ ኮትዲቯርን የምታሸንፍ ከሆነ በካሜሩን አዘጋጅነት በሚካሄደው ጨዋታ ተሳታፊነቷን የምታረጋግጥ ሲሆን፤ ማደጋስካር ከኒጀር የሚያደርጉት ጨዋታ በኒጀር አሸናፊነት የሚጠናቀቅ ከሆነ ደግሞ ሰፊ የማለፍ እድል ይኖራታል።

በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በአንድ ዓመት በተራዘመው 33ኛው የአፍሪካ እግር ኳስ ዋንጫ ከወዲሁ አምስት አገራት ማለፋቸውን አረጋግጠዋል።

እነዚህም አገራት አዘጋጇ ካሜሩን፣ ሴኔጋል፣ ቱኒዚያ፣ ማሊ እና አልጄሪያ ናቸው።