ማኅበራዊ ሚዲያ፡ የቲክቶክ እና የኢንስታግራም ተጠቃሚዎች እየገጠማቸው ያለ ጫና

ሰውነትን 'ስለ መለወጥ' የሚያስተዋውቁት መተግበሪያዎች ያሳደሩት ጫና

ቲክቶክ እና ኢንስታግራም ላይ የሰውነት አካልን እንዴት መለወጥ እንደሚቻል የሚያስተዋውቁ መተግበሪያዎች ይቀርባሉ።

የማኅበራዊ ሚዲያዎቹ ተጠቃሚዎች የሆኑና የአመጋገብ ሥርዓት መዛባት ያለባቸው ሰዎች በእነዚህ ማስታወቂያዎች ጫና ሥር እንደወደቁ የመብት ተሟጋቾች እገለጹ ነው።

ወገብን እንዴት ማቅጠን እንደሚቻል፣ በምን መንገድ ጡንቻ ማውጣት እንደሚቻልና ሌላም ሰውነት ላይ ስለሚደረግ ለውጥ መተግበሪያዎቹ ይገልጻሉ።

እነዚህን መተግበሪያዎች [አፕ] የሚያስተዋውቁ ገጾች ደግሞ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ተስፋፍተዋል።

እነዚህ መተግበሪያዎች አፕል እና አንድሮይድ ላይም አሉ። ተጠቃሚዎች በፎቶ ወይም በቪድዮ የሚታይ ሰውነታቸው ላይ የፈለጉትን አይነት ለውጥ እንዲያደርጉ እንደሚችሉ የሚገልጹ ናቸው።

ይህም ቆዳን ማለስለስ፣ የሰውነት ክብደት መቀነስ፣ ጡንቻ ማሳደግን ያካትታል።

የአመጋገብ ሥርዓት መዛባትን በተመለከተ ንቅናቄ የሚያደርጉ ድርጅቶች፤ ማኅበራዊ ሚዲያዎቹ እየተፈጠረ ያለውን ጫና ከግምት እንዲያስገቡ ጠይቀዋል።

የቴክኖሎጂ ተቋሞቹ እንደሚሉት፤ እነዚህ መተግበሪያዎች የማኅበራዊ ሚዲያዎቹን የማስታወቂያ ደንብ አልጣሱም።

ነገር ግን ቲክቶክ በበኩሉ የማስታወቂያ ፖሊሲውን ለመከለስ ፍቃደኛ ሆኗል።

"ሰዎች ስለ ሰውነታቸው በጎ አመለካከት እንዲኖራቸው ከማበረታታት ወደ ኋላ አንልም" ብሏል ቲክቶክ።

ምግብ ስለመቀነስ እና ክብደትን ለመቆጣጠር ስለሚወሰዱ ተጨማሪ ንጥረ ነገሮች የሚያስተዋውቁ ጽሑፎችን ባለፈው ዓመት ማገዱ ይታወሳል።

"ጤናማ ያልሆነና የተዛባ መልዕክት ማስተላለፍ አይገባም"

የአመጋግብ ሥርዓት መዛባት ተሟጋቿ ሆፕ ቪርጎ "ጤናማ ያልሆነና የተዛባ መልዕክት ማስተላለፍ አይገባም" ትላለች።

ማኅበራዊ ሚዲያዎች ተጠያቂ መደረግ እንዳለባቸው ትናገራለች።

ባለፈው ዓመት የአመጋገብ ሥርዓት መዛባት ያለባቸው ሰዎች ቁጥር መጨመሩን ትናገራለች።

የአመጋግብ ሥርዓት መዛባት ከሚከሰትባቸው ምክንያቶች አንዱ ለሰውነት ቀና አመለካከት ማጣት ነው።

ቲክቶክ እና ኢንስታግራም ላይ ሰውነትን ስለመለወጥ የሚያሳዩ መተግበሪያዎች መተዋወቃቸው ደግሞ ችግሩን እንዳያባብሰው ተሰግቷል።

ሲድ የተባለው የአመጋግብ ሥርዓት መዛባት ላይ የሚሠራው ድርጅት ባወጣው አሀዝ መሠረት፤ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተ ወዲህ ይህ መዛባት የገጠማቸው ከ10 እስከ 19 ዓመት የሆኑ ታዳጊዎች እና ወጣቶች ቁጥር በ68 በመቶ ጨምሯል።

የጤና ጉዳዮች ጋዜጠኛ ሆነችው ዴኒ ሜሲር ከዚህ ቀደም የአመጋገብ ሥርዓት መዛባት ገጥሟት ነበር።

ኢንስታግራም እና ቲክቶክ ላይ ሰውነትን በመልካም መንገድ ማየትን የሚያበረታቱ መልዕክቶች ታጋራለች።

"እነዚህ መተግበሪያዎች ችግሩን እንደሚያባብሱ በራሴ አይቼዋለሁ። ከተፈጥሯዊ ሰውነቴ የቀጠነ ምስል ያሳያሉ። የሚያሳዩት ነገር በተፈጥሮ ሊፈጠር የማይችል ነው" ትላለች።

መተግበሪያዎቹ ያሳደሩት ጫና ከፍተኛ እንደሆነ ገልጻ "ተጽዕኖውን ገና ለዓመታት እናየዋለን" በማለት ተናግራለች።

በቀላሉ ተጽዕኖ ሥር ሊወድቁ የሚችሉ ታዳጊዎች በዋነኛነት ተጎጂ እንደሆኑም አያይዛ አስረድታለች።

"ታዳጊዎች ነገሩን ለማገናዘብ እድሜያቸው ገና ነው። የሰውነት ክብደትን ለመቀነስ ስለሚወሰዱ ንጥረ ነገሮች ለሕፃናት ማስታወቂያ እንደማይሠራው ሁሉ እነዚህ መተግበሪያዎችም መታገድ አለባቸው" ስትልም አስተያቷን ሰጥታለች።

ኃላፊነት መውሰድ

የሲድ ኃላፊ ጀማ ኦተን በወረርሽኙ ወቅት ብዙዎች ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚያሳልፉት ጊዜ መጨመሩን ትናገራለች።

ሰዎች ትክክለኛ ገጽታቸውን ለውጠው ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ መቅረብ የሚችሉበት መተግበሪያ መፈጠሩ በጊዜ ሂደት ሥነ ልቦናዊ ቀውስ እንደሚያስከትልም ታስረዳለች።

በተለይም ዓለም ወደ መደበኛው ሕይወት ሲመለስ እንደ አሁኑ ከስክሪን ጀርባ መደበቅ ስለማይቻል ነገሮች ይባባሳሉ።

ማኅበራዊ ሚዲያዎች ሰውነት ላይ ስለሚደረግ ለውጥ የሚያስተዋውቁ መተግበሪያዎችን በማገድ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም ታሳስባለች።

ቢት የተባለው የአመጋገብ ሥርዓት መዛባት ላይ የሚሠራው ተቋም የውጭ ጉዳዮች ዳይሬክተር ቶም ክዊን "መተግበሪያዎቹን የሚሠሩ ሰዎች ምን ያህል ጎጂ ነገር እያመረቱ እንደሆነ እንዲያውቁት እንፈልጋለን" ይላል።