የሞዛምቢክ እስላማዊ ታጣቂዎች ‹ሆቴል ለቀው በሚሸሹ ሠራተኞች› ላይ ጥቃት አደረሱ

የሞዛምቢክ እስላማዊ ታጣቂዎች
የምስሉ መግለጫ,

የሞዛምቢክ እስላማዊ ታጣቂዎች

በሰሜናዊ ሞዛምቢክ የተቀሰቀሰውን ግጭት ተከትሎ በአንድ ሆቴል ውስጥ የነበሩት ሰዎችን ለመታደግ የሞከሩ ሰዎች አድብተው ሲጠብቁ በነበሩ እስላማዊ ታጣቂዎች ጥቃት እንድተፈጸመባቸው ተገለጸ።

በጥቃቱ አንድ የደቡብ አፍሪካዊ ግለሰብ መሞት ቢረጋገጥም ብዙ ዝርዝር ጉዳዮች እስካሁን ግልፅ አልሆኑም።

ከረቡዕ ዕለት ጀምሮ የሞዛምቢክ እስላማዊ ታጣቂዎች ፓልማ የተሰኘች ከተማን ለመቆጣጠር ከመንግሥት ኃይሎች ጋር ሲዋጉ ቆይተዋል።

በፓልማ ከተማ የጀመረውን ውጊያ በመሸሽ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከተማዋን ለቀው ተሰደዋል። ከአካባቢው እንዲወጡ ከተደረጉት መካከል የጋዝ አውጭ ሠራተኞችን ይገኙበታል።

ግዙፉ የፈረንሳይ ነዳጅ አቅራቢ ኩባንያ ቶታል በአቅራቢያው ያለውን ከፍተኛ የጋዝ ፕሮጀክት ለማቆም መገደዱን አስታውቋል።

ኩባንያው በጥር ወር በደህንነት ስጋት ምክንያት ያቆመውን የ20 ቢሊዮን ዶላር ፕሮጀክት እንደገና እንደሚጀምር በቅርቡ ነበር ያስታወቀው።

ሂውማን ራይትስ ዎች የዓይን እማኞችን ጠቅሶ "በጎዳናዎች ላይ አስከሬን ማየታቸውንና ... ተዋጊዎቹ በሰዎች እና በህንፃዎች ላይ ያለ አንዳች ልዩነት ከተኮሱ በኋላ ነዋሪዎች እንደሸሹ" አስታውቋል።

ሰሜን ሞዛምቢክ ከጎርጎሮሳዊያኑ 2017 ጀምሮ በአመፅ ስትናጥ ቆይታለች።

ከኢስላሚክ ስቴት(አይ ኤስ) ጋር ግንኙነት ያላቸው ታጣቂዎች ሙስሊሞች በብዛት በሚኖሩበት የካቦ ዴልጋዶ አካባቢ ግጭት ምክንያት ናቸው። በውጊያው ከ2500 በላይ ሰዎች ሲሞቱ 700 ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ ተፈናቅለዋል።

አማጽያኑ በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ በፓልማ ከተማ በሚገኙ ሱቆች፣ ባንኮችን እና ወታደራዊ ሰፈሮች ላይ ድንገተኛ ጥቃት ሰንዝረው ነበር።

በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ውጊያውን ሸሽተው ወደ ጫካዎች ወይም በአቅራቢያ ወዳሉ መንደሮች ሸሽተዋል። 180 የሚደርሱ የውጭ እና የሀገር ውስጥ ጋዝ ሠራተኞች በአማሩላ ፓልማ ሆቴል ተጠልለዋል።

አንዳንዶቹ አርብ ዕለት በአቅራቢያው ወደሚገኘው የባህር ዳርቻ ለመድረስ በማሰብ በተሸከርካሪ ከሆቴሉ ለማምለጥ ሞክረዋል ሲል ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

ቢያንስ 20 ሰዎች በሄሊኮፕተሮች ደህንነቱ ወደ ተጠበቀ ቦታ ተወስደዋል ተብሏል።

አንድ ምንጭ ለቢቢሲ እንደገለጹት በርካታ ሰዎች በተሳካ ሁኔታ ከፓልማ በስተደቡብ አቅጣጫ 420 ኪ.ሜ. ርቃ ወደምትገኘው ፔምባ ከተማ በሠላም ደርሰዋል።