የትምህርት ዘርፉን ለማዘመን ኢትዮጵያ ከብሎክቼይን አቅራቢ ድርጅት ጋር መስማማቷ ተገለጸ

በመዋዕለህጻናት የምትማር ተማሪ

የፎቶው ባለመብት, ullstein bild

አይኦኤችኬ (IOHK) የተባለው የብሎክቼይን ድርጅት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በጋራ ለመሥራት መስማማቱን ገለጸ።

ብሎክቼይን ላይ ምርምር በማድረግና በማበልጸግ የሚታወቀው ድርጅቱ አገልግሎት የሚሰጠው በኢትዮጵያ የትምህርት ዘርፍ ነው።

የትምህርት ሚንስትሩ ዶ/ር ጌታሁን መኩሪያ፤ ብሎክቼይን በመጠቀም የትምህርት ሥርዓቱ ዲጂታል እንደሚደረግ መናገራቸው ተዘግቧል።

በትምህርቱ ዘርፍ በዲጂታል መንገድ አካታችነት እንዲኖር፣ የከፍተኛ ትምህርትና የሥራ እድል እንዲሰፋ እንደሚያግዝም አክለዋል።

ብሎክቼይን የዳታቤዝ (የመረጃ ክምችት) አይነት ሲሆን፤ ዳታ (መረጃ) የሚያከማቸው በብሎክ ነው። እነዚህ ብሎኮች እርስ በእርስ የሚተሳሰሩ ናቸው። እንደ ቢትኮይን ያሉ ዲጂታል ገንዘቦች በዋነኛነት የሚሠሩት በብሎክቼይን ሲሆን፤ የዲጂታል ገንዘቡ ክምችት እና ዝውውር ባልተማከለ መንገድ የሚቀመጥበት ነው።

ድርጅቱ እንደሚለው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ብሎክቼይን በመጠቀም አገር አቀፍ የተማሪዎችና መምህራን መለያ ሥርዓት ይዘረጋል።

ይህም በዲጂታል መንገድ የተማሪዎችን ውጤት ለማጣራት፣ የትምህርት ቤቶችን ውጤታማነት ለመቆጣጠር እና በአገር አቀፍ ደረጃ የትምህርት ጥራትን ለማሳደግ ያለመ ነው ተብሏል።

ትምህርት ነክ መረጃ በብሎክቼይን መከማቸቱ ከከተማ ርቀው ለሚኖሩ ዜጎች የዩኒቨርስቲና የሥራ እድል ተደራሽነት እንደሚፈጥር አይኦኤችኬ የሰጠው መግለጫ ይጠቁማል።

ቴክኖሎጂው በ3,500 ትምህርት ቤቶች፣ አምስት ሚሊዮን ተማሪዎችንና 750,000 መምህራንን እንደሚደርስ ተገልጿል።

በእነዚህ ትምህርት ቤቶችም የትምህርት እንቅስቃሴን መረጃ ለመመዝገብ ያስችላል። ከደረጃ በታች ውጤት ሲመዘገብ ምክንያቱን ለመፈተሽ እንዲሁም የትምህርት መርጃ መሣሪያን በአግባቡ ለማከፋፈል ይውላል።

ሁሉም ተማሪዎች ትክክለኛነቱ የተረጋገጠ ዲጂታል መለያ እንዲኖራቸው በማድረግ ሐሰተኛ የዩኒቨርስቲ መግቢያ እና የቅጥር ሰነዶችን ቁጥር ለመቀነስ መታሰቡ ተነግሯል።

ቀጣሪዎች፤ ለሥራ ቅጥር በማመልከቻነት የገቡ የትምህርት ሰነዶችን ያለ ሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት ትክክለኛነታቸውን ማረጋገጥ ይችላሉ።

ፕሮጀክቱ ምንድን ነው?

መንግሥት ለሁሉም ተማሪዎችና መምህራን ታብሌት በመስጠት፤ የትምህርት ውጤት እንዲመለከቱ የማስቻል እቅድ እንዳለው ተነግሯል።

በገጠር ለሚኖሩ 80% ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ትምህርት የማግኘትና የሥራ ቅጥርን እንደሚያመቻች የብሎክቼይን ድርጅቱ መግለጫ ያትታል።

በብሎክቼይን አማካይነት ተማሪዎች ክፍል መግባታቸውን፣ ውጤታቸውንና ሌሎችም ትምህርት ነክ ክንውኖችን መከታተል ይቻላል። ሥርዓቱ ከመዋለ ሕፃናት አንስቶ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ድረስ ጥቅም ላይ ይውላል።

መምህራን ክፍለ ጊዜ ለመመደብ፣ ስለ ተማሪዎች ባህሪ መረጃ ለመመዝገብ እና ለሌላም ግልጋሎት ያውሉታል።

በቀጣይ ፕሮጀክቱ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተስፋፍቶ፤ የዲግሪን ትክክለኛነት በዲጂታል መንገድ መፈተሽ እንዲሁም ለሥራ ቅጥር የሚገባን የትምህርት ማስረጃ እውነተኛነት መመርመር ይቻላል።

ብሎክቼይንን መሠረት ያደረገ አገር አቀፍ መለያ በማቅረብ ረገድ የድርጅቱ አታላ ፕሪዝም ብሎክቼይን አይዲ ሥርዓት (Atala PRISM blockchain ID) አወንታዊ ተጽዕኖ እንደሚኖረው ተገልጿል።

መረጃ የሚከማችበት ብሎክቼይን ካርዴኖ (Cardano) የሚባለው ነው።

ኢትዮጵያ ከትምህርት ዘርፍ በተጨማሪ ግብርና፣ ትራንስፖርት፣ ጤና እና ሌሎች ዘርፎችንም ወደ ዲጂታል ሥርዓት ለመለወጥ መጀመሯን ተከትሎ ከአይኦኤችኬ ጋር በጥምረት መሥራት መጀመሯን ድርጅቱ አስምሮበታል።

አይኦኤችኬ ማነው?

ድርጅቱ የተመሠረተው በብሎክቼይን በሚታወቁት ቻርልስ ሆስኪንሰን እና ጀርሚ ውድ ነው። ለመንግሥታት፣ ድርጅቶች፣ የትምህርት ተቋሞችና ግለሰቦች ብሎክቼን በማበልጸግ ይታወቃል።

እአአ በ2015 የተቋቋው አይኦኤችኬ፤ አገልግሎቱን በምሥራቅ አውሮፓ፣ አሜሪካ እና በአፍሪካ ይሰጣል።