ኢትዮጵያ ቴሌኮም፡ ጨረታ ያሸነፈው የቴሌኮም ተቋም ለኢትዮጵያ ምን ይዞ ይመጣል?

5ጂ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ኢትዮጵያ በቴሌኮም ዘርፍ እንዲሳተፍ ፈቃድ የሰጠችው ተቋም ከፍተኛ መጠን ያለው መዋዕለ ነዋይ ወደ አገሪቱ እንደሚያስገባና በርካታ የሥራ ዕድሎችን እንደሚፈጥር ተነገረ።

የቴሌኮም ዘርፉን ለውጪ ተቋማት ለመጀመሪያ ጊዜ ክፍት ያደረገችው ኢትዮጵያ የበርካታ ተቋማት ስብስብ ለሆነው ኩባንያ የቴሌኮም አገልግሎት ፈቃድ መስጠቷን አስታውቃለች።

በዚህም መሠረት ግሎባል ፓርትነርሽፕ ፎር ኢትዮጵያ የተባለውና የስድስት ኩባንያዎች ጥምረት የሆነው ተቋም አገሪቱ ለጨረታ አቅርባቸው ከነበሩት ሁለት የቴሌኮም ፈቃዶች ውስጥ አንዱን በማሸነፍ በዘርፉ እንዲሰማራ መመረጡን የገንዘብ ሚኒስቴርና የኮምዩኒኬሽን ባለሥልጣን ይፋ አድርገዋል።

የኬንያው ሳፋሪኮም፣ የዩናይትድ ኪንግደም ቮዳፎን እና ሲዲሲ ግሩፕ፣ የደቡብ አፍሪካ ቮዳኮም፣ የጃፓኑ ሱሚቶሞ እንዲሁም ዲኤፍሲ ናቸው በአገሪቱ በኢትዮ ቴሌኮም ከ120 ዓመታት በላይ በብቸኝነት ተይዞ ወደነበረው ዘርፍ ለመግባት ፈቃድ ያገኙት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በበኩላቸው የተሰጠውን ፈቃድ "ታሪካዊ ውሳኔ" ብለውታል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተመረጠው ተቋም ከፍተኛ የፈቃድ ክፍያ ዋጋ እና አስተማማኝ የመዋዕለ ነዋይ ፍሰት ዕቅድ እንዳቀረበ ጠቅሰው ይህም "እስከ ዛሬ በኢትዮጵያ ከተደረጉት የውጪ ቀጥተኛ የዋዕለ ነዋይ ፍሰቶች ብልጫ እንዳለው" በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።

ተሳታፊዎቹ እነማን ነበሩ?

ኢትዮጵያ ከሁለት ዓመት በፊት የቴሌኮም ዘርፉን ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት እንደምታደርግ ካሳወቀች በኋላ ሁለት ፈቃዶችን ለዘርፉ ተሳታፊዎች በጨረታ አቅርባ ነበር።

ኅዳር 18/2013 ዓ.ም የኢትዮጵያ ኮምዩኒኬሽን ባለሥልጣን በአገሪቱ የቴሌኮም ዘርፍ ውስጥ ለመሰማራት ፍላጎቱ ላላቸው ኩባንያዎች ይፋዊ የጨረታ ጥሪ አቅርቦ ሚያዝያ 16/2013 ዓ.ም ሁለት ተቋማት በጨረታው ተሳታፊ መሆናቸውን ማሳወቁ ይታወሳል።

በዚህም መሠረት የተለያዩ ኩባንያዎች ጥምረት የሆነው ግሎባል ፓርትነርሽፕ ፎር ኢትዮጵያ የተባለው ተቋም ከፍተኛውን 850 ሚሊዮን ዶላር በማቅረብ በጨረታው ተመራጭ ሲሆን ሁለተኛው ፈቃድ ሳይሰጥ ቀርቷል።

ጨረታው ከወጣ በኋላ በርካታ የቴሌኮም ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የቴሌኮም ዘርፍ ውስጥ ለመሳተፍ ፍለጎት እንዳላቸው የገለጹ ቢሆንም የፈረንሳዩን ኦሬንጅ እንዲሁም የዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ ኢቲሳላትን ጨምሮ ሌሎችም በጨረታው ላይ ሳይሳተፉ መቅረታቸውን ኤኤፍፒ ዘግቧል።

ሁለተኛ ተጫራች የነበሩት የደቡብ አፍሪካው ኤምቲኤን እና አጋሩ የቻይና መንግሥት ኢንቨስትመንት አካል የሆነው ሲልክ ሮድ ፈንድ 600 ሚሊዮን ዶላር ለጨረታው ያቀረበ ቢሆንም ሳይመረጥ ቀርቷል።

በዚህም ሳቢያ ሁለተኛው የቴሌኮም ዘርፍ አዲስ ፈቃድ ሳይሰጥ ቢቀርም በቀጣይ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ተደርጎ ለጨረታ እንደሚቀርብ የገንዘብ ሚኒስትሩ አማካሪ ዶ/ር ብሩክ ለብሉምበርግ ገልጸዋል።

ምን ይዘው ይመጣሉ?

በአፍሪካ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ ካላቸው ቀዳሚ አገራት መካከል የምትመደበው ኢትዮጵያ፤ የቴሌኮም ዘርፍ በአንድ አገልግሎት ሰጪ ያለተፎካካሪ በብቸኝነት ተይዞ በመቆየቱ ተጠቃሚዎች በዋጋም ሆነ በአገልግሎት ጥራት አማራጭ ሳይኖራቸው ቆይቷል።

እነዚህም አዳዲስ ቴክሎኖሎጂዎች፣ ከፍተኛ መጠን ያለው መዋዕለ ነዋይ፣ በርካታ የሥራ ዕድሎች እንዲሁም የተለያዩ የቴሌኮም መሰረተ ልማቶች ግንባታዎች ናቸው።

የምጣኔ ሀብት ባለሙያውና ፌርፋክስ አፍሪካ ግሎባል ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ የቴሌኮም ዘርፉ ለውድድር ክፍት መሆኑ ጥራት ያለው አገልግሎት በርካሽ ዋጋን ከማስገኘቱ ባሻገር "ለሥራ ፈጠራና ለውድድር በር ይከፍታል" ይላሉ።

የጨረታው ውጤት ይፋ በተደረገበት መግለጫ ላይ የአገሪቱ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ እንዳሉት ውሳኔው አገሪቱ በምታካሂደው የምጣኔ ሀብታዊ ለውጥ ሂደት ውስጥ ወሳኝ እርምጃ መሆኑን ጠቅሰው "ይህም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ጥራት ያው አገልግሎት በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ ያስችላል" ብለዋል።

በዘርፉ የረጅም ጊዜ ልምድ ያላቸው የተለያዩ ታዋቂ የቴሌኮም ኩባንያዎች ስብስብ የሆነው ግሎባል ፓርትነርሽፕ ፎር ኢትዮጵያ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ውስጥ ከ750 በላይ ተጠቃሚዎች እንዳሉት ይነገራል።

የኩባንያዎቹ ዘርፈ ብዙ ልምድ በኢትዮጵያ የቴሌኮም ዘርፍ ውስጥ ጉልህ ለውጥ ለማምጣት እንደሚያስችላቸው የሚጠበቅ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ቴሌኮምዩኒኬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ኢንጂኒየር ባልቻ ሬባ እንዳሉት "የተሰጠው ፈቃድ ሚሊዮኖች ጥራት ያው አስተማማኝ አገልግሎትን እንዲያገኙ በማስቻል በአገሪቱ የቴሌኮም ዘርፍ አዲስ ምዕራፍ ይከፍታል" ብለዋል።

በኢትዮጵያ እንዲሰራ ፈቃድ ያገኘው አዲሱ የቴሌኮም ተቋም ከ110 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ባላት አገር ውስጥ ሰፊ የገበያ ዕድል ያለው ሲሆን ዘመኑ ያፈራቸውን የቴሌኮም ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የተለያዩ አገልግሎቶችን እንደሚያቀርብ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ገንዘብ ሚኒስትር አማካሪ ዶ/ር ብሩክ ታዬ ለኤኤፍፒ እንደተናገሩት በጨረታው የተመረጠው ተቋም የ4ጂ እና የ5ጂ የኢንተርኔት አገልግሎቶችን ያቀርባል። በተጨማሪም ሳተላይት በመጠቀም ከሁለት ዓመት በኋላ መላው አገሪቱ የ4ጂ የኢንተርኔት ሽፋን እንዲያገኝ ያደርጋል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ የቴሌኮም አገልግሎት ለመስጠት የመጀመሪያውን ፈቃድ ያገኘው የውጭ ተቋም በርካታ ጥቅሞችን ለአገሪቱና ለሕዝቧ ያስገኛል ተብሎ ይጠበቃል።

በተለይ በየጊዜው እያደገ ከመጣው የሥራ ፈላጊ ወጣት ቁጥር አንጻር አስተዋጽኦ እንደሚኖረው የተነገረ ሲሆን ከፍተኛ መጠን ያለው የሥራ ዕድልን ይፈጥራል ተብሏል።

የፎቶው ባለመብት, Thinkstock

ዶ/ር ብሩክ እንዳሉት ተቋሙ በሚቀጥሉት አስር ዓመታት ውስጥ እስከ 1.5 ሚሊዮን የሚደርሱ አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን የሚፈጥር ሲሆን 8.5 ቢሊየን ዶላር የሚደርስ መዋዕለ ነዋይን ወደ አገሪቱ ያስገባል።

በውጭ ኩባንያዎች ከሚያዙት ሁለቱ የቴሌኮም ፈቃዶች በተጨማሪ ዋነኛው የአገሪቱ አገልግሎት ሰጪ ኢትዮ ቴሌኮምም በሩን ለባለሃብቶች ይከፍታል።

በዚህም በመንግሥት ብቸኛ ባለቤትነት ሥር የቇየው ተቋሙ በቅርቡ 40 በመቶን ድርሻ ለውጪ ባለሃብቶች፣ 5 በመቶን ለኢትዮጵያውያን እና 55 በመቶውን መንግሥት እንደሚይዘው ይጠበቃል።

የኢትዮጵያን የቴሌኮም ገበያ በብቸኝነት እያገለገለ ያለው መንግሥታዊው ኢትዮ ቴሌኮም ሲሆን፤ በአህጉሪቱ በሕዝብ ብዛት ሁለተኛ የሆነችው አገር የቴሌኮም ዘርፍ ለውጭ ኩባንያዎች አጓጊ ገበያ እንደሆነ ሲነገር ቆይቷል።

በዚህም ኢትዮጵያ በቴሌኮም ዘርፍ ለሚሳተፉ ኩባንያዎች ሁለት ፈቃዶችን ከማዘጋጀቷ በተጨማሪ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር የሚገኘውን የኢትዮቴሌኮም የተወሰነ ድርሻ ለመሸጥም እቅዷን አሳውቃለች።

በኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ የቴሌኮም አገልግሎትን በብቸኝነት እየሰጠ የሚገኘው ኢትዮቴሌኮም በአፍሪካ ከፍተኛ ቁጥር የሞባይል ስልክ አገልግሎት ተጠቃሚ ካላቸው ተቋማት መካከል አንዱ ነው።

ኢትዮጵያ የቴሌኮም ዘርፉን ለውጭ ተቋማት ክፍት እንደምታደርግ ያስታወቀችው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በተወሰዱ የለውጥ እርምጃዎች ነው።

በአፍሪካ በርካታ ሕዝብ ይዛ አንድ የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢ ድርጅት ያላት አገር ኢትዮጵያ አሁን ለዘርፉ በሯን ከፍታለች። በዚህም መሠረት የተለያዩ ኩባንያውያዎች ጥምረት የሆነው ተቋም ቀዳሚው የውጭ አገልግሎት ሰጪ ለመሆን ተመርጦ ፈቃድ ተሰጥቶታል።

ለመሆኑ የስድስት ኩባንያዎች የጋራ ጥምረት የሆነው ግሎባል ፓርትነርሽፕ ፎር ኢትዮጵያ የተባለው ተቋም በውስጡ የያዛቸው ኩባንያዎች እነ ማን ናቸው? በዘርፉ ያላቸውስ ልምድ?

ሳፋሪኮም

ዋና መሥሪያ ቤቱ ናይሮቢ የሚገኘው ሳፋሪኮም የኬንያ የቴሌኮም ድርጅት ሲሆን፤ ኬንያ ውስጥ ትልቁ የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢና በምሥራቅ እና በመካከለኛው አፍሪካ ትርፋማ ከሆኑ ድርጅቶች አንዱ ነው።

ሳፋሪኮም የተንቀሳቃሽ ስልክ መስመር፣ የኢንተርኔት፣ የስልክ ግብይት እንዲሁም ሌሎችም አገልግሎቶች ይሰጣል።

እአአ በ1997 ገደማ የተቋቋመው ሳፋሪኮም፤ በተለይም ኤምፔሳ በተባለው የሞባይል ገንዘብ ማዘዋወሪያ አገልግሎቱ በስፋት ይታወቃል።

ሳፋሪኮም በሌሎች አገራት ከሚሠሩ የቴሌኮም ድርጅቶች ጋር በመጣመር አገልግሎቱን እያስፋፋ ነው። ከእነዚህ መካከል ታንዛንያ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ሕንድ ይጠቀሳሉ።

የሳፋሪኮም ድረ ገጽ እንደሚያሳየው፤ ከኬንያ የቴሌኮም ገበያ 64.5 በመቶ ድርሻን ይወስዳል። ወደ 35.6 ሚሊዮን የሚጠጉ ተጠቃሚዎችም አሉት።

የዩናይትድ ኪንግደሙ ቮዳፎን ኩባንያ ከሳፋሪኮም 40 በመቶ ድርሻን ገዝቷል።

ቮዳኮም

በአፍሪካ ውስጥ ሰፊ የቴሌኮም አገልግሎት ከሚሰጡት ኩባንያዎች መካከል ቮዳኮም ይጠቀሳል። የኢንተርኔት፣ የተንቀሳቃሽ ስልክ ጥሪ እንዲሁም ከገንዘብ ዝውውወር ጋር የተያያዙ ዘርፎችም አሉት።

መነሻውን ደቡብ አፍሪካ ያደረገው ቮዳኮም፤ በታንዛንያ፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ሞዛምቢክ፣ ሌሶቶ እና ኬንያ ውስጥ አገልግሎት ይሰጣል።

የሞባይል ኔትወርክ ዝርጋታው ከ296 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ እንዳደረገ የድርጅቱ ድረ ገጽ ይጠቁማል።

ቮዳኮም ቢዝነስ አፍሪካ በሚል በ29 አገራት ንግድ ነክ አገልግሎቶች ይሰጣል። ከቮዳኮም 60.5 በመቶ የሚሆነው የባለቤትነት ድርሻ የብሪታኒያው ቮዳፎን ነው።

የ3ጂ እና 4ጂ የሞባይል ኢንተርኔት አገልግሎት የሚሰጠው ቮዳኮም፤ በአፍሪካ በግንባር ቀደምነት የቀጥታ 5ጂ ኔትወርክ እንደዘረጋ ይነገርለታል።

ቮዳፎን

የብሪታኒያው ቮዳፎን አገልግሎት የሚሰጠው በአውሮፓ፣ በእስያ እና በአፍሪካ ሲሆን፤ በ21 አገራት ውስጥ ኔትወርክ ዘርግቷል።

አውሮፓ ውስጥ በኔትወርክ ዝርጋታ የአንበሳውን ድርሻ እንደያዘ የሚነገርለት ቮዳፎን፤ አፍሪካ ውስጥ ከ42 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የሞባይል ገንዘብ መለዋወጫ አገልግሎትን እንዲጠቀሙ እንዳስቻለ በድረ ገጹ የሰፈረው መረጃ ይጠቁማል።

ቮዳፎን የተንቀሳቃሽ ስልክ ጥሪ፣ ኢንተርኔትና ሌሎችም ተያያዥ አገልግሎቶች ይሰጣል።

በኢንተርኔት አማካይነት የተለያዩ ኤሌክትሮኒክስ ነክ መገልገያዎችን በማስተሳሰር የሚታወቀውና 'ኢንተርኔት ኦፍ ቲንግስ' የሚባለውን አገልግሎት በተለይም ለንግድ ተቋማት ያቀርባል።

እንደ አውሮፓውያኑ ከ1980ዎቹ ወዲህ የተስፋፋው ቮዳፎን የስልክ ጥሪ፣ የጽሁፍ መልዕክትና ኢንተርኔት የሚያቀርብ ሲሆን፤ አውሮፓ ውስጥ የ5ጂ ዝርጋታ ላይ በስፋት ይሠራል።

በአፍሪካ በጋና፣ በሊቢያና በካሜሩን፤ በመካከለኛው ምሥራቅ ደግሞ በኳታር፣ በባህሬንና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፤ በእስያ ደግሞ በጃፓን እና በሕንድ አገልግሎት ይሰጣል።

ኤምቲኤን ግሩፕ

ኤምቲኤን ግሩፕ መቀመጫውን ደቡብ አፍሪካ ያደረገ የቴሌኮም ተቋም ነው። በተለያዩ የአፍሪካ፣ የአውሮፓ እንዲሁም የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት አገልግሎት ይሰጣል።

ዋና መሥሪያ ቤቱን ደቡብ አፍሪካ ጆሀንስበርግ ያደረገው ተቋም ወደ 273 ሚሊዮን የሚጠጉ ተገልጋዮች እንዳሉት በድረ ገጹ ያሰፈረው መግለጫ ይጠቁማል።

በ20 አገሮች የሚሠራው ኤምቲኤን ግሩፕ ከፍተኛውን ገቢ የሚያገኘው ከናይጄሪያ ነው። እንደ አውሮፓውያኑ በ1994 ገደማ ከደቡብ አፍሪካ መንግሥት በተገኘ ድጋፍ ነበር የተቋቋመው።

ሱሙቲሞ ኮርፖሬሽን

ሱሙቲሞ ኮርፖሬሽን የጃፓን ተቋም ሲሆን ቴሌኮምን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች የተሰማራ ነው።

በብረት ምርት፣ በትራንስፖርትና ምህንድስና፣ በማዕድን፣ በሪልስቴት እና ሌሎችም ዘርፎች ለረዥም ዓመታት ሠርቷል።

ከእነዚህ በተጨማሪ በመገናኛ ብዙሃን እና በቴሌኮምዩኒኬሽን ዘርፍ የሚሰጠው አገልግሎት የኬብል ቴሌቭዥን እና 5ጂ የሞባይል ኢንተርኔትን ያካትታል።

ቲ-ጋያ የሚባል የሞባይል አከፋፋይ ያለው ሱሙቲሞ ኮርፖሬሽን አጠቃላይ አገልግሎቶቹን በ66 አገራት እንደሚሰጥ ከድረ ገጹ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል። ከተሰማራባቸው ዘርፎች መካከል የመገናኛ ብዙሃን እና ቴሌኮምዩኒኬሽን ቅርንጫፉ 11.9 በመቶ ድርሻ ይይዛል።

እንደ አውሮፓውያኑ በ1919 ኦሳካ ኖርዝ ሀርበር በሚል ስያሜ ከተቋቋመ በኋላ በተለያዩ ዘርፎች የተሰማራው ድርጅቱ፤ በምሥራቅ እስያ፣ በአውሮፓ፣ በአፍሪካ፣ በመካከለኛው ምሥራቅና ሌሎችም የዓለም ክፍሎች ውስጥ ይንቀሳቀሳል።

ሲዲሲ ግሩፕ

የብሪታንያው ሲዲሲ ግሩፕ እንደ አውሮፓውያኑ በ1948 ከተመሠረተ ወዲህ ላለፉት 70 ዓመታት በፋይናንስ ዘርፍ ሲሠራ ቆይቷል።

በተመሠረተበት የመጀመሪያዎቹ ዓመታት በዛምቢያ የሲሚንቶ ዘርፍ፣ በቦትስዋና የከብር እርባታ ዘርፍና በሌሎችም የአፍሪካ እና እስያ አገሮች ውስጥ ሠርቷል።

በ1998 ላይ ሴልቴል በተባለ የአፍሪካ የሞባይል ስልክ ድርጅት ኢንቨስት ማድረጉ ከቴሌኮም ዘርፍ እንቅስቃሴው አንዱ ነው።

በድረ ገጹ ላይ በሚገኘው መረጃ መሠረት፤ በተለያዩ አገሮች በጥቃቅን እና አነስተኛ ንግድ፣ በጤና እና ሌሎችም ዘርፎች ኢንቨስት ማድረግ ይቻላል።

ከፍተኛ ኢንቨስትመንት የተደረገባቸው አገራት ሕንድ፣ ናይጄሪያ፣ ኬንያ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ኮትዲቯር ናቸው።