የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን በቶኪዮ አየር ማረፊያ ያጋጠመው ምን ነበር?

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን

የፎቶው ባለመብት, ENA

በቶኪዮ ኦሊምፒክ ለመሳተፍ ወደ ጃፓን ያመራው የመጀመሪያ ዙር የኢትዮጵያ ቡደን ቶኪዮ አየር ማረፊያ ከደረሰ በኋላ ለሰዓታት በአየር ማረፊያ እንዲቆይ መደረጉ ተገልጿል።

በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ማክስኞ አመሻሽ ወደ ቶኪዮ የበረረው ቡድኑ፤ የኮቪድ-19 ምርመራ ሰርተፊኬቶች ሲመረመሩ እና በአየር ማረፊያ የተደረገው ፈጣን የኮቪድ-19 ምርመራ ውጤት እስኪመጣ ድረስ ለሰዓታት በአየር ማረፊያ ለመቆየት መገደዱ ተነግሯል።

ከቡድኑ ጋር አብራ የተጓዘችው ጋዜጠኛ አርያት ራያ የኢትዮጵያ ልዑክ በበረረበት አውሮፕላን ውስጥ ተሳፋሪ ከነበሩት አትሌቶች መካከል የአንጎላ ዜግነት ያለው አንድ አትሌት በኮቪድ-19 መያዙ መረጋገጡን ተከትሎ ለሌላ ተጨማሪ ሰዓት በአየር ማረፊያው ለመቆየት መገደዳቸውን ለቢቢሲ አስረድታለች።

በረራው ረዥም ነበር የምትለው ጋዜጠኛ አርያት፤ በደቡብ ኮሪያ በኩል ትራንዚት አድርገው ቶኪዮ ለመድረስ ከ15 ሰዓታት በላይ መውሰዱን ታስረዳለች።

"ብዙ ነበርን። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ብቻ አልነበረም። የደቡብ አፍሪካ ብሔራዊ ቡድን፣ የማደጋስካር፣ የታንዛኒያ፣ የአንጎላ ብሔራዊ ቡድን አባላትም ከእኛ ጋር ነበሩ። ብዙ ስፖርተኛ ነበር። ያ ሁሉ የኮቪድ-19 ምርመራ ማድረግ ነበረበት" ያለችው አርያት፤ የኤርፖርቱ ኃላፊዎች ከፍተኛ ጥንቃቄ እያደረጉ ስለነበረ የኮቪድ-19 ምርመራውን በፍጥነት እያከናወኑ አልነበረም ትላለች።

"ፓስፖርት አይተው እስኪያጣሩ፤ ይዘን የሄድነውን የኮቪድ-19 ምርመራ ውጤት እስኪያረጋግጡ እና የኮቪድ-19 ውጤታችን እስኪመጣ ድረስ ረዥም ሰዓት ነው የወሰደው። ወደ ሰባት ሰዓት ያህል አየር ማረፊያ ውስጥ ቆይተን ነበረ። ምርመራ ጨርሰን፤ ውጤታችንን አይተን ልንወጣ ስንልን አንድ የአንጎላ አትሌት ውጤቱ ፖዘቲቭ ሆነ ተብሎ እንደገና ትንሽ ቆይታ አድርገን ነው የወጣነው" ብላለች።

በመጀመሪያ ዙር ወደ ቶኪዮ ካቀኑት መካከል የኢፌድሪ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ሂሩት ካሳው (ዶ/ር)፣ የስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ኤሊያስ ሽኩር፤ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት አሸብር ወልደጊዮርጊስ (ዶ/ር) እና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ ይገኙበታል።