ከዋይት ሃውስ በቅርብ ርቀት በተከፈተ ተኩስ ሰዎች ተጎዱ

ጥቃቱ የተፈጸመበት ቦታ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በዋሽንግተን ዲሲ ከዋይት ሃውስ 1.5 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በሚገኝ ምግብ ቤት ላይ አንድ የታጠቀ ግለሰብ በከፈተው የተኩስ እሩምታ ሁለት ሰዎች ተጎዱ።

ከ 20 በላይ ጥይቶች ወደ ምግብ ቤቱ የተተኮሱ ሲሆን በበረንዳው ላይ ሲመገቡ የነበሩ ሰዎች ራሳቸውን ለማዳን ሲሸሹ ታይተዋል።

የአይን እማኞች እንዳሉት ታጣቂው ሎጋን አካባቢ ወደሚገኘው የሜክሲኮ ምግብ ቤት ከተኮሰ በኋላ በመኪና ሸሽቷል።

ሁለት ሰዎች በጥይት የተጎዱ ሲሆን የአካባቢው ፖሊሶች ከመካከላቸው አንዱ የጥቃቱ ዒላማ የነበረው ሰው እንደሆነ አምነዋል። በመላው አሜሪካ የሃይል ጥቃቶች እየቀነሱ ቢመጡም በጦር መሳሪያ የሚደርሱ ጥቃቶች ግን እየጨመሩ ይገኛሉ።

በዋሽንግተን ዲሲ አኃዛዊ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከ2018 ጀምሮ በየዓመቱ በጦር መሳሪያ የተፈጸሙ ጥቃቶች ቁጥር ከፍ ብሏል። በ2021 እስከ አሁን ድረስ ብቻ 471 በጦር መሳሪያ የተፈጸሙ ጥቃቶች ሪፖርት የተደረጉ ሲሆን ባለፈው ዓመት በዚህ ወቅት የደረሱ ጥቃቶች ቁጥር 434 ነበሩ።

ሆኖም ዋሽንግተን ውስጥ አብዛኛዎቹ የጦር መሳሪያ ጥቃቶች የሚከሰቱት በደቡብ ምስራቅ እና በሰሜን ምስራቅ አካባቢዎች ሲሆን እነዚህም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች የመኖሪያ አካባቢዎች ናቸው።

የፖሊስ አዛዡ ሮበርት ኮንቴ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት ፖሊሶች ሃሙስ ማታ ለነበረው የተኩስ ልውውጥ በአምስት ሰከንድ ጊዜ ውስጥ መልስ መስጠታቸውን እና ይህም ሌላ መሰል ክስተት በአካባቢው እየመረመሩ ስለነበር መሆኑን ተናግረዋል።

ጥቃቱን ከተመለከቱት ሰዎች መካከል የሆኑት የሲኤንኤን አቅራቢ ጂም አኮስታ ይገኝበታል። የተኩስ ልውውጥ የሚመስል ነገር መስማታቸውን እና አቅራቢያቸው ከሚገኘው ታዋቂው ሌ ዲፕሎማት ከተሰኘው ሬስቶራት ሰዎች እየሮጡ ሲወጡ መመልከታቸውን በትዊተራቸው አስፍረዋል።

የ 27 ዓመቷ ጄስ ዴቪድሰን የተኩስ በተከፈተበት ወቅት በሜክሲኮ ምግብ ቤት ውስጥ ነበረች። "በጣም አስፈሪ ነው። የምሞት መስሎኝ ነበር። በአሜሪካ ውስጥ ስኖር ሁል ጊዜ የምፈራው ነገር ነው፤ ግን ለዚያ ጊዜ ምንም ነገር ሊያዘጋጅህ አይችልም" ስትል ስሜቷን አስረድታለች።

"በሚያበሳጭ ሁኔታ - ሰዎች በገበያ ማዕከሎች፣ በስፖርት ጨዋታዎች፣ በፊልም ቲያትሮች፣ በትምህርት ቤቶች ውስጥ በሚገኙበት ጊዜ በየቀኑ እኔ እንደሚሰማኝ አይነት የፍርሃት ስሜት ይሰማቸዋል" ስትልም አክላለች።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በአንዳንድ የጦር መሳሪያ አይነቶች ላይ ጠበቅ ያሉ ሕጎችን እና መሳሪዎች ለሰዎች ከመሸጣቸው በፊት ተጨማሪ የኋላ ታሪክ ፍተሻዎችን በማካሄድ በጦር መሳሪያ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ለመቆጣጠር ቃል ገብተው ነበር።

ሆኖም የጦር መሳሪያ የመያዝ መብት በአሜሪካ ሕገ-መንግስት የተጠበቀ ነው። ብዙ ሰዎች የጠመንጃ ቁጥጥር ሕጎች ይህንን ሕገ-መንግስታዊ መብት የሚጥሱ ናቸው ሲሉ ይሞግታሉ።

ሀሙስ ዕለት የአሜሪካ የፍትህ መምሪያ ዋሺንግተን ዲሲን ጨምሮ በአምስት ቁልፍ ስቴቶች ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን ለመግታት አዲስ ሃይል እንዳቋቋመ ይፋ አድርጓል።